1ሰባውን እረኞች ጠራ፤ ይጠብቋቸውም ዘንድ እነዚያን በጎች ሰጣቸው። 2ለእረኞችና ለአገልጋዮቻቸውም እንዲህ አላቸው- “ከእናንተ እያንዳንዱ ሁሉ ከዛሬ ጀምሮ በጎችን ይጠብቋቸው፤ እኔም የማዝዛችሁን ሁሉ አድርጉ። 3እኔም በቍጥር እሰጣችኋለሁ፤ ከእነርሱም የሚጠፋውን እኔ እነግራችኋለሁ፤ እነርሱንም አጥፉ፥” እነዚያንም በጎች ሰጣቸው። 4ሌላውንም ጠርቶ እንዲህ አለው- “ካዘዝኋቸው ወጥተው ከእነርሱ ውስጥ ያጠፋሉና በእነዚህ በጎች ላይ እረኞች የሚያደርጉትን ሁሉ አስተውል፤ ተመልከትም። 5በእኔ ትእዛዝ ምን ያህል እንደሚያጠፉ፥ በራሳቸውም ምን ያህል እንደሚያጠፉ በእረኞች የሚደረገውን ጥጋብና ጥፋት ሁሉ ጻፍ። 6የእያንዳንዳቸውንም እረኞች ጥፋት ሁሉ በእነርሱ ላይ ጻፍ። በፊቴም በቍጥር አንብብ፤ ምን ያህልም ያጠፏቸው እንደ ሆነ፥ ምን ያህልም ለጥፋት ይሰጧቸው እንደ ሆነ፥ 7የእረኞችን ሥራ ሁሉ እንዳውቅ ይህ ምስክር ይሆነኝ ዘንድ፥ 8ባዘዝኋቸውም ትእዛዝ ጸንተው ይኖሩ፥ ወይም አይኖሩ እንደ ሆነ የሚያደርጉትን አይቼ እሰጣቸው ዘንድ፥ 9እነርሱ አይወቁ፤ አንተም አታሳያቸው፤ አትዝለፋቸውም፤ ነገር ግን በየጊዜው እያንዳንዳቸው የሚያጠፉትን የእረኞችን ጥፋት ጻፍ። ሁሉንም ወደ እኔ አምጣ። 10እነዚያም እረኞች በየጊዜው እስኪጠብቋቸው ድረስ አየሁ፤ ከታዘዙትም ወጥተው ብዙ ይገድሉና ያጠፉ ጀመሩ። 11እነዚያንም በጎች በአንበሶች እጅ ጣሏቸው፤ አንበሶችና ነብሮችም ከእነዚያ በጎች አብዛኛዎችን በልተው ዋጧቸው። 12የዱር እሪያዎችም ከእነርሱ ጋር በሉ፤ ያን ግንብም አቃጠሉት፤ ያንም የበጎች ቤት ቈፈሩት። 13እኔም ያ የበጎች ቤት ተቈፍሯልና ስለ ግንቡ እጅግ ብዙ አዘንሁ። 14ከዚያም በኋላ ወደዚያ ቤት ይገቡ እንደ ሆነ፥ ወይም አይገቡ እንደ ሆነ እነዚያን በጎች ማየት አልተቻለኝም። 15እረኞቻቸውና አገልጋዮቻቸውም በጎቹን ይበሏቸው ዘንድ ለዱር አራዊት ሁሉ አሳልፈው ሰጧቸው። 16ከእነርሱም እያንዳንዱ ሁሉ በየጊዜው በቍጥር ይቀበላል፤ ከእነርሱም እያንዳንዱ የሚያጠፋው ምን ያህል እንደ ሆነ ለሁለተኛው በመጽሐፍ ይጽፍለታል፤ ይልቁንም ከሥርዐታቸው ወጥተው እያንዳንዱ ይገድላል፤ ያጠፋልም። 17እኔም ስለ እነዚያ በጎች ብዙ ጊዜ አለቅስና እጮህ ጀመርሁ። 18እንደዚህም በየቀኑ ከእነዚያ እረኞች ለሚያጠፋው ለአንዱ እንዴት እንደሚጽፍለት ያን የሚጽፍለትን በራእይ አየሁ። 19አውጥቶም ያሳርፈዋል፤ ለበጎችም ጌታ መጽሐፉን ሁሉና የሚሠሩትን ሥራ ሁሉ፥ ከእነርሱም እያንዳንዳቸው ያሰወገዱትንና ለጥፋት አሳልፈው የሰጡትን ሁሉ ያሳያል። 