1በእነዚያም ወራት ለእነዚያ መላእክት ረጃጅሞች ገመዶች ሲሰጡ አየሁ፤ 2ለእነርሱም ክንፍን ተቀብለው ፈጥነው ወደ መስዕ ሄዱ። 3“እኔም እነዚህን ረጃጅሞች ገመዶችን ይዘው ለምን ሄዱ?” ብዬ መልአኩን ጠየቅሁት። 4እርሱም- “ይለኩ ዘንድ ሄዱ” አለኝ። 5ከእኔ ጋር የሚኖረውም መልአክ- “እኒህ ለዘለዓለሙ በመናፍስት ጌታ ስም ይጸኑ ዘንድ የጻድቃንን መለኪያና ማሰሪያ ገመድ ያመጣሉ። 6የተመረጡት ከተመረጡት ጋር ለመኖር ይጀምራሉ። 7እነዚህም መለኪያዎች በሃይማኖት የሚሰጡና የጽድቅ ቃልን የሚያጸኑ ናቸው። 8እነዚህም መለኪያዎች በምድረ በዳ የጠፉት፥ በባሕር ዓሣና በአራዊት የተበሉት በአስታራቂው ቀን ተመልሰው ይጸኑ ዘንድ የምድር ጥልቀት ምሥጢርን ሁሉ ይገልጣሉ። 9በመናፍስት ጌታ ፊት የሚጠፋ የለምና። መጥፋትም የሚችል የለምና። 10በሰማይ ያሉና ሠራዊትም ሁሉ ትእዛዝን ተቀበሉ፤ ቃላቸው አንድ ነው፤ ብርሃናቸውም እንደ እሳት አንድ ነው። 11ያንም ቀዳማዊ ቃል ያመሰግኑታል፤ ከፍ ከፍም ያደርጉታል፤ በጥበብም ያከብሩታል። 12በነገርና በሕይወት መንፈስ ይራቀቃሉ፤ የመናፍስት ጌታም አስታራቂውን በጌትነቱ ዙፋን አስቀመጠው። 13በሰማያት ላይም የቅዱሳንን ሥራ ይመረምራል፤ የሁሉም ሥራቸው በሚዛን ይመዘናል። 14በመናፍስት ጌታ ስም ቃል የተሰወረች መንገዳቸውንና በልዑል እግዚአብሔር እውነተኛ ፍርድ መንገድ ላይ ያለች ፍለጋቸውን ይመረምር ዘንድ ፊቱን በአቀና ጊዜ፥ 15ሁሉም በአንድ ቃል ይናገራሉ፤ የመናፍስት ጌታ ስምንም ያመሰግናሉ፤ ያከብራሉም፤ ከፍ ከፍም ያደርጋሉ፤ ይቀድሳሉም። 16እርሱም የሰማያት ሠራዊትን ሁሉ፥ በልዕልና ያሉ ቅዱሳንንም ሁሉ ይጠራል። 17የእግዚአብሔር ሠራዊት ኪሩቤልና ሱራፌል፥ አፍኒን፥ የኀይላት መላእክት ሁሉ፥ የአጋእዝት መላእክትም ሁሉ፥ የተመረጠውም፥ 18በየብስና በደሴት የሚኖረው ሌላው ኀይልም በዚያች ቀን አንድ ቃል ተቀብለው በሃይማኖት መንፈስ፥ በጥበብና በትዕግሥት መንፈስ፥ 19በምሕረት መንፈስ፥ በፍርድና በሰላም መንፈስ፥ በቸርነት መንፈስ ይባርካሉ፤ ያከብራሉ፤ ያመሰግናሉም፤ ከፍ ከፍም ያደርጋሉ። 20ሁሉም በአንድ ቃል “ቡሩክ ነው፥ የመናፍስት ጌታ ስምም ለዘለዓለም ይክበር ይመስገን” ይላሉ። 21የማያንቀላፉ ሁሉ እስከ ዘለዓለም ድረስ በሰማያት ያመስግኑታል። በሰማያት ያሉ ቅዱሳኑ ሁሉ ያመሰግኑታል፤ በሕይወት ገነት የሚኖሩ የተመረጡት ሁሉ ያመሰግኑታል። 22ቅዱስ ስምህን ማመስገን፥ ማክበር፥ ከፍ ከፍ ማድረግና መቀደስ የምትችል የብርሃን መንፈስ ሁላ ታመሰግነዋለች። 