1ዛሬም እኔ በታላቅ ጌትነቱና ክብሩ፥ በከበረ መንግሥቱና በገናናነቱ ለእናንተ ለጻድቃን እምላለሁ። 2ይህንም ምሥጢር እኔ አውቃለሁና፥ በሰማይ ሰሌዳ ያለውን አንብቤአለሁና፥ ቅዱሳን የጻፉትንም አይቻለሁና እምልላችኋለሁ። 3በጎው ነገር ሁሉ፥ ደስታውና ክብሩም ተዘጋጅቶላቸዋልና ስለ እነርሱ በውስጣቸው ተጽፎና ተቀርፆ አገኘሁ። 4በእውነትና በቀና ነገር፥ በብዙም በጎነት ለሞቱ ሰዎች ነፍሳት ተጻፈላቸው፤ የድካማችሁም ዋጋ ይሰጣችኋል፤ እድላችሁም ከሕያዋን እድል ይበልጣል። 5ስለ ጽድቅ የሞታችሁ የእናንተ ነፍስ ትድናለች፤ ነፍሶቻቸውም ደስ ይላቸዋል፤ ሐሤትም ያደርጋሉ። 6መታሰቢያቸውም በእግዚአብሔር ፊት ለልጅ ልጅ ዘመን ይኖራል፤ አሁንም መከራቸውን አትፍሩት። 7የሞታችሁ ኃጥኣን፥ በኀጢአታችሁ በምትሞቱበት ጊዜ ወዮላችሁ! 8እንደ እናንተም ያሉ በእናንተ ላይ እንዲህ ይላሉ፤ ኃጥኣን ብፁዓን ናቸው፤ ዘመናቸውን ሁሉ አይተዋልና። 9ዛሬም በበጎነትና በባለጠግነት ሞቱ፤ መከራውንና ሰልፉንም በሕይወታቸው አላዩም፤ በጌትነትም ሞቱ፤ በሕይወታቸውም ፍርድ አልተደረገባቸውም። 10ነፍሶቻቸው ወደ ሲኦል እንደሚወርዱ፥ ክፋታቸውም ጽኑ መከራ እንደሚሆንባቸው አታውቋቸውምን? 11ሰውነታችሁም በጨለማና በወጥመድ፥ በሚነድ ወላፈንም ወደ ጽኑ ፍርድ ትገባለች፤ ጽኑ ፍርድም በዓለም ትውልድ ሁሉ ትሆናለች። 12ሰላም የላችሁምና ወዮላችሁ! በሕይወት ላሉ ለጻድቃንና ለደጋጎች እንዲህ አትበሉአቸው- “በደከምንበት ወራት ድካምን ደከምን። 13መከራውን ሁሉ አየን፤ ብዙ መከራዎችንም ተቀበልን፤ ጨርሰን ጠፋን፤ አነስን፤ ሰውነታችንም አነሰች፤ ጠፋንም። 14በነገርም የሚረዳን የለም፤ በሥራም ደከምን፤ ምንም አላገኘንም፥ ተጨነቅን፤ ጠፋንም፤ 15ከዛሬ ነገ ሕይወትን እናይ ዘንድ ተስፋ አደረግን፥ ራስ ልንሆን ተስፋ አደረግን፤ ነገር ግን ጅራት ሆን፤ ስንሠራም ደከምን። 16ነገር ግን በድካማችን ላይ ግዳጃችንን አልፈጸምንም፤ ለኃጥኣንም መብሎችን ሆን፤ ዐመፀኞችም ቀንበራቸውን አከበዱብን። 17እኛን የሚጠሉንና የሚወጉን በእኛ ሠለጠኑብን፤ ለሚጠሉንም አንገታችንን ዝቅ አደረግን፤ እነርሱ ግን አልራሩልንም። 18ከእነርሱ እንሸሽና እናርፍ ዘንድ እንድንሄድ ወደድን፤ ከእነርሱም ሸሽተን የምንድንበትን አላገኘንም። 19በመከራችን ጊዜ በአለቆች ዘንድ ከሰስናቸው፤ በሚጠሉንም ላይ ጮህን፤ ጩኸታችንን ግን አልሰሙንም፤ ቃላችንንም ሊሰሙን አይወዱም። 20የሚቀሙንን፥ የሚበሉብንን፥ ያጐደሉብንንም ይረዷቸዋል፤ ግፋቸውንም ይሰውሩላቸዋል፤ ቀንበራቸውን ከእኛ አያወጡም፤ ነገር ግን ይበሉናል። 21ይበትኑናል፤ ይገድሉናል፤ ሞታችንንም ይሰውራሉ፤ እጃቸውንም ከእኛ ላይ ያነሡ ዘንድ አላሰቡም።” 