1ከዚህ በኋላም ሌላ ሕልምን አየሁ፥ ልጄ፥ ሁሉን አሳየሁህ። 2ሄኖክም ለልጁ ማቱሳላ መለሰለት፥ እንዲህም አለ- “ልጄ፥ ነገሬን ስማኝ እልሃለሁ፤ 3የእኔን የአባትህን ሕልም ለመስማት ጆሮህን አዘንብል፥ እናትህ እድናንም ሳላገባት በመኝታዬ ራእይ አየሁ። 4እነሆ፥ ላም ከምድር ወጣ፥ ያም ላም ነጭ ሆነ፤ ከእርሱም በኋላ አንዲት ሴት ጥጃ ወጣች። 5ከእርስዋም ሁለት ጥጆች ወጡ፤ ከሁለቱም አንዱ ጥቁር ሆነ፥ አንዱም ቀይ ሆነ፤ ያም ጥቁሩ ጥጃ ያን ቀይ ጥጃ ወጋው፥ በምድርም ተከታተለው። 6ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ያን ቀይ ጥጃ ማየት አልተቻለኝም፥ ያም ጥቁሩ ጥጃ አደገ። 7ከእርሱም ጋር ያቺ ሴት ጥጃ መጣች። እርሱን መስለው ከእርሱ የሚወጡ ብዙ ላሞችንም አየሁ፥ እርሱንም ይከተላሉ። 8ያችም መጀመሪያዋ ሴቲቱ ጊደር ከዚያ ከመጀመሪያው ላም ፊት ወጣች። 9ያንም ቀይ ጥጃ ፈለገችው፥ አላገኘችውምም፥ ያንጊዜም ታላቅ ጩኸትን ጮኸችና ፈለገችው። 10ያም መጀመሪያው ላም ወደ እርሷ እስኪመጣ ድረስ አየሁ፥ ዝምም አሰኛት፥ ከዚያችም ጊዜ በኋላ አልጮኸችም። 11ከዚህም በኋላ ሌላ ነጭ ላምን ወለደች፥ ከእርሱም ቀጥሎ ብዙ ላሞችንና ጥቋቁር ጊደሮችን ወለደች። 12በመኝታዬም ነጭ በሬን አየሁ፥ እንደዚህም አደገ፥ ታላቅ ነጭ በሬም ሆነ፥ ከእርሱም ብዙ ነጫጭ ላሞች ተወለዱ፥ በመልክም ይመስሉታል። 13ብዙ ነጫጭና የሚመስሏቸውን ላሞችንም ይወልዱ ጀመር፥ አንዱም ሌላውን ተከተለው። 14ዳግመኛም ተኝቼ በዐይኖቼ አየሁ፥ ወደ ላይም ሰማይን ተመለከትሁ። 15እነሆ፥ ከሰማይ አንድ ኮከብ ወደቀ፤ ከፍ ከፍም ይላል፥ ይበላልም፥ በእነዚያም ላሞች መካከል ይሰማራል። 16ከዚያም በኋላ ታላላቆችንና ጥቋቁር ላሞችን አየሁ፥ እነሆ፥ ሁሉም መመሰጊያቸውንና መሰምሪያቸውን፥ ጥጆቻቸውንም ለወጡ፤ አያንዳንዳቸውም ከሌላው ጋር ይጮሁ ጀመሩ፥ 17ዳግመኛም ራእይ አየሁ፥ ሰማይንም ተመለከትሁ። 18እነሆ፥ ብዙ ከዋክብትንም አየሁ፥ ከሰማይም ወደዚያ ወደ መጀመሪያው ኮከብ ወርደው ወደቁ፥ በእነዚያም ጥጆች መካከል ላሞች ሆኑ። 19ከእነርሱም ጋር በመካከላቸው የሚሰማሩ ሆኑ፥ እነርሱንም ፈጽሜ አየኋቸው። 20እነሆ፥ ሁሉም እንደ ፈረሶች ኀፍረታቸውን አውጥተው በላሞች ጊደሮች ላይ ይንጠላጠሉ ጀመሩ። 21ሁሉም ፀንሰው ዝሆኖችንና ግመሎችን፥ አህዮችንም ወለዱ፤ ላሞችም ሁሉ እነርሱን ፈሩአቸው፥ ከእነርሱም የተነሣ ደነገጡ። 22በጥርሳቸውም እየበታተኑ ይጥሏቸውና ይውጧቸው፥ በቀንዶቻቸውም ይወጓቸው ጀመሩ፤ ከዚያም በኋላ እነዚያን ላሞች ይበሏቸው ጀመሩ። 23እነሆም፥ የምድር ልጆች ሁሉ ከእነርሱ የተነሣ ይንቀጠቀጡና ይነዋወጡ፥ ከእነርሱም ይሸሹ ጀመሩ።