1ጻድቃን፥ በእነዚያ ወራቶች ለመታሰቢያ ጸሎታችሁን ትቀበሉ ዘንድ ተዘጋጁ። 2ኃጥኣን በልዑል ፊት ኀጢአትን ለመታሰቢያ እንደሚያኖሩት እናንተም በመላእክት ፊት ምስክሮች አድርጋችሁ አኑሯቸው። 3በእነዚያም ወራቶች አሕዛብ ይታወካሉ ፥ በጥፋትም ቀን የአሕዛብ ዘመዶች ይነሣሉ። 4በእነዚያም ወራቶች የተቸገሩ ይወጣሉ፤ ልጆቻቸውንም ይነጥቃሉ፥ ልጆቻቸውንም ይጥሏቸዋል። 5ከእነርሱም ልጆቻቸውን ያስወርዳሉ፤ እየጠቡም ሳሉ ልጆቻቸውን ይጥሏቸዋል። 6ወደ እነርሱም አይመለሱም፥ ለሚወዷቸውም አይራሩላቸውም። 7ዳግመኛም ለእናንተ ለኃጥኣን እኔ እምልላችኋለሁ፥ የማይገታ ደም ለሚፈስባት ቀን ኀጢአት ተዘጋጅታለችና። 8ለድንጋይም ይሰግዳሉ፥ የወርቁንና የብሩን፥ የእንጨቱንና የሸክላውን ምስልም ይሠራሉ። 9ለረከሱ መናፍስትና ለክፉዎች አጋንንት፥ ለጣዖቱም ሁሉ፥ ለመስገጃውም ሁሉ ይሰግዳሉ። 10ከእነርሱም ረድኤት ሁሉ አይገኝም፤ ስለ ልቡናቸውም ድንቍርና ይዘነጋሉ፥ በልቡናቸው ፍርሀትም ዐይኖቻቸው ይጋረዳሉ። 11ሕልማቸውንም በማየት ይረሳሉ፥ ይፈራሉም፤ ሥራቸውን ሁሉ በሐሰት ሠርተዋልና፥ ለድንጋዩም ሰግደዋልና፥ ፈጥነውም ይጠፋሉና። 12በእነዚያም ወራቶች የጥበብን ነገር የሚቀበሉና የሚያውቋት ሁሉ ብፁዓን ናቸው። 13የልዑልንም ሥራዎች ይሠሯቸዋል፥ በጽድቅም መንገድ ይሄዳሉ። እነርሱ ይድናሉና ከሚዘነጉ ሰዎች ጋር አይዘነጉም። 14ለወንድማችሁ ክፉውን የምትዘረጉ ወዮላችሁ! በሲኦል ትጠፋላችሁና። 15የኀጢአትንና የተንኰልን መሠረት የምትሠሩ፥ በምድርም ላይ የምታሳዝኑ ወዮላችሁ! በእርሱ ትጠፋላችሁና። 16በባዕድ ገንዘብ ቤታችሁን የምትሠሩ ወዮላችሁ! ሥራቸውም ሁሉ ጡብ ነው፥ የኀጢአትም ድንጋይ ነው፤ ሰላም እንደሌላችሁም እኔ እነግራችኋለሁ። 17ለዘለዓለም የሚኖር የአባቶቻቸውን ድንበርና ርስት ለሚያፈርሱ ወዮላቸው! ለእነርሱም ዕረፍት አይደረግላቸውምና ልቡናቸውን ወደ ጣዖቱ ይወስዱታል። 18ዐመፅን የምትሠሯትና ግፍን የምትረዷት፥ እስከ ታላቋ የፍርድ ቀንም ድረስ ባልንጀሮቻችሁን የምትገድሉ፥ ወዮላችሁ! ክብራችሁን ይጥላልና፤ በልቡናችሁም ክፋትን ይጨምራልና። 19ሁላችሁንም በሰይፍ ያጠፋችሁ ዘንድ የቍጣውን መንፈስ ያስነሣል፥ ቅዱሳንና ጻድቃን ሁሉም ኀጢአታችሁን ያስባሉ። 