1“ከዚህም በኋላ ሁለተኛዋ ጽድቅ የሚደረግባት ስምንተኛዪቱ ሱባዔ ትደረጋለች፤ ከግፈኞች የተነሣም የእውነት ፍርድ ይደረግባት ዘንድ ለእርስዋ ሰይፍ ይሰጣል፤ ኃጥኣንም በጻድቃን እጅ ይሰጣሉ። 2በመጨረሻዋም ከጽድቃቸው የተነሣ ንብረት ያደርጋሉ፥ ለገናናው ንጉሥም እስከ ዘለዓለም ሊመሰገንበት ቤት ይሠራል። 3“ከዚህም በኋላ በዘጠነኛዪቱ ሱባዔ ለዓለም ሁሉ የእውነት ፍርድ ትገለጣለች። 4የዝንጉዎችም ሥራ ሁሉ ከምድር ይጠፋል፤ ዓለምም ለጥፋት ይቈጠራል፤ ሰዎችም ሁሉ የቀናች መንገድን ይመለከታሉ። 5“ከዚህም በኋላ በዐሥረኛዪቱ ሱባዔ በሰባተኛው ክፍል የዘለዓለም ፍርድ ትደረግባታለች። 6ከመላእክት ሁሉ መካከል የሚወጣ ታላቅ ፍርድም በዘለዓለማዊው ሰማይ ከትጉሃን መላእክት ይደረጋል። 7የቀደመውም ሰማይ ፈጽሞ ያልፋል፤ አዲሱ ሰማይም ይገለጣል። የሰማይ ሠራዊትም ሁሉ ሰባት እጥፍ ለዘለዓለም ያበራሉ። 8ከዚህም በኋላ ቍጥር የሌላቸው ብዙ ሱባዔዎች በቸርነቱና በይቅርታው ለዘለዓለም ይሆናሉ፤ ከዚያም በኋላ ኀጢአት እስከ ዘለዓለም ትሠራለች አትባልም። 9“አሁንም ልጆቼ፥ እነግራችኋለሁ፤ የጽድቅ መንገዶችንና የግፍ መንገዶችንም አሳያችኋለሁ። 10ዳግመኛም የሚመጣውን ታውቁ ዘንድ አሳያችኋለሁ፤ አሁንም ልጆቼ፥ ስሙኝ፤ በጽድቅ መንገዶችም ሂዱ። 11በዐመፅ መንገድ የሚሄዱ ሁሉ ለዘለዓለም ይጠፋሉና በግፍ መንገዶች አትሂዱ።” 12ከሰው ሁሉ ክቡር፥ የምድርም ሁሉ መምህር ከሆነው፥ የጥበብን ትምህርት ሁሉ ከጻፈው ከሄኖክ የተጻፈ መጽሐፍ፥ 13በምድር ለሚኖሩ ለልጆቼ ሁሉ፥ ፍርድንና ሰላምን ለሚያደርጉ ለኋላ ልጆችም፥ 14ቅዱሱና ገናናው ለሁሉ ቀኖችን ሰጥትWaልና መንፈሳችሁ በዘመናት አትዘን። 15ጻድቅ ሰው ከእንቅልፉ ይነሣል፤ በጽድቅ መንገዶችም ይሄዳል። 16መንገዱም፥ አኗኗሩም ሁሉ በቸርነትና በዘለዓለማዊ ይቅርታ ነው፤ ጻድቁን ይቅር ይለዋል፤ ለእርሱም ለዘለዓለሙ ቅንነትን ይሰጠዋል፤ ሥልጣንንም ይሰጠዋል። 17በቸርነትና በጽድቅ ጸንቶ ይኖራል፤ ብርሃንም ለዘለዓለም ይኖራል፤ ኀጢአትም በጨለማ እስከ ዘለዓለም ትጠፋለች፤ ከእንግዲህ ወዲያም ከዚያች ቀን ጀምሮ እስከ ዘለዓለም አትታይም። 18ከዚህም በኋላ እንዲህ ሆነ፥ ሄኖክ ከመጻሕፍት ይናገር ጀመረ። 19ሄኖክ ስለ ልጆችና ስለ ዓለም ምርጦች፥ ስለ ጽድቅና ስለ ቅን ፍርድ ተክልም እንዲህ አለ- “ልጆቼ፥ እነዚህን ነገሮች እነግራችኋለሁ፤ አስረዳችኋለሁም። 