1ለልጁ ለማቱሳላ፥ ከእርሱም በኋላ ለሚመጡና በኋላ ዘመን ሥርዐቱን ለሚጠብቁ ሰዎች ሄኖክ የጻፈው ሁለተኛ መጽሐፍ ይህ ነው። 2ክፉውን ሥራ የሚሠሩ ሰዎች እስኪጨረሱ ድረስ፥ የበደለኞችም ሠራዊት እስኪፈጸም ድረስ መልካም የሠራችሁ እናንተ፥ በእነዚያ ወራቶች ትቈያላችሁ። 3እናንተ ግን ኀጢአት እስክታልፍ ድረስ ደጅ ጥኑ። ስማቸው ቅዱሳን ከተጻፉበት መጽሐፍ ይፋቅ ዘንድ አለውና፥ ዘራቸውም ለዘላለም ይጠፋልና። ልጆቻቸውም ይሞታሉ፥ በማይታይም ምድረ በዳ ጮኸው ያለቅሳሉ፤ በእሳትም ይቃጠላሉ፥ በዚያ ምድር የለምና። 4የእሳቱም ወላፈን ሲነድ አየሁት፥ የሚበራም ነበር፤ እንደሚያበሩ ተራሮችም የተከበቡ ነገሮች ነበሩ፥ ወዲያና ወዲህም ይታወካሉ። 5ከእኔ ጋር ካሉ ከቅዱሳን መላእክት አንዱን ጠየቅሁት፥ እንዲህም አልሁት- “ይህ የሚያበራው ምንድን ነው? ሰማይ አይደለምና፥ ነገር ግን ብቻውን የሚነድድ የእሳት ወላፈን፥ የጩኸትና የልቅሶ፥ የዋይታና የብርቱ ሕማም ቃል ነው።” 6እርሱም እንዲህ አለኝ- “ይህ የምታየው ቦታ የኃጥኣንና የተሳዳቢዎች፥ ኀጢኣትን የሚሠሩ፥ 7እግዚአብሔር በነቢያት አንደበት ያናገራቸውን በምድር ላይ ይደረጉ ዘንድ ያላቸውን ሁሉ የሚለውጡ ሰዎች ነፍሳት የሚጣሉበት ቦታ ነው። 8መላእክት ያነብቧቸው ዘንድ፥ በኃጥኣንና በተዋረዱትም ሰዎች መናፍስት ይደርስባቸው ዘንድ ያለውን ያውቁ ዘንድ ከእነርሱ ወገን በላይ በሰማይ የተጻፉና የተቀረጹ አሉና። 9ነገር ግን ሥጋቸውን መከራ ያስቻሉ፥ ከፈጣሪም ዘንድ ዋጋ የተቀበሉ፥ ከክፉ ሰዎችም የተነሣ የተዋረዱ፥ ፈጣሪያቸውንም የወደዱ ወርቅና ብርን፥ በዚህም ዓለም ያለውን በጎ ነገር ሁሉ አይወዱም፤ ነገር ግን ሥጋቸውን ለመከራ ሰጡ፤ ከተፈጠሩም ጀምሮ በዚህ ዓለም ያሉ መብሎችን ያልተመኙ ራሳቸውን እንደ ሞተች ሰውነት አደረጉ። ይህንም ጠበቁ፥ ጌታም ብዙ ጊዜ ፈተናቸው፤ ስሙንም ያመሰግኑ ዘንድ ሰውነቶቻቸው በንጽሕና ተገኙ። 10በረከታቸውንም ሁሉ በመጻሕፍት ተናገርሁ፤ እኒህ ከዘለዓለማዊ ሕይወታቸው ጀምሮ ሰማያዊውን ሲወዱት፥ 11ከክፉ ሰዎችም መከራን ሲቀበሉ፥ ከእነርሱም ተግዳሮትንና ስድብን ሲሰሙ፥ እያመሰገኑኝም ሲጐሳቈሉ ተገኝተዋልና ለእየራሳቸው ዋጋቸውን ሰጣቸው። 12አሁንም ከብርሃን ልጆች የተወለዱ የደጎችን ነፍሳት እጠራለሁ፥ ለሃይማኖታቸው እንደሚገባ በሥጋቸው ክብርን ላልተቀበሉና በጨለማ ለተወለዱ እለውጣለሁ። 13ቅዱስ ስሜንም የወደዱትን በብሩህ ብርሃን አወጣቸዋለሁ፤ እያንዳንዱንም እንደ ክብሩ በክብር ዙፋን አስቀምጠዋለሁ፥ የአምላክም ፍርድ እውነት ነውና ቍጥር በሌላቸው ዘመኖች ያበራሉ። 14በቅን መንገዶች ማደሪያ ለምእመናን ሃይማኖትን ይሰጣቸዋልና። 15ጻድቃን እያበሩ በጨለማ የተወለዱትን በጨለማ ሲጣሉ ያዩአቸዋል፤ ኃጥኣንም እየጮኹ ጻድቃንን ሲያበሩ ያዩአቸዋል። 16እነርሱም በተጻፉላቸው ቀኖችና ዘመኖች ይኖራሉ።