1የሰማይ ልጆች ሁሉ፥ ሰማይን ተረዷት፥ የልዑልንም ሥራ ሁሉ ተረዱ፤ ከእርሱም የተነሣ ፍሩ፤ በፊቱም ክፉ ነገርን አትሥሩ፤ ከእነርሱ የተነሣ ፍሩ። 2የሰማይ ደጃፍን ቢዘጋ፥ ዝናቡንና ጠሉንም በምድር ላይ እንዳይወርድ በእናንተ ምክንያት ቢከለክል ምን ታደርጉ ዘንድ አላችሁ? 3መዓቱንም በእናንተ ላይና በሥራችሁ ሁሉ ላይ ቢልክ እርሱን እናንተ የምትማልዱት አይደላችሁምን? 4በቸርነቱ ላይ ታላላቅና የጸኑ ነገሮችን ትናገራላችሁና ሰላም የላችሁም። 5ከማዕበሉ የተነሣ እንደሚታወኩ፥ መርከቦቻቸውም ከነፋሳት የተነሣ እንደሚነዋወጡና እንደሚጨነቁ በመርከብ የሚሄዱ ነገሥታትን አታይዋቸውምን? 6መልካሙ ገንዘባቸውም ሁሉ ከእነርሱ ጋር ወደ ባሕር ይወጣልና ስለዚህ ይፈራሉ። 7ባሕር ትውጣቸዋለችና፥ በውስጧም ይጠፋሉና በልቡናቸው በጎ ነገርን አያስቡም፤ ባሕሯ ሁሉ፥ ውኃዎችዋም ሁሉ፥ መነዋወጧም ሁሉ የልዑል ሥራ አይደለምን?። 8እርሱ ሥራዋንና ውኃዎችዋን ሁሉ ወሰነ፥ ሁለመናዋንም በአሸዋ ገደበ። 9በተግሣጹም ፈርታ ትደርቃለች፥ ዓሣዎችዋም ሁሉ ይሞታሉ፥ በውስጧም ያለ ሁሉ ይሞታል። 10በምድር ያላችሁ እናንተ ኃጥኣን ግን አትፈሩትም፤ ሰማይንና ምድርን፥ በውስጣቸው ያለውንም ሁሉ የፈጠረ እርሱ አይደለምን? 11በየብስና በባሕር ለሚንቀሳቀሱ ሁሉ ትምህርትንና ጥበብን የሰጠ ማን ነው? በመርከብ የሚሄዱ እነዚያ ባሕርን የሚፈሩ አይደለምን? ኃጥኣን ግን ልዑልን አይፈሩትም። 12በእነዚያ ወራቶች አስጨናቂ እሳትን በላያችሁ ቢጨምር ወዴት ትሸሻላችሁ? በየትስ ትድናላችሁ? 13ቃሉንም በእናንተ ላይ በሚያኖር ጊዜ የምትደነግጡና የምትፈሩ አይደለምን? ብርሃናትስ ሁሉ በታላቅ ፍርሀት የሚደነግጡና የሚታወኩ አይደለምን? 14ምድርስ ሁላ በታላቅ ፍራት የምትደነግጥ፥ የምትንቀጠቀጥና የምትቸኩል አይደለምን? 15መላእክትም ሁሉ የታዘዙትን ይፈጽማሉ፥ ከክብር ጌታም ፊት ሊሰወሩ ይወዳሉ። 16የዓለም ልጆች ይርዳሉ፤ ይታወካሉም፤ እናንተም ኃጥኣን ለዘለዓለም የተረገማችሁ ናችሁ፥ ሰላምም የላችሁም። 17እናንተ የጻድቃን ነፍሳት፥ አትፍሩ፤ እናንተም በእውነት የሞታችሁ፥ ተስፋ አድርጉ። 18ነፍሳችሁ በታላቅ መከራና ጩኸት፥ በልቅሶና ኀዘን ወደ ሲኦል ስለ ወረደች አትዘኑ። 19ሥጋችሁም በሕይወታችሁ እንደ ቸርነታችሁ አላገኘም፤ ነገር ግን ጊዜው ኃጥኣን የተባላችሁበት ነበር፥ የመርገምና የመከራም ጊዜ ነበር። 20በምትሞቱበትም ጊዜ ኃጥኣን በእናንተ ላይ እንዲህ ይላሉ- “ጻድቃን እኛ እንደ ሞትን ሞቱ፥ በሥራቸውስ ጥቅማቸው ምንድን ነው? 21እነሆ፥ በኀዘንና በመከራ እንደ እኛ ሞቱ፥ ከእኛስ ብልጫቸው ምንድን ነው? ከዛሬም ጀምሮ ተካከልን፥ ምንስ ያገኛሉ? ለዘለዓለምስ ምን ያያሉ? እነሆ፥ እነርሱ ሞተዋልና፥ ከዛሬም ጀምሮ ለዘለዓለም ብርሃንን አያዩምና።” 22እናንተ ኃጥኣን፥ እንዲህ እላችኋለሁ- “መብልና መጠጥ ቅሚያና ኀጢአት፥ ሰውን መግፈፍና ገንዘብ ማጠራቀም፥ ደግ ዘመን ማየትም በቃችሁ። 23ፍጻሜያቸው እንዴት ሰላም እንደ ሆነ ጻድቃንን አያችኋቸውን? እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ ግፍ ሁሉ በእነርሱ ላይ አልተገኘምና። 24ጠፉ፤ ተፈጥረውም እንዳልተፈጠሩ ሆኑ፥ ሰውነቶቻቸውም በመከራ ወደ መቃብር ወረዱ።”