20በእነዚያም ወራቶች አባቶች ከልጆቻቸው ጋር በአንድ ቦታ ይገደላሉ፤ 21ወንድሞች ከወንድሞቻቸው ጋር ደማቸው እንደ ፈሳሽ ውኃ እስኪፈስስ ድረስ በሞት ይወድቃሉ። ሰው ከልጁና ከልጅ ልጁ ይገድለው ዘንድ በመራራት እጁን አይከለክልምና። 22ኀጢአተኛውም ከከበረ ወንድሙ እጁን አይከለክልም፥ ከንጋትም ጀምሮ ፀሐይ እስኪገባ ድረስ ይዋጋሉ። 23ፈረስም በኃጥኣን ደም ውስጥ እስከ እምቢያጕሱ ድረስ ይሄዳል፥ ሠረገላም እስከ ራሷ ድረስ ትሰጥማለች። 24በእነዚያም ወራቶች መላእክት ወደሚሰወሩበት ቦታ ይወርዳሉ። 25ኀጢአትን የሚረዷትንም ሁሉ ወደ አንድ ቦታ ይመልሷቸዋል። 26ልዑልም በኃጥኣን ሁሉ ታላቅ ፍርድ ይፈርድ ዘንድ በዚያች ቀን ይነሣል። 27ከቅዱሳን መላእክትም በቅዱሳንና በጻድቃን ላይ ጠባቂዎችን ይሰጣል፥ እነርሱም ክፋት ሁሉ፥ ኀጢአትም ሁሉ ጨርሶ እስኪጠፋ ድረስ እንደ ዐይን ብሌን ይጠብቋቸዋል። 28ጻድቃን ረዥም እንቅልፍን ቢተኙም የሚፈሩት ነገር የላቸውም። 29ጠቢባን እውነተኛ ነገርን ያያሉ፤ የዚህ ዓለም ልጆችም የዚችን መጽሐፍ ነገር ሁሉ ያስተውላሉ፥ ባለጸግነታቸውም በኀጢአታቸው በሚወድቁበት ጊዜ ሊያድናቸው እንደማይችል ያውቃሉ። 30ኃጥኣን፥ በጽኑ መከራ ቀን ጻድቃንን በምታስጨንቋቸው ጊዜ ወዮላችሁ! በእሳትም ታቃጥሏቸዋላችሁ፥ እናንተም እንደ ሥራችሁ ፍዳውን ትቀበላላችሁ። 31ክፉውን ነገር ልብ ታደርጉ ዘንድ የምትተጉ ልበ ግልብጦች ወዮላችሁ! ፍራትም ያገኛችሁ ዘንድ አላችሁ፥ የሚረዳችሁም የለም። 32ኃጥኣን፥ ወዮላችሁ! በአፋችሁ ነገር ላይና ሥራን በዘነጋችሁባቸው በእጆቻችሁ ሥራ ላይ በእሳት ወላፈን ትቃጠላላችሁና። 33አሁንም ዕወቁ፥ መላእክት በሰማይ ከፀሐይና ከጨረቃ፥ ከከዋክብትም የተነሣ ስለ ኀጢአታችሁ ሥራችሁን ይመራመራሉና። 34በምድር ላይ በጻድቃን ዘንድ ፍርድን ታደርጉባቸዋላችሁና ደመናውንና ጉሙን ሁሉ፥ ጠሉንና ዝናቡንም በእናንተ ያዳኝባችኋል፤ ወደ እናንተ እንዳይወርዱ ሁሉ ከእናንተ ይከለከላሉና፥ በኀጢአታችሁም አያስቡምና። 35አሁንም ዝናብ ወደ እናንተ መውረድን እንዳይከለከል፥ ጠልም ከእናንተ ወርቅንና ብርን ተቀብሎ እንዲወርድ ለዝናም እጅ መንሻን ስጡ። 36ውርጭና ዐመዳይ፥ የእነርሱም ቅዝቃዜ፥ የዐመዳይ ነፋሳትም ሁሉ፥ የእነርሱም ጭንቅ ሁሉ ቢወድቁባችሁ በእነዚያ ወራቶች በፊታቸው መቆም አይቻላችሁም።