1የምድረ በዳ አውሬዎችንና ወፎችንም ይወልዱ ጀመሩ- ከእነርሱም የአሕዛብ ሁሉ ዓይነት ተገኘ። 2አንበሶችና ነብሮች፥ ዥቦችና ውሾች፥ አውጮችና የዱር እሪያ፥ ቀበሮዎችና ሽኮኮዎች፥ 3አነርና ዘማች አሞራ፥ ጥንብ አሞራና አንጭት አሞራ፥ ጉሬዛና ቍራዎች። 4በመካከላቸውም ነጭ ላም ተወለደ፤ አንዱም ከሌላው ጋር እርስ በርሳቸው ይነካከሱ ጀመሩ። 5በመካከላቸው የተወለደው ያ ነጭ ላምም የሜዳ አህያን፥ ከእርሱም ጋር ነጭ ላምን ወለደ። 6የሜዳ አህዮችም በዙ፤ ከእርሱም የተወለደው ያ ላም- ጥቁር የዱር እሪያንና ነጭ በግን ወለደ። 7ያም የዱር እሪያ ብዙ እሪያዎችን ወለደ፤ በጉም ዐሥራ ሁለት በጎችን ወለደ። 8ዐሥራ ሁለቱ በጎችም ባደጉ ጊዜ ከእነርሱ አንዱን ለሜዳ አህዮች አሳልፈው ሰጡት። 9እነዚያ የሜዳ አህዮችም ያን በግ ለዥቦች ሁለተኛ አሳልፈው ሰጡት። በጉም በዥቦች መካከል አደገ። 10ጌታም ዐሥራ አንዱን በጎች ከእርሱ ጋር ይኖሩ ዘንድ፥ ከእርሱም ጋር በዥቦች መካከል ይሰማሩ ዘንድ አመጣቸው። 11እነዚህም በዙ፤ ብዙ የበጎች መንጋዎችንም ሆኑ፤ ዥቦችም ልጆቻቸውን እስኪጨርሱባቸው ድረስ ያስፈሯቸውና ያስጨንቋቸው ጀመሩ። 12ልጆቻቸውንም በብዙ ውኃ ፈሳሽ ጣሏቸው፤ እነዚያም በጎች ስለ ልጆቻቸው ይጮሁ፥ ወደ ጌታቸውም ይከሱ ጀመሩ። 13ከዥቦች የዳነውም በግ ሸሽቶ ወደ ሜዳ አህዮች ሄደ። 14የበጎች ጌታም የበጎችን ድምፅ ሰምቶ ከፍ ካለው ከጽርሐ አርያም እስኪወርድ ድረስ በጎችን እየጮሁ ሲያለቅሱ፥ በፍጹም ኀይላቸውም ጌታቸውን ሲለምኑት አየኋቸው። 15ወደ እነርሱም መጥቶ አያቸው፤ ከዥቦች ያመለጠውን ያን በግ ጠራው፤ በጎችንም እንዳይነኳቸው ያዳኝባቸው ዘንድ ስለ ዥቦች ነገረው። 16በጉም በጌታ ቃል ወደ ዥቦች ሄደ፤ ሌላው በግም ያን በግ ተገናኘው፤ ከእርሱም ጋር ሄደ። 17ሁለቱም በአንድነት ወደ ዥቦቹ ማኅበር ገቡ፤ ተናገሯቸውም። 18እንግዲህም ወዲህ በጎቹን እንዳይነኳቸው አዳኙባቸው። 19ከዚህም በኋላ በፍጹም ኀይላቸው እጅግ እንደ ጸኑባቸው ዥቦችን አየኋቸው። 20በጎችም ጮሁ፤ ጌታቸውም ወደ በጎች መጥቶ ዥቦቹን ይመታቸው ጀመረ። 21ዥቦችም ይጮሁ ጀመሩ፤ በጎቹም ዝም አሉ፤ ከዚያም ጊዜ ጀምሮ አልጮሁም፤ በጎችንም ከዥቦች ተለይተው እስኪወጡ ድረስ አየኋቸው። 