1በእነዚያም ወራቶች ኖኅ ምድር እንደ አዘነበለች፥ ጥፋትWaም እንደ ቀረበ አየ። 2ከዚያም እግሩን አንሥቶ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ሄደ። 3ለአያቱ ለሄኖክም ጮኸ፤ ኖኅም በመረረ ቃል ሦስት ጊዜ “ስማኝ፤ ስማኝ፤ ስማኝ” አለ። 4እንዲህም አለው- “በምድር ላይ የሚሠራው ሥራ ምንድን ነው? ንገረኝ! 5ምድር ደክማለችና፥ እንዲህ ተነዋውጣለችና፥ ምንአልባት እነሆ፥ እኔ ከእርስዋ ጋር እጠፋ ይሆን?” 6በዚያም ጊዜ በምድር ላይ ታላቅ ሁከት ሆነ፤ ከሰማይም ቃል ተሰማ። 7በግንባሬ ወደቅሁ፤ አያቴ ሄኖክም ወደ እኔ መጣ፤ በአጠገቤም ቆመ፤ እንዲህም አለኝ- “ወደ እኔ መራራ ጩኸትንና ልቅሶን ለምን ትጮኻለህ? 8እርሱም- ጥፋታቸው ይሆን ዘንድ በምድር በሚኖሩ ሰዎች ላይ ከመናፍስት ጌታ ፊት ትእዛዝ ወጣ። 9የመላእክትን ምሥጢር ሁሉ፥ የሰይጣናትን ግፍ ሁሉ፥ የተሰወረ ሥራቸውንም ሁሉ፥ ሟርት የሚያሟርቱ ሰዎችን ኀይል ሁሉ፥ የቀለማትንም ኀይል፥ የምድርን ሁሉ ጣዖት የሚሠሩ ሰዎችን ኀይል አሳውቀዋልና። 10ብር ከመሬት ትቢያ እንዴት ይገኝ ነበር? ቅልቅል ብረትስ በምድር ላይ እንዴት ይገኝ ነበር? 11እነርሱን የሚያስገኛቸው መሬትና በውስጥዋ የሚቆመው መልአክ መጀመሪያ ምንጭ እንደ ሆኑ እርሳስና ቆርቆሮ ከምድር አይገኙም ነበርና፤ 12ከዚያም በኋላ አያቴ ሄኖክ በእጁ ይዞ አነሣኝ። 13እንዲህም አለኝ- “በምድር ላይ ስላለው ሁከት የመናፍስትን ጌታ ጠይቄዋለሁና ሂድ።” 14እንዲህም አለኝ- “ስለ በደላቸው ፍርዳቸው ተፈጸመችባቸው፤ ስለ ፈለጓቸውም ወራቶች በፊቴ አይቈጠሩም። 15ምድርም እንደምትጠፋ፥ በእርሷም የሚኖሩ ሰዎች እንደሚጠፉ ዐወቁ፤ እኒህም የተሰወረውን ለሰዎች አስተምረዋልና፥ እነርሱም የተፈረደባቸው ናቸውና ለዘለዓለም መመለሻ የላቸውም። 16ነገር ግን አንተ ልጄ! ከዚህ ከተሰወረው ነቀፋ አንተ ንጹሕና ቸር እንደ ሆንህ የመናፍስት ጌታ ዐውቋልና ይህ ለአንተ አይደለም። 17በቅዱሳን መካከልም ስምህን አጸናው፤ በምድርም ላይ ከሚኖሩት ለይቶ ይጠብቅሃል። 18ለመንግሥትና ለብዙ ምስጋናም ሊሆን ዘርህን በእውነት አጸናው፤ ከዘርህም የጻድቃንና የቅዱሳን መገኛ ይወለዳል፤ ለዘለዓለሙም ቍጥር የላቸውም።” 19ከዚህም በኋላ እንዲመጡ በምድር ላይ በሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ለፍርድና ለጥፋት ሊሆን ከምድር በታች ያለ የውኃውን ኀይል ሁሉ መጥተው ይከፍቱ ዘንድ የተዘጋጁ የመቅሠፍት መላእክትን አሳየኝ። 20የመናፍስት ጌታም እነዚያ መላእክት በውኃው ኀይል ላይ ተሾመዋልና የወጡትን መላእክት እጃቸውን እንዳያነሡ፥ እንዲጠብቁም አዘዘ። 