1ዳግመኛም፥ አንዱ ሌላውን ሲወጋው፥ አንዱም ሌላውን ሲውጠው አየሁ። 2ምድርም ትጮህ ጀመረች፥ ዳግመኛም ዐይኖቼን ወደ ሰማይ አቅንቼ በራእይ አየሁ። 3እነሆም፥ የሸበተ ሰውን የመሰሉ ከሰማይ ወጡ፥ አንዱም ከዚያ ቦታ ወጣ፤ ሦስቱም ከእርሱ ጋር ወጡ። 4ኋላም ከእርሱ ጋር የወጡ እነዚያ ሦስቱ እጄን ያዙኝ፥ በምድር ካሉ ሰዎችም ለይተው አነሡኝ። 5በረጅም ተራራ ላይም ከፍ አድርገው ከምድር የራቀች ግንብን አሳዩኝ፥ ኮረብታውም ሁሉ ከእርሱ ያነሰ ሆነ። 6እንዲህም አሉኝ- “በእነዚያ ዝሆኖችና ግመሎች ላይ፥ በአህዮችም ላይ፥ በከዋክብትም ላይ፥ በላሞቹም ሁሉ ላይ፥ የሚመጣውን ሁሉ እስክታይ ድረስ በዚህ ተቀመጥ።” 7ቀድመው ከወጡት ከእነዚያ ከአራቱ አንዱን አየሁት፥ ከሰማይም የወደቀ ያን መጀመሪያውን ኮከብ ያዘው። 8እጅና እግሩንም አስሮ በጥልቁ ጣለው፥ ያም ጕድጓድ ጠባብና ጥልቅ፥ ጭንቅና ጨለማም ነው። 9ከእነዚያም አንዱ ሰይፉን መዝዞ ለእነዚያ ዝሆኖች፥ ለእነዚያም ግመሎችና አህዮች ሰጣቸው። 10አንዱም ሌላውን ይወጋው ጀመረ፥ ምድርም ሁላ በእነርሱ ላይ ተነዋወጠች። 11በራእይም ባየሁ ጊዜ ከእነዚያ ከወጡት ከአራቱ አንዱ እነሆ፥ ከሰማይ መረቡን ጣለ። 12ኀፍረታቸው እንደ ፈረሶች ኀፍረት የሆነ ታላላቅ ከዋክብትንም ሁሉ ሰብስቦ ያዘ። 13ሁሉንም እጃቸውንና እግራቸውን አስሮ በምድር ጕድጓድ ጣላቸው። 14ከእነዚያም ከአራቱ አንዱ ወደ ነጩ ላም ሄደ፥ እየራደም ምሥጢርን አስተማረው። 15ያ ላምም ተወለደ፤ ሰውም ሆነ፥ መርከብንም ሠርቶ በእርሷ ተቀመጠ። 16ሦስቱ ላሞችም በዚያች መርከብ ከእርሱ ጋር ተቀመጡ፥ በእነርሱም ላይ መርከቡ ተዘጋ። 17ዳግመኛም ዐይኖቼን ወደ ሰማይ አቅንቼ ከፍ ያለ ጠፈርን አየሁ፥ በእርሱም ሰባት የውኃ ሻሻቴዎች አሉ፤ እነዚህም ሻሻቴዎች በአንድ ቦታ ብዙ ውኃን ያፈስሳሉ። 18ዳግመኛም አየሁ፥ እነሆም፥ በምድር ላይ በዚያ በታላቁ ቦታ ምንጮች ተከፈቱ። 19ያም ውኃ ይፈላና በምድር ላይ ይነሣ ጀመር፥ ምድሩም ሁሉ በውኃ እስኪሸፈን ድረስ ያን ቦታ አያሳየውም ነበር። 20በሁሉም ላይ ውኃው በዛ፤ ጨለማና ጉምም ሆነ፤ የዚያንም ውኃ ከፍታውን አየሁ፥ ውኃውም በዚያ ቦታ ላይ ከፍ ከፍ አለ። 21በቦታውም ላይ ውኃውን ያፈስስ ነበር፥ በምድር ላይም ጸና። 22በዚያም ቦታ ላሞች ሁሉ በውኃው ሲሰጥሙ፥ ሲዋጡና ሲጠፉም እስከማያቸው ድረስ ተሰበሰቡ። 23ያም መርከብ በውኃው ላይ ይንሳፈፍ ነበር፥ ላሞችና ዝሆኖች፥ አህዮችና ግመሎች፥ ከብቶችም ሁሉ በምድር ተሰጠሙ። 24እኔም እነርሱን ማየት አልተቻለኝም፤ እነርሱም መውጣት ተሳናቸው፥ በጥልቁም ባሕር ተሰጥመው ጠፉ። 25ዳግመኛም ከዚህ ከታላቁ ጠፈር እነዚህ ሻሻቴዎች እስኪጠፉ ድረስ በራእይ አየሁ፥ የምድሩም ምንጭ ተደፈነ። 26ሌሎች ጕድጓዶችም ተከፈቱ፥ ምድር እስኪገለጥ ድረስም ውኃው ወደ እነርሱ ይወርድ ጀመር። 27ያ መርከብም በምድር ላይ ተቀመጠ። ጨለማዪቱ ራቀች፥ ብርሃንም ሆነ። 28ሰው የሆነ ያም ነጭ ላም ከመርከቡ ወጣ፥ ሦስቱም ላሞች ከእርሱ ጋር ወጡ። 29ከእነዚህም ከሦስቱ ላሞች አንዱ ነጭ ላም ያን ላም ይመስለዋል፥ ከእነርሱም አንዱ እንደ ደም ቀይ ነው፤ አንዱም ጥቁር ነው፥ ያም ነጩ ላም ከእነርሱ ተለይቶ ሞተ።