23ሥጋም ሁሉ- በብዙ ኀይል ስምህን ለዘለዓለም ታከብራለች፤ ታመሰግናለች። የመናፍስት ጌታ ምሕረቱ ብዙ ነውና፤ ከመዓትም የራቀ ነውና። 24ሥራውን ሁሉና ኀይሉን ሁሉ፥ የሥራውንም መጠን በመናፍስት ጌታ ስም ለጻድቃንና ለተመረጡት ገለጠ። 25ጌታም ለነገሥታትና ለአዛዦች፥ ለልዑላንና በምድር ለሚኖሩ እንዲህ አዘዘ። 26“አስታራቂውን ማወቅ ትችሉ እንደ ሆነ ዓይኖቻችሁን ግለጡ፤ ሥልጣናችሁንም አንሡ” አለ። 27የመናፍስት ጌታም በጌትነቱ ዙፋን ተቀመጠ፤ የጽድቅ መንፈስም በእርሱ ተገለጠ። 28የአንደበቱም ነገር ኃጥኣንን ሁሉና ዐመፀኞችን ሁሉ ይገድላል። እነርሱም ከፊቱ ይጠፋሉ። 29በዚያችም ቀን ነገሥታትና አዛዦች ሁሉ፥ ልዑላንና ምድርን የሚገዟት ሁሉ ይቆማሉ። 30በጌትነቱም ዙፋን እንደ ተቀመጠ ያዩታል፤ ያውቁታልም፤ ጽድቅም በፊቱ ይፈረዳል። 31በፊቱም የሚነገር ዋዛ ፈዛዛ የለም። 32በምጥ እንደ ተያዘች፥ ልጅዋም በአፈ ማኅፀኗ በመጣ ጊዜ መውለዱ እንደሚያስጨንቃት፥ ለመውለድም እንደምትጨነቅ ሴት መከራው ይመጣባቸዋል። 33እኩሌቶቹ እኩሌቶቹን አይተው ይደነግጣሉ፤ አንገታቸውንም ይደፋሉ። 34ያንም የሰው ልጅ በጌትነቱ ዙፋን ተቀምጦ በአዩት ጊዜ መከራው ይይዛቸዋል። 35ነገሥታትና አዛዦች፥ ምድርን የሚገዙአትም ሁሉ የተሰወረውን ሁሉ የሚገዛውን ያከብሩታል፤ ያመሰግኑታል፤ ከፍ ከፍም ያደርጉታል። 36የሰው ልጅ ከጥንት ጀምሮ የተሰወረ ሆኖ ነበርና፥ ልዑልም በሠራዊቱ ፊት ጠበቀው፤ ለተመረጡትም ገለጠው፤ የቅዱሳንና የተመረጡት ማኅበራቸው ይሰፋል። 37በዚያች ቀንም የተመረጡት ሁሉ በፊቱ ይቆማሉ። 38ነገሥታትና አዛዦች፥ ልዑላንና ምድርን የሚገዟትም ሁሉ በፊቱ በግንባራቸው ወድቀው ይሰግዳሉ። 39ያንም የሰው ልጅ ተስፋ ያደርጉታል፤ ይማልዱታልም፤ ከእርሱም ዘንድ ምሕረትን ይለምናሉ። 40ከዚያ በኋላም ያ የመናፍስት ጌታ ከፊቱ ፈጥነው ይወጡ ዘንድ ያስቸኵላቸዋል። 41ፊታቸውም ኀፍረትን ይሞላል፤ ፊታቸውም ጥቍረትን ይጨምራል። 42ልጆቹንና የመረጣቸውን በበደሏቸው ሰዎች ፍዳን ያመጡባቸው ዘንድ የመቅሠፍት መላእክት ይቀበሏቸዋል። 43ለመረጣቸውና ለጻድቃኑም አርአያ ይሆናሉ። 44በእነርሱም ደስ ይላቸዋል፤ የመናፍስት ጌታ ቍጣው በእነርሱ ላይ ታርፋለችና፥ የመናፍስት ጌታ ሾተልም ከእነርሱ የተነሣ ትሰክራለችና። 45ጻድቃንና የተመረጡትም በዚያች ቀን ይድናሉ። 46ከእንግዲህም ወዲህ የኃጥኣንና የዐመፀኞችን ፊት አያዩም፤ የመናፍስት ጌታም በእነርሱ ያድራል። 47ከዚያም ከሰው ልጅ ጋር ይኖራሉ፤ ይበላሉ፤ ይጠጣሉም፤ ያርፋሉም፤ ለዘለዓለሙም ይነሣሉ። 48ጻድቃንና የተመረጡትም ከምድር ተነሡ፤ አንገታቸውንም መድፋት ተዉ። 