1ባማረችው ምድር ዙፋን እስኪሠራ ድረስ አየሁ፤ የበጎችም ጌታ በእርሱ ላይ ተቀመጠ። 2የታጠፉትንም መጣፎች ሁሉ አነሣ፤ እነዚያንም መጣፎች በበጎች ጌታ ፊት ገለጣቸው። 3እነዚያንም የቀደሙትን ሰባቱን ነጮች ጠራቸው፤ ኀፍረታቸው እንደ ፈረስ ኀፍረት ከሆነ ከእነዚያ ከዋክብት ከሚቀድም ከመጀመሪያው ኮከብ ወደ እርሱ ያመጡ ዘንድ አዘዘ። 4አስቀድሞ የወደቀውን መጀመሪያውንም ኮከብ፥ ሁሉ ወደ እርሱ አመጧቸው። 5ከሰባቱ ነጮች አንዱ የሆነውን በፊቱ የሚጽፈውንም ያን ሰው እንዲህ አለው- 6“በጎችን የሰጠኋቸውን፥ ተቀብለውም ካዘዝኋቸው ወጥተው ብዙዎችን ያጠፉትን እነዚህን ሰባውን እረኞች አግዛቸው።” 7እነሆ ሁሉንም ታስረው አየኋቸው፤ ሁሉም በፊቱ ቆመው ነበር፤ ፍርድም አስቀድሞ ከከዋክብት ተጀመረ፤ ተወቀሱ፤ ኀጢአተኞችም ሆነው ተገኙ፤ ወደ ቅጣት ቦታም ሄዱ። 8ወደ ጥልቁም ጣሏቸው፤ ያም ቦታ የሚያላልብ፥ እሳትንና የእሳት ምሰሶን የተመላ ነው። 9እነዚያም ሰባው እረኞች ለፍርድ ቀረቡ፤ ኀጢአተኞችም ሆኑ፤ እነርሱም ወደዚያ የእሳት ጕድጓድ ተጣሉ። 10ያንጊዜም እንደዚሁ እሳትን የተመላ አንድ ጕድጓድ በምድር መካከል እንደ ተከፈተ አየሁ። 11የታወሩ እነዚያን በጎችም አመጧቸው። ለፍርድ ቀረቡ፤ ኀጢአተኞችም ሆነው ተገኙ፤ ወደዚያ ወደ እሳቱ ጕድጓድም ተጣሉ፤ ተቃጠሉም። 12ያም ጕድጓድ በዚያ ቤት በስተቀኝ ነበር፤ እነዚያንም በጎች ሲቃጠሉ፥ አጥንቶቻቸውም ሲቃጠሉ አየሁ። 13ያን ያረጀውንም ቤት እስኪጠቀልለው አይ ዘንድ ቆምኹ፤ ምሰሶዎችንም ሁሉ አወጧቸው። 14የዚያም ቤት ተክሉና ጌጡ ሁሉ ከእርሱ ጋር ተጠቀለለ፤ አውጥተውም በምድር ቀኝ ባለ በአንድ ቦታ ጣሉት። 15የበጎች ጌታም ከዚያ ከቀደመው ቤት ታላቅና ከፍ ያለ አዲስ ቤትን እስኪያመጣ ድረስ አየሁ፤ ያንም አስቀድማ በተጠቀለለችው ቤት ቦታ አቆመው። 16ምሰሶዎችዋም ሁሉ አዲሶች ናቸው፤ ጌጧም ሁሉ አዲስ ነው፤ ካፈረሳት ካረጀችው ከመጀመሪያዪቱም ቤት ይልቅ ታላቅ ነው፤ በጎችም ሁሉ በመካከሏ ናቸው። 17የቀሩትንም በጎች ሁሉና በምድር ላይ ያሉ እንስሳትን ሁሉ፥ የሰማይ ወፎችንም ሁሉ፥ 18ለእነዚያ በጎች ሲወድቁና ሲሰግዱ፥ ሲማልዷቸውና ቃላቸውንም ሁሉ ሲሰሟቸው አየኋቸው። 19ከዚያም በኋላ ነጫጭ ልብስ የለበሱና አስቀድመው ወደ ሰማይ ያወጡኝ እነዚያ ሦስቱ እጄን ያዙኝ። 20የዚያም አውራ እጅ ይዛኝ ሳለች አወጡኝ፤ ፍርድም ሳትደረግ በእነዚያ በጎች መካከል አኖሩኝ። 21እነዚያም በጎች ሁሉ ነጫጭ ሆኑ፤ ፀጕራቸውም ታላቅና ንጹሕ ነበር። 22የጠፉና የተበተኑ ሁሉ፥ የዱር አራዊት ሁሉና የሰማይ ወፎችም ሁሉ በዚያ ቤት ተሰበሰቡ። 23ሁሉም ደጋግ ሁነዋልና፥ ወደ ማደሪያውም ተመልሰዋልና የበጎች ጌታ እጅግ ደስ አለው። 24ለበጎችም የተሰጣቸውን ያን ሰይፍ እስኪያጋድሙት ድረስ አየሁ፤ ወደ ቤቱም መለሱት፤ በጌታም ፊት አተሙት። 25በጎችም ሁሉ በዚያ ቤት ተዘጋባቸው፤ ነገር ግን አልቻላቸውም፤ የሁሉም ዐይኖቻቸው ተገልጠው በጎውን ይመለከቱ ነበር፤ ከእነርሱም በመካከላቸው የማያይ አንድ እንኳ አልነበረም። 