22ጻድቃን! እምልላችኋለሁ፤ መላእክት በገናናው ጌትነት ፊት በሰማይ ስለ እናንተ በጎ ያስባሉና። 23ስሞቻችሁም በገናናው ጌትነት ፊት ይጻፋሉ። አስቀድሞ በክፋትና በድካም ጐስቍላችኋልና ተስፋ አድርጉ። 24አሁንም እንደ ሰማይ ብርሃን አብርታችሁ ትታያላችሁ፤ የሰማይ ደጃፍም ይከፈትላችኋል። 25ጩኸታችሁ ይሰማል፤ ለፍርድ ጩኹ፤ ይገለጥላችሁማል፤ ችግራችሁም ሁሉ ከመላእክትና የሚነጥቋችሁን ከሚረዷቸው ሁሉ ይመረመራልና። 26እንደ መላእክት በሰማይ ታደርጓት ዘንድ ታላቅ ደስታ ትሆንላችኋለችና ተስፋ አድርጉ፤ ተስፋችሁንም አትተዉ፥ በታላቋ የፍርድ ቀንም ትሰወሩ ዘንድ ያላችሁ አይደለም። 27እንደ ኃጥኣንም ሁናችሁ አትገኙም፤ ከእናንተ ወዲያ የዘለዓለም ፍርድ ለዓለም ትውልድ ሁሉ ትሆናለች። 28አሁንም ጻድቃን! ኃጥኣንን በፈቃዳቸው ጸንተውና ተዘጋጅተው በምታይዋቸው ጊዜ አትፍሩ። 29ከሰማይ ሠራዊት ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ አላችሁና ከእነርሱ ግፍ ራቁ እንጂ ከእነርሱ ጋራ አትተባበሩ። 30እናንተ ኃጥኣን! ኀጢአታችን ሁሉ አይመረመርም፤ አይጻፍብንም፥ ትላላችሁ፥ ነገር ግን ኃጢአቶቻችሁ ሁሉ በየቀኑ ይጻፉ ዘንድ አላቸው። 31አሁንም ብርሃንና ጨለማ፥ ቀንና ሌሊት ኀጢአታችሁን ሁሉ ይገልጡባችኋልና እኔ አሳያችኋለሁ፤ በልቡናችሁም አትዘንጉ፤ አቷሹም። 32የፍርድንም ነገር አትመልሱት፤ የቅዱሱንና የገናናውንም ነገር ሐሰት አታድርጉት፤ ጣዖታችሁንም አታክብሩት፥ ሐሰታችሁ ሁሉ፥ ዝንጋታችሁም ሁሉ ለታላቅ ኀጢኣት እንጂ ለጽድቅ አይደለችምና። 33ዛሬም እኔ ይህን ምሥጢር ዐውቀዋለሁ፤ ብዙዎች ኃጥኣን የፍርድን ነገር ይመልሳሉና፥ ይገለብጡማልና። 34ክፉዎችንም ነገሮች ይናገራሉ፤ ታላላቅ ልብ ወለድንም በሐሰት ፈጥረው ይናገራሉ፤ በነገራቸውም ላይ መጻፎችን ይጽፋሉ። 35ነገር ግን ነገሮቼን ሁሉ በቅንነት በአንደበቶቻቸው ቢጽፉ ኖሮ፥ ከነገሮቼም በአይለውጡና በአያጐድሉም ስለ እነርሱ አስቀድሜ ያዳኘሁባቸውን ሁሉ በቅንነት በጻፉ ነበር። 36ሌላ ምሥጢርንም ዐውቃለሁ፤ ለጻድቃንና ለጠቢባን ስለ ደስታና ስለ ቅን ፍርድ፥ ስለ ብዙ ጥበብም መጻሕፍት ይሰጧቸዋልና፤ 37ለእነርሱም መጻሕፍት ይሰጣሉ፤ እነርሱም ያምኑባቸዋል፤ በእነርሱም ደስ ይላቸዋል፤ ሐሤትም ያደርጋሉ፤ ከእነርሱም የእውነት መንገዶችን ሁሉ ያወቁ ጻድቃን ሁሉ ዋጋቸውን ያገኛሉ። 38በእነዚያም ወራቶች ጌታ እንዲጠሯቸውና ጥበባቸውን ለምድር ልጆች እንዲያሰሙ እንዲህ አለ- 39“እናንተ መሪዎቻቸው ናችሁና፥ በምድርም ሁሉ ላይ ስጦታዎች ናችሁና አሳዩአቸው። 40እኔና ልጄ በእውነት መንገዶች በሕይወታቸው ከእነርሱ ጋር ለዘለዓለም አንድ እንሆናለን፤ ሰላምም ይሆንላችኋል፤ የእውነት ልጆች! በእውነት ደስ ይበላችሁ።”