22የዥቦችም ዐይኖቻቸው ተጋረዱ። እነዚያም ዥቦች በፍጹም ኀይላቸው በጎችን እየተከተሉ ወጡ። 23የበጎችም ጌታ እየመራቸው ከእነርሱ ጋር ሄደ፤ በጎችም ሁሉ እርሱን ተከተሉት፤ ፊቱም የበራና የከበረ ነው፤ መልኩም የሚያስፈራ ነው። 24ዥቦች ግን በአንዲት የውኃ መጠራቀሚያ እስኪገናኙአቸው ድረስ በጎቹን ይከተሏቸው ጀመሩ። 25ያም የውኃ መጠራቀሚያ ተከፈለ፤ ውኃውም በዚህና በዚያ በፊታቸው ቆመ፤ የበጎቹም ጌታ ይመራቸው ነበር፤ በመካከላቸውና በዥቦቹም መካከል ቆመ። 26ዥቦቹም በጎቹን ገና አላዩአቸውም ነበር፤ በውኃው ማጠራቀሚያ መካከልም ሄዱ። 27ዥቦችም በጎችን ተከተሏቸው፤ ዥቦቹም በውኃው መጠራቀሚያ ላይ ተከትለዋቸው ሮጡ። 28የበጎቹንም ጌታ ባዩት ጊዜ ከፊቱ ይሸሹ ዘንድ ተመለሱ። 29ያም የውኃው መጠራቀሚያ ተሰበሰበ፤ ፈጥኖም እንደ ቀድሞ ፍጥረቱ ሆነ፤ ውኃውም- እኒህን ዥቦች እስኪአሰጥማቸው ድረስ መልቶ ከፍ ከፍ አለ። 30በጎቹንም የተከተሏቸው ዥቦች ሁሉ እስኪጠፉና እስኪሰጥሙ ድረስ አየሁ። 31በጎች ግን ከውኃው ዐለፉ፤ ሣርና ውኃ ወደሌለበትም ምድረ በዳ ወጡ። 32ዐይኖቻቸውንም ገልጠው ያዩ ጀመሩ፤ ጌታቸውም ሲጠብቃቸውና ሣርና ውኃ ሲሰጣቸው አየሁ። 33ያም በግ በፊት በፊት እየሄደ ይመራቸው ነበር፤ በጉም ወደ ረዥሙ ዐለት ራስ ላይ ወጣ። 34የበጎቹም ጌታ ወደ እነርሱ ላከው፤ ከዚህ በላይ በፊታቸው የቆመውን የበጎችን ጌታ አየሁት። 35መልኩም ያማረ የሚያስፈራና፥ ኀይለኛ ነው፤ በጎቹም ሁሉ እርሱን አይተው ከፊቱ የተነሣ ፈሩ። 36እነዚያም ሁሉ ከእርሱ የተነሣ ይፈሩና ይንቀጠቀጡ ነበር፤ በመካከላቸውም ከነበረው ከሁለተኛው በግ ጋር ያለ ያን በግ ተከትለው ጮሁ። 37በጌታችን ፊት መቆም እርሱንም ማየት አይቻለንም አሉ፤ የሚመራቸውም ያ በግ ተመልሶ ወደ ዐለቱ ራስ ወጣ። 38በጎቹም ዐይኖቻቸውን ይጋረዱ፥ ካሳያቸውም መንገድ ይስቱ ጀመሩ። 39ያም በግ አላወቀም ነበር፤ የበጎችም ጌታ በእነርሱ ላይ ታላቅ ቍጣን ተቈጣባቸው። 40በጉም ዐውቆ ከዐለቱ ራስ ወረደ። 41ወደ በጎችም መጣ፤ ዐይኖቻቸው የተጋረዱባቸውንና ከመንገዱ የወጡትን አብዛኛዎቹን አገኘ። 42ባዩትም ጊዜ ፈሩ፤ ከፊቱም የተነሣ ተንቀጠቀጡ፤ ወደ ቦታቸውም ይመለሱ ዘንድ ወደዱ። 