1ጻድቃን፥ እመኑ፤ ኃጥኣን ለስድብ ይሆናሉና፥ በዐመፅም ቀን ይጠፋሉና። 2ልዑል የእናንተን ጥፋት ያስባልና፥ መላእክትም በሰማይ በእናንተ ጥፋት ላይ ደስ ይላቸዋልና ይህ የታወቀ ይሆንላችኋል። 3ኃጥኣን፥ ምን ታደርጉ ዘንድ አላችሁ? የጻድቃን የጸሎታቸውን ቃል በምትሰሙበት ጊዜ በዚያች የፍርድ ቀን ወዴት ትሸሻላችሁ? 4በእነዚያም ወራቶች የቅዱሳን ጸሎት ወደ እግዚአብሔር ትደርሳለች፥ በእናንተ ግን የቅጣታችሁ ወራት ይደርስባችኋል። 5የዐመፃችሁም ነገር ሁሉ በገናናውና በቅዱሱ ፊት ይነበባል፤ ፊታችሁም ያፍራል፤ በዐመፅ የጸና ሥራ ሁሉ ይጣላል። 6በባሕርና በየብስ መካከል ያላችሁ፥ ክፉ መታሰቢያችሁም በላያችሁ ያለባችሁ ኃጥኣን ወዮላችሁ! 7በእውነት ያይደለ ብርንና ወርቅን የምትሰበስቡ፥ ባለጸግነትን በለጸግን፤ ገንዘብም በዛልን፤ የወደድነውንም ሁሉ ገንዘብ አደረግን የምትሉ እናንተ፥ ወዮላችሁ! 8ብሩን ሰብስበን በሳጥኖቻችን መልተናልና፥ በቤታችንም ያሉ አራሾች እንደ ውኃ በዝተውልናልና አሁን ያሰብነውን እናድርግ የምትሉ እናንተ ወዮላችሁ! 9ሐሰታችሁ እንደ ውኃ ይፈስሳል፤ ባለጠግነታችሁ አይኖርላችሁምና፤ ነገር ግን ከእናንተ ፈጥኖ ይጠፋል። ሁሉን በዐመፅ ሰብስባችሁታልና። 10እናንተም ለታላቅ ርግማን ትሰጣላችሁ። 11ዛሬም እኔ ለብልሆችና ለሰነፎች እምልላችኋለሁ፤ በምድር ላይ ብዙ ነገርን ታያላችሁና። 12እናንተ ወንዶቹ ከሴቶች ይልቅ ጌጥን ታጌጣላችሁና፥ ይልቁንም ከድንግሊቱ ይልቅ ብዙ መልክ ያለውን ጌጥ ታደርጋላችሁና። 13በመንግሥትና በገናናነት፥ በሥልጣንም፥ በብርና በወርቅ፥ በነጭ ሐርም፥ በክብርም ታጌጣላችሁ። 14መብሎችም እንደ ውኃ ይፈስሳሉ፤ ስለዚህም ትምህርትና ጥበብ የላቸውም። 15በዚያም ከገንዘባቸውና ከጌትነታቸው፥ ከክብራቸውም ሁሉ ጋር አንድ ሆነው ይጠፋሉ። 16በስድብና በችጋር፥ በታላቅ በቀልም ነፍሳቸው ወደ እሳት ጕድጓድ ትወድቃለች። 17ኃጥኣን፥ ተራራው ወንድ ባሪያ እንዳልነበረ፥ እንግዲህም ወዲህ እንደማይሆን፥ ኮረብታም ለሴት ሴት ባሪያ እንዳይደለች ለእናንተ ማልሁላችሁ። 18እንደዚሁም ኀጢአት በምድር ላይ አልተላከችም፤ ነገር ግን ሰዎች ከራሳቸው ፈጠሩአት፤ እርሷንም የሠሯት ሰዎች ለታላቅ መርገም ይሆናሉ። 19ለሴትም ምክነት አልተሰጣትም፤ ነገር ግን በእጅዋ በሠራችው ሥራ ልጅ ሳትወልድ ትሞታለች። 20ኃጥኣን፥ በቅዱሱና በገናናው ማልሁላችሁ፤ ክፉ ሥራችሁ ሁሉ በሰማያት የተገለጠ ነውና፥ የተከደነና የተሰወረ የግፍ ሥራም የላችሁምና። 21በመንፈሳችሁ አታስመስሉ፤ በሰማይም በልዑል ፊት በየቀኑ ይጻፍ ዘንድ ያለውን ኀጢአታችሁን ሁሉ እንደማታውቁና እንደማታዩ በልቡናችሁ አትናገሩ። 22የምትሠሩትም ግፍ ሁሉ በየቀኑ እስከ ፍርዳችሁ ቀን ይጻፋልና ከዛሬ ጀምሮ ታውቃላችሁ። 23ሰነፎች፥ ወዮላችሁ! በስንፍናችሁ ትጠፋላችሁና፥ ጠቢባንንም አትሰሟቸውምና፥ በጎ ነገርም አታገኛችሁምና። 24አሁንም ለጥፋት ቀን የተዘጋጃችሁ እንደ ሆናችሁ ዕወቁ፥ ኃጥኣን ተፈርዶባችሁ ትሄዳላችሁ እንጂ እንድናለን ብላችሁ ተስፋ አታድርጉ። 25መድንን አታውቁምና ትሞታላችሁ። በነፍሳችሁ ለታላቅዋ የፍርድ ቀን፥ ለታላቅዋ የመከራና የጕስቍልና ቀንም ተዘጋጅታችኋልና። 26ክፉ ሥራን የምትሠሩ፥ ብርንዶንም የምትበሉ ልበ ደንዳኖች ወዮላችሁ! በልታችሁና ጠጥታችሁ የምትጠግቡትን መልካሙን ነገር ከየት አገኛችሁ? ልዑል እግዚአብሔር በምድር ላይ ካበዛው መልካም ሁሉ አይደለምን? ነገር ግን ሰላም የላችሁም። 27የዐመፅን ሥራ የምትወዷት ወዮላችሁ! በጎዋን ነገር ለእናንተ ለምን ተስፋ ታደርጋላችሁ? 28በጻድቃንም እጆች ተላልፋችሁ ትሰጡ ዘንድ እንዳላችሁ ዕወቁ፤ አንገቶቻችሁንም ቈርጠው ይገድሏችኋል፤ አይራሩላችሁምም። 29በጻድቃን መከራ ደስ የሚላችሁ ወዮላችሁ! ለእናንተ መቃብር አይቈፈርላችሁምና። 30የጻድቃንን ነገር የምትንቁ ወዮላችሁ! የሕይወት ተስፋ አይሆንላችሁምና። 31ሐሰት ነገርንና የዝንጉዎችን ነገር የምትጽፉ ወዮላችሁ! እነርሱ ስንፍናን እንዲሰሟትና እንዳይዘነጓት ሐሰታቸውን ይጽፋሉና። 32ሰላምም አይሆንላቸውም፤ ነገር ግን ሳይዘገዩ ፈጥነው ሞትን ይሞታሉ። 33ኀጢአትን የምትሠሩ፥ የሐሰትን ነገር የምታመሰግኑና የምታከብሩም ወዮላችሁ! በዚሁም ጠፋችሁ፤ ሕይወትና በጎ ነገርም የላችሁም። 34የቅን ፍርድ ነገሮችን የሚለዋውጡ ወዮላቸው! የዘለዓለም ሥርዐትንም ይለውጣሉ፤ ራሳቸውንም ኀጢአተኞች እንዳልሆኑ የሚያደርጉ በምድር ላይ ይረገጡ ዘንድ አላቸው።