20መጽሐፉም በበጎች ጌታ ፊት ተነበበ፤ እርሱም መጽሐፊቱን በእጁ አነሣ፤ አነበባት፤ አጥፎም አኖራት። 21ከዚያም በኋላ እረኞች ዐሥራ ሁለት ሰዓት ሲጠብቁ አየሁ፤ ከእነዚያም በጎች ሦስቱ ተመልሰው መጥተው ገቡ። 22ከዚያም ቤት የፈረሰውን ሁሉ ይሠሩ ጀመሩ፤ የዱር እሪያዎችም ከለከሏቸው፤ ነገር ግን አልተቻላቸውም። 23ዳግመኛም እንደ ቀድሞው ይሠሩ ጀመሩ፤ ግንቡንም አነሡት፤ ግንቡም ረዥም ይባላል። 24ዳግመኛም በግንቡ ፊት ማዕዷን ሲያኖሩ፥ የረከሰውንና ንጹሕ ያይደለውን ኅብስት ሁሉ በእርሱ ላይ ሲሠሩ አየሁ። 25በዚህ ሁሉ ላይም በጎች ዐይኖቻቸውን ተጋርደዋል፤ አያዩምም፤ እረኞቻቸውም እንደዚሁ ናቸው። 26ለጥፋትም አሳልፈው ይሰጧቸዋል፤ በጎቹንም በእግራቸው ይረግጧቸዋል፤ ይበሏቸዋልም። 27የበጎቹም ጌታ በጎች ሁሉ ዳግመኛ እስኪበተኑ ድረስ ዝም አለ፤ ከእነርሱም ጋር አንድ ሆኑ፤ ከአራዊትም እጅ አላዳኗቸውም። 28ያም መጽሐፉን የሚጽፍ አውጥቶ አሳየው፤ በበጎች ጌታ ማደሪያም አነበበው፤ ስለ እነርሱም ይማልደዋል። 29የእረኞችንም ሥራ ሁሉ እያሳየው፤ ይለምነዋል፤ በእረኞችም ሁሉ ላይ በፊቱ ያዳኛል፤ ያንም መጽሐፍ አንሥቶ በእርሱ ዘንድ አኑሮ ወጣ። 30ሠላሳ ሰባቱም እረኞች እንደዚህ እስከሚጠብቁበት ዘመን ድረስ አየሁ። 31ሁሉም በየጊዜያቸው እንደ ቀድሞዎቹ ፈጸሙ። 32ሌሎችም በየጊዜያቸው ይጠብቋቸው ዘንድ ከእጃቸው ተቀበሏቸው፤ እያንዳንዱም እረኛ ሁሉ በየጊዜው ነው። 33ከዚህም በኋላ የሰማይ ወፎችን ሁሉ በራእይ አየሁ፥ ንስሮችና ጥንብ አሞራ፥ አንጭት አሞራና ቍራዎች መጡ። ንስሮችም ወፎችን ሁሉ ይመሯቸው ነበሩ። 34እነዚያንም በጎች ይበሏቸው ጀመሩ፤ ዐይኖቻቸውንም ይጐጠጕጧቸው ጀመሩ፤ ሥጋቸውንም ይበሉአቸው ጀመሩ። 35በጎችም ሥጋቸው በወፎች ተበልቶአልና ጮኹ። 36እኔም ተኝቼ ሳለሁ ጮኽሁ፤ በጎችንም በሚጠብቃቸው በእረኛው ላይ አለቀስሁ። 37በጎችም በውሾችና በንስሮች፥ በአንጭት አሞራዎችም እስከ ተበሉ ድረስ አየሁ። 38አጥንቶቻቸው ብቻቸውን እስከ ቆሙ ድረስ ሥጋንና ቍርበትን፥ ጅማትንም ፈጽሞ አልተዉላቸውም፤ አጥንቶቻቸውም በምድር ላይ ወደቁ፤ በጎችም አነሱ። 39ሃያ ሦስቱም እረኞች እስከሚጠብቁበት ዘመን ድረስ አየሁ፤ አምሳ ስምንት ሱባኤንም በየዘመናቸው ፈጸሙ። 40ታናናሾች ጠቦቶችም ከእነዚያ ነጫጭ በጎች ተወለዱ፤ ዐይኖቻቸውንም ይገልጡና ያዩ፥ ወደ በጎችም ይጮኹ ጀመሩ። 