26ያም ቤት ታላቅና ሰፊ እንደ ሆነ አየሁ፤ ፈጽሞም ሙሉ ነበር። አንድ ነጭ ላምም ተወልዶ አየሁ፤ ቀንዶቹም ታላላቆች ነበሩ። 27የዱር አራዊትና የሰማይ ወፎችም ሁሉ ፈርተው በየጊዜው ይማልዱታል። 28ዘመዶቻቸውም ሁሉ እስኪለወጡ ድረስ አየሁ፤ ላሞችም ሁሉ ነጫጭ ሆኑ። 29በመጀመሪያም ነገር በመካከላቸው ሆነ፤ ያም ነገር ታላቅ አውሬ ሆነ፤ በራሱም ላይ ታላላቅና ጥቋቍር ቀንዶች አሉ። 30የበጎችም ጌታ በእነርሱና በላሞች ሁሉ ደስ አለው። 31እኔም በመካከላቸው ተኝቼ ነቃሁ፤ ሁሉንም አየሁ፤ ተኝቼም ያየሁት ራእይ ይህ ነው፤ ነቅቼም የጽድቅ ጌታን አመሰገንሁት፤ ለእርሱም ምስጋናን አቀረብሁለት። 32ከእርሱም የተነሣ ታላቅ ልቅሶን አለቀስኹ፤ ወደዚያም ወደ አየሁት ሲወርዱ ባየሁ ጊዜ መታገሥን አልቻልሁምና እንባዬ አልተገታም። 33ሁሉ መጥቶ ይጨረሳልና፥ የሰውም ሁሉ ሥራ በየወገኑ ተገለጠልኝ። 34በዚያችም ሌሊት የቀደመውን ሕልሜን አሰብሁት፤ ያን ራእይ አይቻለሁና ስለ እርሱ ነገር አለቀስሁ፤ ታወክሁም። 35አሁንም ልጄ፥ ማቱሳላ! ወንድሞችህን ሁሉ ጥራልኝ፤ የእናትህንም ልጆች ሁሉ ሰብስብልኝ፤ ቃል ጠርቶኛልና። 36እስከ ዘለዓለምም የሚደርስባችሁን እገልጥላችሁ ዘንድ መንፈስ በእኔ ላይ አድሮአልና። 37ከዚያም በኋላ ማቱሳላ ሄዶ ወንድሞቹን ሁሉ ወደ እርሱ ጠራቸው፤ ዘመዶቹንም ሰበሰባቸው፤ ለልጆቹም ሁሉ እውነት ነገርን ነገራቸው። 38እንዲህም አለ- “ልጆቼ፥ የአባታችሁን ነገር ሁሉ ስሙ፤ ወዳጆቼ፥ በእናንተ አዳኝባችኋለሁና፥ እነግራችኋለሁምና የአፌን ቃል በቅንነት አድምጡ። 39ሕግንም ውደዷት፤ በእርሷም ሂዱ፤ ሁለት ልብም ሆናችሁ ወደ ሕግ አትቅረቡ፤ ልጆቼ፥ በእውነት ኑሩ እንጂ ሁለት ልብ ሆነው ከሚኖሩ ሰዎች ጋር አትተባበሩ። 40እርስዋም በመልካም ጐዳና ትመራችኋለች፤ በምድር ላይ የግፍ አካል እንዲጸና አውቃለሁና ጽድቅ ለእናንተ ኅብረት ይሆናል። 41በምድርም ላይ ታላቅ መቅሠፍት ይፈጸማል፤ ዐመፅም ሁላ ትጨረሳለች፤ ከሥርዋም ትቈረጣለች። 42ሕንጻውም ሁሉ ያልፋል፤ ዐመፅም ትደገማለች፤ በምድርም ላይ ትፈጸማለች፤ የዐመፅና የግፍ፥ የበደልም ሥራ ሁሉ እጥፍ ሆና ትሠራለች። 43ዐመፅና ኀጢአት፥ ስድብና ግፍ፥ ክፉውም ሥራ ሁሉ በበዛ ጊዜ፥ በደልና ወንጀል፥ ርኵሰትም በበዛ ጊዜ ታላቅ መቅሠፍት ከሰማይ በእነዚህ ሁሉ ላይ ይደረጋል። 44ቅዱስ እግዚአብሔርም በምድር ላይ ፍርድን ያደርግ ዘንድ በመቅሠፍትና በመዓት ይመጣል። 45በእነዚያም ወራቶች ግፍ ከሥርዋ ትቈረጣለች፤ የዐመፅም ሥሮች ከሽንገላ ጋር ይቈረጣሉ፤ ከሰማይም በታች ይጠፋሉ። 46ሁሉም ከአሕዛብ ጋር ይሰጣል፤ አዳራሾችም በእሳት ይቃጠላሉ፤ ከምድርም ሁሉ ያወጧቸዋል፤ በገሃነመ እሳትም ይጣላሉ። በመዓትና በዘለዓለማዊ ኀይለኛ ፍርድ ይጠፋሉ። 47ጻድቁ ከእንቅልፉ ይነሣል፤ ጥበብም ይነሣል፤ ለእነርሱም ይሰጣል፤ ከእርሱም የተነሣ የዐመፅ ሥሮች ይቈረጣሉ። 48ኃጥኣንም በሰይፍ ይጠፋሉ፤ ተሳዳቢዎችም በቦታው ሁሉ ይቈረጣሉ። 49ግፍን የሚያስቧትና ስድብንም የሚሠሯት በሰይፍ ይጠፋሉ።