49የክብር ልብስንም ለበሱ፤ እርሱም በመናፍስት ጌታ ዘንድ የሕይወት ልብስ ይሆናችኋል። 50ልብሶቻችሁም አያረጁም፤ ክብራችሁም በመናፍስት ጌታ ፊት አይፈጸምም። 51በእነዚያም ወራቶች ምድርን የሚገዟት ነገሥታትና አዛዦች ተላልፈው በተሰጡበት ቦታ ጥቂት ዕረፍትን ይሰጧቸው ዘንድ፥ በመናፍስት ጌታ ፊትም ወድቀው ይሰግዱ ዘንድ ለመቅሠፍት ከታዘዙ መላእክት ይለምናሉ። 52ኀጢአታቸውን በፊቱ ያምናሉ ፤ የመናፍስት ጌታንም ያመሰግኑታል፤ ያከብሩታልም። 53እንዲህም ይላሉ- “የመናፍስት ጌታ፥ የነገሥታት ጌታ፥ የአዛዦች ጌታ፥ የባለጸጋውም ጌታ፥ የክብር ጌታ፥ የጥበብም ጌታ እግዚአብሔር፥ ቡሩክ ነህ። የተሰወረም ሁሉ በአንተ ይገለጣል። 54ኀይልህም ለልጅ ልጅ ዘመን ነው፤ ጌትነትህም ለዘለዓለም ነው። 55ምሥጢርህም ሁሉ ጥልቅ ነው፤ ቍጥርም የለውም። ለቸርነትህም ቍጥር የለውም። 56አሁንም የነገሥታቱን ጌታ፥ በነገሥታቱም ሁሉ ላይ የሚነግሥውን እናከብርና እናመሰግን ዘንድ ዐወቅን” አሉ። 57እንዲህም አሉ- “እናከብረው፥ ፈጽመንም እናመሰግነው ዘንድ፥ ጌትነቱንም እናምን ዘንድ ዕረፍትን ማን በሰጠን? 58አሁንም ጥቂት ዕረፍትን እንመኛለን፤ ነገር ግን አናገኘውም፤ እንከተለዋለን፤ ግን አንይዘውም። 59ብርሃን ከእኛ አለፈ። ጨለማም ለዘለዓለሙ መኖሪያችን ነው። በፊቱ አላመንምና፥ የመናፍስት ጌታ ስሙንም አላመሰገንምና። 60ጌታንም በሥራው ሁሉ አላመሰገንነውም፤ አለኝታችንም በመንግሥታችንና በጌትነታችን ዙፋን ሥልጣን ላይ ሆነ። 61በድካማችንና በመከራችን ቀንም አላዳነንም። 62እናምንም ዘንድ ዕረፍትን አናገኝም፤ ጌታችን በሥራው ሁሉ፥ በፍርዱና በቸርነቱም ሁሉ የታመነ ነውና። 63የፍርዱንም ፊት አያገኙም፤ ስለ ሥራችንም ከፊቱ እንሄዳለን፤ ኀጢአታችንም ሁሉ በጽድቅ ተቈጠረ፤” 64አሁንም እንዲህ ይሏቸዋል- “ሰውነታችን ከዐመፅ ገንዘብ ትጠግባለች፤ ወደ ሲኦል መከራ ትኩሳት ከመውረድም አታድነንም።” 65ከዚህም በኋላ በዚያ በሰው ልጅ ፊት ፊታቸው ጨለማንና ኀፍረትን ይሞላል። 66ከፊቱም ተሰድደው ይሄዳሉ፤ በመካከላቸውም በፊቱ ሰይፍ ያድራል። 67የመናፍስትም ጌታ እንዲህ አለ- “የአዛዦችና የነገሥታት፥ የልዑላንና ምድርን የሚገዟት ሰዎች ሥርዐታቸው፥ ፍርዳቸውም በመናፍስት ጌታ ፊት ይህ ነው።” 68በዚያም ቦታ የተሰወሩ ሌሎች ፊቶችን አየሁ። 69የመልአኩንም ቃል እንዲህ ሲል ሰማሁ- “ከሰማይ ወደ ምድር የወረዱ፥ በስውር ያለውንም ለሰው ልጆች የገለጡ፥ ኀጢአትንም ይሠሩ ዘንድ የሰው ልጆችን ያሳትWaቸው መላእክት እኒህ ናቸው።”