43ያም በግ ሌሎች በጎችን ከእርሱ ጋር ወሰደ፤ ወደ እነዚያ ወደ በደሉ በጎችም ገባ። 44ከዚህም በኋላ ይገድላቸው ጀመረ፤ በጎችም ከፊቱ የተነሣ ፈሩ፤ በጉም የበደሉ እነዚያን በጎች መለሳቸው፤ ወደ ቦታዎቻቸውም ተመለሱ። 45በዚያም በጉ ሰው እስኪሆን ድረስ፥ ለበጎቹም ጌታ ቤትን እስኪሠራ ድረስ፥ በጎቹንም ሁሉ በዚያ ቤት እስኪያቆማቸው ድረስ ራእይን አየሁ። 46በጎችንም የመራቸውን ያን በግ የተገናኘው በግ እስኪተኛ ድረስ አየሁ። 47ታላላቁ በጎችም ሁሉ እስኪጠፉ ድረስ አየሁ፤ በእነርሱም ፋንታ ታናናሾቹ ተነሥተው ወደ መንጋው ገቡ። 48ወደ ውኃው ፈሳሽም ቀረቡ፤ ይመራቸው የነበረው፥ ሰው የሆነው ያም በግ ከእነርሱ ተለይቶ ተኛ። 49በጎችም ሁሉ ፈለጉት፤ በእርሱም ላይ ታላቅ ጩኸትን ጮሁ፤ ለዚያም በግ ከሚጮሁት ጩኸት ዝም እስኪሉ ድረስ አየሁ። 50ያንም የውኃ ፈሳሽ አልፈውት ሄዱ፤ ስለ አንቀላፉትም ምትክ የሚመሯቸው በጎች ተተክተው መሯቸው። 51በጎችም ወደ አማረ ቦታ፥ ወደ ተወደደችና ወደ ሰባች ምድርም እስኪገቡ ድረስ አየሁ። 52እነዚያም በጎች እስኪጠግቡ ድረስ አየሁ፤ ያም ቤት ባማረች ምድር በመካከላቸው ይኖር ነበር። 53ሌላ በግ ተነሥቶ እስኪመራቸው ድረስ ዐይኖቻቸው የሚገለጡበትና የሚጋረዱበት ጊዜ ነበረ። 54ሁሉንም መለሳቸው፤ ዐይኖቻቸውም ተገለጡ። 55የበጎች አውራ ሌላ በግ እስኪነሣ ድረስም- እነዚያን በጎች ውሾችና ቀበሮች፥ የዱር እሪያም ይበሏቸው ጀመሩ። የሚመራቸውም አውራ ከእነርሱ አንዱ ነበር። 56ያም አውራ ሁሉን እስኪያጠፋቸው ድረስ እነዚያን ውሾችና ቀበሮች፥ የዱር እሪያውንም ወዲህና ወዲያ ይወጋ ጀመር። 57የዚያም በግ ዐይኖቹ ተገለጡ፤ በበጎች መካከል ያለ ክብሩን የተወ ያን አውራም አየው። 58እነዚያንም በጎች ይወጋቸውና ይረግጣቸው ጀመረ፤ እርሱም ያለ ደስታ ኖረ። 59የበጎችም ጌታ በጉን ወደ ሌላው በግ ላከው፤ ክብሩንም በተወው በዚያ በግ ፋንታ አውራ ይሆንና በጎችን ይመራቸው ዘንድ አስነሣው። 60ወደ እርሱም ሄዶ ለብቻው አነጋገረው፤ ያንም አውራ አስነሥቶ ለበጎቹ ገዥና መሪ አደረገው። 61በዚህም ሁሉ እነዚያ ውሾች በጎቹን ያስጨንቋቸው ነበር። 62መጀመሪያው አውራ ያን ኋለኛውን አውራ አሳደደው፤ ያም ኋለኛው አውራ ተነሥቶ ከፊቱ ሸሸ። 