41በጎችም አልጮሁላቸውም፤ የነገሯቸውንም ነገር አላዳመጧቸውም፤ ነገር ግን ፈጽመው ቸል አሉ፤ ዐይኖቻቸውንም ተሸፈኑ፤ በረታባቸውም። 42በራእይም በጠቦቶቹ ላይ ሲበርሩባቸው ቍራዎችን አየሁ፤ ከእነዚያም ጠቦቶች አንዱን ያዙት። 43በጎችንም ቀጥቅጠው በሏቸው፤ ለእነዚያ ጠቦቶችም ቀንዶች እስኪወጡላቸው ድረስ አየሁ። ቍራዎችም ቀንዶቻቸውን ይሰብሩባቸው ነበር። 44ከእነዚያም በጎች በአንዱ ላይ አንድ ትልቅ ቀንድ እስኪበቅል አየሁ። ዐይኖቻቸውም ተገለጡ። 45በእነርሱም አየባቸው፤ ዐይኖቻቸውም ተከፈቱ፤ ለበጎችም ጮኸላቸው፤ አውራዎችም አዩት፤ ሁሉም ወደ እርሱ ሮጡ። 46ንስሮችና ጥንብ አሞራዎች፥ ቍራዎችና አንጭት አሞራዎች እስከ ዛሬ ድረስ ይነጥቋቸው ነበር። በላያቸውም እያንዣበቡ ይበሏቸው ነበር። 47በጎች ግን ዝም ብለው ነበር፤ አውራዎችም ፈጽመው ይጮኹ ነበር፤ እነዚያም ቍራዎች ከእነርሱ ጋር ይጋደሉና ይጣሉ ነበር። ቀንዱንም ሊያስወግዱ ወደዱ፤ ነገር ግን አልቻሉትም። 48እረኞች፥ ንስሮችና እነዚያ ጥንብ አሞራዎች፥ አንጭት አሞራም እስኪመጡ ድረስ አየኋቸው። 49የዚያንም አውራ ቀንዱን ይሰብሩ ዘንድ ለቍራዎች ጮኹ። 50እነርሱም ከእርሱ ጋር ተጣልተው ተጋደሉ፤ እርሱም ከእነርሱ ጋር ተጣላ፤ ረድኤቱም ትመጣለት ዘንድ ጮኸ። 51የእረኞችን ስሞች የሚጽፍና በበጎች ጌታ ፊት የሚያቀርብ ያ ሰውም እስኪመጣ ድረስ አየሁ። 52እርሱም ረዳው፤ ሁሉንም አሳየው፤ የዚያም አውራ ረዳቱ ወረደ፤ ያም የበጎች ጌታ ወደ እነርሱ በመዓት እስኪመጣባቸው ድረስ አየሁ። 53ያዩትም ሁሉ ሸሹ፤ ሁሉም ከፊቱ የተነሣ በጥላው ወደቁ። ንስሮች፥ ጥንብ አሞራዎችና ቍራዎች፥ አንጭት አሞራም ተሰበሰቡ። 54ከእነርሱም ጋር የሜዳ በጎችን አመጡ፤ ሁሉም በአንድነት የዚያን አውራ ቀንድ ሊሰብሩ ተረዳዱ። 55በጌታ ቃል መጽሐፉን የሚጽፍ ያን ሰውም በኋላ የተነሡ እነዚያ ዐሥራ ሁለቱ እረኞች ያጠፉትን ያን የጥፋት መጽሐፍ እስኪገልጠው ድረስ አየሁት። 56ከእነርሱም አስቀድመው ከነበሩት እነርሱ አብልጠው እንዳጠፉ በበጎች ጌታ ፊት አሳየ፤ የበጎችም ጌታ ወደ እነርሱ እስኪመጣ ድረስ አየሁ። 57የቍጣውንም በትር በእጁ አንሥቶ ምድርን መታት፤ ምድርም ተሰነጠቀች፤ አራዊትም ሁሉ፥ የሰማይ ወፎችም ሁሉ ከእነዚያ ከበጎች የተነሣ ወደቁ፤ በምድርም ሰጠሙ፤ ምድርም ተጫነቻቸው። 58ለበጎችም ታላቅ ሰይፍ እስኪሰጣቸው ድረስ አየሁ፤ በጎችም ይገድሏቸው ዘንድ በዱር አራዊት ሁሉ ላይ ወጡ። 59አራዊትና የሰማይ ወፎችም ሁሉ ከፊታቸው ሸሹ።