1አሁንም ልጆቼ፥ እላችኋለሁ፤ ጽድቅን ውደዱአት፤ በእርሷም ሂዱ፤ የጽድቅ መንገዶችን ይቀበሏቸው ዘንድ ይገባልና፤ 2የዐመፅ መንገዶችም ፈጥነው ይጠፋሉ፤ ያንሳሉም፤ ለታወቁ ሰዎችም ከልጅ ልጅ ጀምሮ የዐመፅና የሞት መንገዶች ይገለጣሉ፤ ከእነርሱም ይርቃሉ፤ አይከተሏቸውምም። 3አሁንም ለእናንተ ለጻድቃን እላችኋለሁ፤ በክፉ መንገዶች አትሂዱ፤ በግፍዕና በሞት መንገድም አትሂዱ፤ እንዳትጠፉም ወደ እነርሱ አትቅረቡ፤ ነገር ግን የተመረጠች ጽድቅንና ሕይወትን ለእናንተ ፈልጉ፤ ምረጡም። 4በሰላም መንገዶችም ሂዱ፤ ትድናላችሁ፤ በተድላም ትኖራላችሁ፤ በልቡናችሁም ዐሳብ ትይዛላችሁ። 5ክፉ ጥበብን ይሠሩ ዘንድ ኃጥኣን ሰዎችን እንደሚፈትኗቸው አውቃለሁና ነገሬ ከልቡናቸሁ አይጥፋ፤ ቦታም ሁሉ አይገኝላትም፤ መከራም ሁሉ አይጐድልም። 6ዐመፅንና ግፍን ለሚያንጹ፥ ተንኰልንም ለሚሠሯት ሰዎች ወዮላቸው! እነርሱ ፈጥነው ይጠፋሉና፥ ሰላምም የላቸውምና። 7ቤታቸውን በኀጢአት ለሚሠሩ ሰዎች ወዮላቸው! ከመሠረታቸው ሁሉ ይጠፋሉና፥ በሰይፍም ይወድቃሉና፥ ወርቅንና ብርንም የሚሰበስቧት በፍርድ ፈጥነው ይጠፋሉና። 8እናንተ ባለጠጎች ወዮላችሁ! በባለጠግነታችሁ ላይ ታምናችኋልና፥ ከባለጠግነታችሁም ትለያላችሁና። 9በባለጠግነታችሁ ወራት ልዑልን አላሰባችሁትምና፥ እናንተስ ስድብን፥ በደልንም ሠራችኋት፤ ደም ለሚፈስባት ቀንና ለጨለማዋ ቀን፥ ለታላቅዋ ፍርድ ቀንም የተዘጋጃችሁ ሆናችኋል። 10የፈጠራችሁ እንደሚያጠፋችሁ፥ በውድቀታችሁም ላይ ይቅርታው እንደማይደረግላችሁ እኔ እንደዚህ ብዬ እነግራችኋለሁ። 11ፈጣሪያችሁም በጥፋታችሁ ደስ ይለዋል፤ የእናንተም ጻድቃን በእነዚያ ወራት ለዝንጉዎችና ለኃጥኣን መዘባበቻ ይሆናሉ። 12ዐይኖቼ ውኃን የቋጠሩ ደመናዎችን ይሆኑ ዘንድ፥ በእናንተም ላይ አለቅስ ዘንድ፥ ውኃንም እንደ ቋጠረ ደመና እንባዬን አፈስ ዘንድ፥ ከልቡናዬ ኀዘንም አርፍ ዘንድ ማን በሰጠኝ ነበር። 13ስድብንና ክፋትን ታደርጉ ዘንድ ማን ሰጣችሁ? እናንተን ኃጥኣንን ቍርጥ ፍርድ ያገኛችኋል። 14ጻድቃን ከኃጥኣን የተነሣ አትፍሩ፤ እንደ ወደዳችሁ በእነርሱ ላይ ፍርድን ታደርጉባቸው ዘንድ እግዚአብሔር ዳግመኛ በእጃችሁ ይጥላቸዋልና። 