21ከሄኖክም ፊት ወጣሁ። 22በእነዚያም ወራቶች የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ መጣ። 23እንዲህም አለኝ- “ኖኅ! እነሆ፥ ዕድል ፋንታህ ወደ እኔ ደረሰ፤ “ነቀፋ የሌለበት ዕድል የፍቅርና የቅንነት ዕድል ነው።” 24አሁንም መላእክት እንጨቶችን ያዘጋጃሉ፤ እነርሱም ለዚያ መልእክት በወጡ ጊዜ እጄን በላይዋ ጭኜ እጠብቃታለሁ። 25ከእርስዋም ወጥተህ የሕይወት ዘር ትሆናለህ፤ ምድርም ባዶውን እንዳይቀር ለውጡ ይግባ። 26ዘርህንም ለዘለዓለም በፊቴ አጸናዋለሁ፤ ከአንተ ጋራም የሚኖሩ ዘሮችህን በምድር ፊት አበዛቸዋለሁ። 27በመናፍስትም ጌታ ስም በምድር ላይ ይበዛል፤ ይባረካልም። 28ዐመፅን የአሳዩ እነዚያን መላእክትም 29ታላቅ ሁከትና የውኃዎች መታወክ ያለባትንም ያችን ሸለቆ አየኋት። 30ይህ ሁሉ ከተደረገ በኋላ፥ ከዚህ ከእሳቱ ነጠብጣብ የተነሣ ከሚያውካቸውም ሁከት የተነሣ በዚያ ቦታ የድኝ ሽታ ተገኘ፤ ከእነዚያም ውኃዎች ጋር አንድ ሆነ። 31ያችም ሰውን የአሳቱ የመላእክት 32የእሳት ፈሳሾችም በምድር ላይ የሚኖሩትን ያሳትWaቸው መላእክት በሚኰነኑበት ቦታ ወደ ሸለቆዎችዋ ይፈስሳሉ። 33በእነዚያም ወራት እነዚህ ውኃዎች ለነገሥታቱና ለአዛዦች፥ ለልዑላንና በምድር ለሚኖሩ ሰዎች፥ ለነፍስና ለሥጋ ፈውስ፥ ለመንፈስም ፍርድ ይሆናሉ። 34የመናፍስት ጌታን ክደውታልና በሥጋቸው ይፈረድባቸው ዘንድ ልቡናቸው ዋዛ ነገርን ይመላል። 35የየቀኑን ሁሉ ፍርዳቸውንም ያያሉ፤ በስሙም አያምኑም። 36በመናፍስት ጌታ ፊት ዋዛ ፈዛዛ የሚናገር የለምና፥ ሥጋቸው ብዙ ጊዜ እንደ ተቃጠለ እንደዚሁ በነፍሳቸው ለዘለዓለሙ ለውጥ ይኖርባቸዋል። 37በእነርሱ ላይ ፍርድ ትመጣለችና፥ በሥጋቸውም ዋዛ ነገር ያምናሉና፥ የጌታንም መንፈስ ይክዳሉና። 38በዚያም ወራት እነዚያ ውኃዎች ለውጥ ይኖራቸዋል፤ እነዚያ መላእክት በሚፈረድባቸው ጊዜ በዚያ ወራት የእነዚያ የውኃዎች ምንጮች መቃጠል ይለወጣልና። 39መላእክትም በወጡ ጊዜ የምንጮች ውኃ ተለውጦ ይቀዘቅዛል። 40ቅዱስ ሚካኤልንም እንዲህ ብሎ ሲመልስ ሰማሁት- “አለቆች የሚቀጡባት ይህች ፍርድ ለነገሥታትና ምድርን ለሚቈጣጠሩ አዛዦች ምስክር ናት፤ እኒህ የቅጣት ውኃዎች ለአለቆች ሥጋ ፈውስ፥ ለሥጋቸውም ለሞት ናቸውና።” 41እነዚያ ውኃዎች ተለውጠው ለዘለዓለም የሚነድድ እሳት እንደሚሆኑባቸው አያዩም፤ አያምኑምም። 42ከዚህም በኋላ አያቴ ሄኖክ የተሰጡትን የምሥጢሮችን ሁሉና የምሳሌዎችን ምልክት በመጽሐፍ ሰጠኝ፤ በእኔ ዘንድ ከአለው የመጽሐፍ ቃል ጋርም ጨመራቸው።