63መጀመሪያውንም አውራ ውሾቹ እስኪያጠፉት ድረስ አየሁ። 64እንዲህም ሆነ- ኋለኛው አውራ ተነሥቶ ታናናሽ በጎችን መራቸው። 65ይህም ኋለኛው አውራ ብዙ በጎችን ወልዶ ሞተ። 66ትንሹም በግ በእርሱ ፋንታ አውራ ሆነ፤ ለእነዚያም በጎች ገዥና መሪ ሆነ። 67እነዚያም በጎች አደጉ፤ በዙም። እነዚያም ውሾችና ቀበሮች፥ የዱር እሪያም ፈሩ፤ ከእርሱም ሸሹ። 68ያም አውራ አራዊትን ሁሉ ወጋ፤ አራዊትም ዳግመኛ በበጎች መካከል መግባት አልቻሉም። ከእነርሱም ምንም አልነጠቁም። 69ቤቱም ታላቅና ሰፊ ሆነ፤ ለእነዚያም በጎች በዚያ ቤት ላይ ግንብ ተሠራ። ለበጎችም ጌታ በዚያ ቤት ላይ ረዥምና ታላቅ ግንብ ተሠራ። 70ያም ቤት ተዋረደ፤ ግንቡ ግን ከፍ ከፍ አለ፤ ረዥምም ሆነ፤ የበጎችም ጌታ በዚያ ግንብ ላይ ቆመ፤ ሙሉ የሆነች ማዕድንም በፊቱ አቀረቡ። 71ዳግመኛም እነዚያን በጎች እንደ ሳቱና በብዙ ጎዳና እንደሄዱ አየኋቸው፤ ያንም ቤታቸውን ተዉ። 72የበጎችም ጌታ ከበጎች ውስጥ ጠርቶ ወደ በጎች ላካቸው፤ በጎችም ይገድሏቸው ጀመሩ። 73ከእነርሱም አንዱ ከሞት አመለጠ፤ አልተገደለምም፤ ፈጥኖም ሄዶ በበጎች ላይ ጮኸ። 74ሊገድሉትም ወደዱ፤ የበጎችም ጌታ ከበጎች እጅ አዳነው፤ ወደ እኔም አውጥቶ አኖረው። 75ጩኸውም ያዳኙባቸው ዘንድ ሌሎች ብዙ በጎችን ወደ እነዚያ በጎች ላከ። 76ከእነርሱም የተነሣ የበጎችን ጌታ ቤቱንና ግንቡን ሲተዉ አየሁ፤ ከዚህም ሁሉ ስተው ዐይኖቻቸው ተጋረዱ። 77የበጎችም ጌታ ብዙ ሰልፍን በእነርሱ ላይ እንዳደረገ፥ እነዚያም በጎች ያን ሰልፍ እስኪጠሩት ድረስ አየሁ። 78ቦታቸውንም አሳልፈው ሰጡ፤ እርሱም በአንበሶችና በነብሮች፥ በዥቦችና በአውጮች፥ በቀበሮችና በአውሬዎች ሁሉ እጅ ጣላቸው፤ እነዚያ የዱር አራዊትም በጎቹን ይነጥቋቸው ጀመሩ። 79እርሱም ቤታቸውንና ግንባቸውን እንደ ተወው አየሁ። 80ይነጥቋቸውም ዘንድ በአንበሶች እጅ፥ ይበሏቸውም ዘንድ በአራዊት ሁሉ እጅ ሁሉንም ጣላቸው። 81እኔም በፍጹም ኀይሌ እጮህ፥ የበጎችንም ጌታ እጠራውና ስለ በጎቹም አመለክተው ዘንድ ጀመርሁ፤ በዱር አራዊት ሁሉ ተበልተዋልና። 82እርሱም እያየ ዝም አለ፤ ደስም አለው፤ እነርሱ ተበልተው ተውጠዋልና፥ ንብረታቸውንም ተነጥቀዋልና፤ መብል እንዲሆኗቸውም በአራዊት ሁሉ እጅ ጣላቸው።