20ከሰማይ የታየኝን ራእይ፥ ከቅዱሳን መላእክት ቃልም ያወቅሁትንና በሰማይ ሰሌዳ ላይ ያስተዋልሁትን እነግራችኋለሁ። 21ሄኖክም ከመጻሕፍት ይናገር ጀመረ፥ እኔ ሰባተኛው ትውልድ በመጀመሪያቱ ሱባዔ ተወለድሁ። 22ፍርድና እውነት እስኪደረጉ ድረስ ጌታ ታገሠ፤ ከእኔም በኋላ በሁለተኛዪቱ ሱባዔ ታላቅ ኀጢአት ትሠራለች። 23ተንኰልም ጸናች፤ በእርሷም የመጀመሪያዪቱ መጨረሻ ትደረጋለች። 24ሰውም በእርስዋ ይድናል፤ እርሱም ከተጨረሰ በኋላ ዐመፅ ታድጋለች፤ እርሱም ለኀጥኣን ሥርዐትን ያደርጋል። 25ከዚህም በኋላ በሦስተኛዪቱ ሱባዔ በመጨረሻዋ ሰው ለእውነተኛ ፍርድ ተክል ይመረጣል፤ ከእርሱም በኋላ የዘለዓለም ጽድቅና ርትዕ ተክል ይወጣል። 26ከዚህም በኋላ በአራተኛዪቱ ሱባዔ በመጨረሻዋ የቅዱሳንና የጻድቃን ራእያት ይገለጣሉ። ሥርዐትና ቅጥርም ለልጅ ልጅ ዘመን ይሠራላቸዋል። 27ከዚህም በኋላ በአምስተኛዪቱ ሱባዔ በመጨረሻዋ የምስጋናና የመንግሥት ቤት እስከ ዘለዓለም ይሠራል። 28ከዚህም በኋላ በስድስተኛዪቱ ሱባዔ በእርሷ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ደንቆሮዎች ናቸው፤ የሁሉም ልቡናቸው ከጥበብ ይለያል፤ በእርሷም ሰው ያርጋል። 29በመጨረሻዋም ቤተ መንግሥቱ በእሳት ይቃጠላል፤ የተመረጠው የመንግሥት ወገን ሁሉም በእርሷ ይበተናሉ። 30ከዚህም በኋላ በሰባተኛዪቱ ሱባዔ ወንጀለኛዋና ሥራዋ ብዙ የሆነ ትውልድ ትነሣለች፤ ሥራዋም ሁሉ ወንጀል ነው። 31በመጨረሻዋም ለፍጥረቱ ሁሉ ሰባት ዕጥፍ ትምህርት የሚሰጣቸው የተመረጡ ጻድቃን ከዘለዓለም የጽድቅ ተክል ይመረጣሉ። 32ከሰው ልጆች ሁሉ የቅዱሱን ቃል መስማት የሚችልና የማይታወክ ማን ነው? አሳቡንስ ያስብ ዘንድ የሚችል ማን ነው? 33ሰማይንና ሥራዋንም ሁሉ ቀና ብሎ ማየት የሚችል ማን ነው? 34የሰማይንስ ሥራ ማወቅ የሚቻለው ማን ነው? ነፍሱን ያይ ዘንድ፥ ያም ባይሆን መንፈሱ ያይና ይናገር ዘንድ፥ ያም ባይሆን ወደ ላይ ይወጣና ክንፎቻቸውን ሁሉ ያይና ያስባቸው ዘንድ፥ ያም ባይሆን እንደ እነርሱ ያደርግ ዘንድ የሚቻለው ማን ነው? 35የምድር ወርዷና ርዝመትWa ምን እንደ ሆነ ማወቅ የሚችል ሰው ሁሉ ማን ነው? 36የእነዚህ ሁሉ ልካቸው ለማን ተገለጠ? የሰማይም ምጥቀትWaና ርዝመትWa ምን እንደ ሆነ፥ የጸናችም በምን ላይ እንደ ሆነ ማወቅ የሚችል፥ የኮከቦችም ቍጥራቸው ምን ያህል እንደ ሆነ፥ ብርሃናትም ሁሉ በየት እንደሚያርፉ ማወቅ የሚቻለው ሰው ሁሉ ቢኖር በእርሱ ነው።