1ከብዙ ቀንም በኋላ ልጄ ማቱሳላ ለልጁ ላሜህ ሚስት አጋባው፤ ከእርሱም ፀንሳ ወንድ ልጅን ወለደች። 2ሰውነቱም እንደ በረዶ ነጭ ሆነ፥ እንደ ጽጌረዳም ቀይ ነው፤ የራሱም ጠጕር እንደ ባዘቶ ነጭ ነው፤ የተሸራሸም ነው፤ ዐይኖቹም ያማሩ ናቸው። 3ዐይኖቹንም በገለጠ ጊዜ ቤቱን ሁሉ እንደ ፀሐይ አበራ፤ ቤቱም ሁሉ ፈጽሞ በራ፤ ከአዋላጂቱም እጅ በተነሣ ጊዜ አፉን ከፈተ፤ የጽድቅ ጌታንም ክብር ተናገረ። 4አባቱ ላሜህም ከእርሱ የተነሣ ፈርቶ ሸሸ፥ ወደ አባቱም ወደ ማቱሳላ መጣ፤ እንዲህም አለ- “እኔ ልውጥ ልጅ ወለድሁ፤ እንደ ሰውም አይደለም። 5የሰማይ መላእክት ልጆችንም ይመስላል፤ ፍጥረቱም ልዩ ናት፤ እንደ እኛም አይደለም፤ ዐይኖቹም እንደ ፀሐይ ጨረር ናቸው፤ ፊቱም የበራ ነው። 6ከመላእክት ነው እንጂ ከእኔ ያልተወለደ ይመስለኛል፥ እኔስ በምድር ላይ በዘመኑ ድንቅ ሥራ እንዳይሠራ ብዬ እፈራለሁ። 7“አሁንም አባቴ ወደ አባታችን ወደ ሄኖክ ትሄድና እውነቱን ከእርሱ ትሰማ ዘንድ እማልድሃለሁ፤ እለምንሃለሁም። መኖሪያው ከመላእክት ጋር ነውና።” 8ማቱሳላም የልጁን ነገር በሰማ ጊዜ እኔ በዚያ እንደ አለሁ ሰምትWaልና ወደ ምድር ዳርቻ ወደ እኔ መጣ። 9ጮኸ፤ እኔም ቃሉን ሰማሁት። ወደ እርሱም መጣሁ፤ “ወደ እኔ መጥተሃልና ልጄ፥ እነሆ፥ አለሁ” አልሁት። 10እርሱም መለሰልኝ፥ እንዲህም አለኝ- “ስለ ታላቁ ነገርና ስለ ቀረብሁበት አስጨናቂ ራእይ ወደ አንተ መጣሁ። 11አሁንም አባቴ ሆይ! ስማኝ፤ መልኩና ፍጥረቱ እንደ ሰው ፍጥረት ያልሆነ፥ መልኩም ከበረዶ ይልቅ የሚነጣ፥ ከጽጌረዳም የሚቀላ፥ የራሱም ጠጕር ከነጭ ባዘቶ ይልቅ የሚነጣ፥ ዐይኖቹም እንደ ፀሐይ ጨረር የሚያበሩ ልጅ ለልጄ ለላሜህ ተወልዷልና። 12ዐይኖቹንም በገለጠ ጊዜ ቤቱን ሁሉ አበራ፤ ከአዋላጂቱም እጅ ተነሣ፤ አፉንም ፈትቶ የሰማይን ጌታ አመሰገነው። 13አባቱ ልጄ ላሜህም ፈርቶ ወደ እኔ ሸሸ፤ ከሰማይ መላእክት የተወለደ አስመሰለው እንጂ ከእርሱ እንደ ተወለደ አላመነም። 14እነሆም፥ እውነቱን ትነግረኝ ዘንድ እኔ ወደ አንተ መጣሁ።” 15እኔም ሄኖክ ስለ እርሱ መለስሁ፥ እንዲህም አልሁት- “እግዚአብሔር በምድር ላይ አዲስ ነገርን ያደርጋል፤ የአባቴ የያሬድ የልጁ ወገኖች ከሰማይ በላይ ያለ የጌታን ቃል ተላልፈዋልና ይህን በራእይ ፈጽሜ አይቼ ነገርሁህ። 16እነኋቸው፥ ኀጢአትን ይሠራሉ፤ ሥርዐቱንም ይተላለፋሉ፤ ከሴቶችም ጋር አንድ ሆኑ፤ ከእነርሱም ጋር ኀጢአትን ይሠራሉ፤ ከእነርሱም ሚስቶችን አገቡ፤ ከእነርሱም ልጆችን ወለዱ፤ በምድርም ሁሉ ላይ ታላቅ ጥፋት ይደረጋል። 17የጥፋት ውኃም ይወርዳል፤ ታላቁም ጥፋት በአንዱ ዓመት ይደረጋል፤ ለእናንተም የተወለደው ልጅ ይህ ነው፤ እርሱ በምድር ላይ ይቀራል፤ ሦስቱ ልጆቹም ከእርሱ ጋራ ይድናሉ። 18በምድር ላይ ሰው ሁሉ በሚሞትበት ጊዜ እርሱ ይድናል፤ ልጆቹም አርበኞችን ይወልዳሉ፥ እነዚህም ሥጋውያን እንጂ መንፈሳውያን አይደሉም። 19ታላቅ መቅሠፍትም በምድር ላይ ይደረጋል፤ ምድርም ከጥፋት ሁሉ ትነጻለች። 20“አሁንም ይህ የተወለደ ልጅ በእውነት የእርሱ ልጅ እንደ ሆነ ለልጅህ ለላሜህ ንገረው፤ እርሱም ቀሪ ይሆንላችኋልና ስሙን ኖኅ ብለህ ጥራው፤ በእርሱ ዘመን በምድር ላይ ትፈጸም ዘንድ ካላት ከኀጢአት ሁሉና ከዐመፅ ሁሉ የተነሣ ወደ ምድር ከምትመጣ ጥፋት እርሱና ልጆቹ ይድናሉ። ከዚህም በኋላ በምድር ላይ አስቀድማ ከተፈጸመችው ይልቅ ፈጽማ የምትበልጥ ዐመፅ ትደረጋለች፤ የቅዱሳንን ምሥጢራት ዐውቃለሁና። እርሱ እግዚአብሔር ገልጦልኛልና፥ አስረድቶኛልምና፤ በሰማይ ሰሌዳም አነበብሁ፤ አስተዋልሁም። 21“እውነተኛ ትውልድ እስክትነሣ ድረስ ትውልድ ከትውልድ ይልቅ አብልጣ ትበድላለችና በእነርሱ ላይ የተጻፈውን አየሁ፤ በደልም ትጠፋለች፤ ኀጢአትም ከምድር ላይ ትርቃለች፤ በጎውም ነገር ሁሉ በእርሷ ላይ ይመጣል፤ አሁንም ይህ የተወለደው ልጅ በእውነት የእርሱ ልጅ ነውና፥ ሐሰትም አይደለምና ሄደህ ለልጅህ ለላሜህ ንገረው፤” ማቱሳላም የአባቱ የሄኖክን ነገር በሰማ ጊዜ ሥራውን ሁሉ በስውር አሳይቶታልና ነገሩን ሰምቶ ተመለሰ። 22እርሱም ምድርን ከጥፋቷ ሁሉ ያሳርፋታልና የዚያን ልጅ ስም ኖኅ አለው።