15እንዳትፈቱ ሆናችሁ ግዝትን ለምትገዝቱ ለእናንተ ወዮላችሁ! ስለ ኀጢአታችሁም ድኅነት ከእናንተ ራቀ። 16ለባልንጀራችሁ ክፉ ምላሽ ለምትመልሱ ለእናንተ ወዮላችሁ! እንደ ሥራችሁ መጠን ፍዳውን ትቀበላላችሁና። 17ሐሰት ለምትመሰክሩ፥ ለበደልም ለምትገቧት ለእናንተ ወዮላችሁ! ፈጥናችሁ ትጠፋላችሁና። 18እናንተ ኃጥኣን፥ ወዮላችሁ! ጻድቃንን ታሳድዱአቸዋላችሁና፥ እናንተም በእነርሱ እጅ ትወድቃላችሁና፥ ከዐመፅም የተነሣ ትሰደዳላችሁና፥ የእነርሱም ቀንበር በእናንተ ይጸናልና። 19ጻድቃን፥ ይህን ተስፋ አድርጉ፤ ኃጥኣን ከፊታችሁ ፈጥነው ይጠፋሉና፥ እንደ ወደዳችሁም ሥልጣን በእነርሱ ላይ ይሆንላችኋልና። 20ኃጥኣንም መከራ በሚቀበሉበት ቀን የእናንተ ልጆች እንደ አሞሮች ከፍ ከፍ ይላሉ፤ ይነሣሉ። 21ማረፊያችሁም ከጥንብ አሞራ ቦታ ይልቅ ይርቃል፤ ወጥታችሁም ከዐመፀኞች ፊት የተነሣ ወደ ጕድጓድና ወደ ዐለቱ ንቃቃት እንደ ሽኮኮ ለዘለዓለም ትገባላችሁ። 22በእናንተም ላይ ይጮኻሉ፤ ይህ ኀጢአታችሁ በእናንተ ምስክር ይሆንባችኋል እንጂ እናንተ እንደ እነርሱ አትሆኑም፤ ከኃጥኣንም ጋር አንድ ሆናችሁ፤ እንደ ሄለይም ያለቅሳሉ። 23መከራን የምትቀበሉ እናንተ ግን አትፍሩ፤ ድኅነት ይሆንላችኋልና፥ የበራ ብርሃንም ለእናንተ ያበራላችኋልና፥ ከሰማይም የዕረፍት ቃልን ትሰማላችሁና። 24ኃጥኣን ወዮላችሁ! ባለጸግነታችሁ ጻድቃንን ያስመስላችኋልና፥ ልቡናችሁም ኃጥኣን እንደ ሆናችሁ ይዘልፋችኋልና። 25ይህም ነገር ለክፋታችሁ መታሰቢያ በእናንተ ላይ ምስክር ይሆናል። 26የስንዴውን ፍሬ የምትበሉ፥ ከምንጩም መነሻ ኀይልን የምትጠጡ፥ የተዋረዱትንም በኀይላችሁ የምትረጋግጧቸው ወዮላችሁ! 27ሁልጊዜ ውኃን የምትጠጡ ወዮላችሁ! ፍዳን ፈጥናችሁ ትቀበላላችሁና፥ የሕይወትንም ምንጭ ትታችኋልና ፈጽማችሁ ትጠፋላቸሁ። 28ዐመፅንና ሽንገላን፥ ፅርፈትንም የምትሠሩ ወዮላችሁ! ይህም በእናንተ ላይ ለክፋት መታሰቢያ ይሆናል። 29ጻድቁን በኀይል የምትቀጠቅጡት ኀያላን ወዮላችሁ! የጥፋታችሁ ቀን ትመጣለችና። 30በእነዚያም ወራቶች በፍርዳችሁ ቀን ብዙዎችና ደጎች ወራቶች ለጻድቃን ይመጣሉ።