1ልጄ ማቱሳላ፥ ዛሬ ያየሁትን ራእይ ሁሉ ገለጥሁልህ፥ ይህንም በፊትህ እናገራለሁ። 2ሚስት ሳላገባ ሁለት ራእዮችን አየሁ፤ ከእነርሱም አንዱ ከሌላው ጋር አይመሳሰልም። 3መጀመሪያውን ራእይ መጽሐፍን በምማርበት ጊዜ አየሁ፤ ሁለተኛም እናትህን ሳላገባት ጽኑዕ ራእይን አየሁ። 4ስለ እነዚህም ነገሮች ጌታን ለመንሁት፤ በአያቴ በመላልኤልም ቤት ተኝቼ ሳለሁ በራእይ ሰማይ ሲወድቅና ሲነጠቅ፥ በምድርም ላይ ሲወድቅ አየሁ። 5በምድርም ላይ በወደቀ ጊዜ ምድርን በታላቅ ጥልቅ እንደምትሰጥም አየኋት። 6ተራሮች በተራሮች ላይ ሲሰቀሉ፥ ኮረብታዎችም በኮረብታዎች ላይ ሲሰጥሙ፥ ረዣዥም ዛፎችም ከግንዶቻቸው እየተነቀሉ ሲወድቁ፥ በጥልቅ ወንዝም ሲሰጥሙ አየኋቸው። 7ከእርሱም የተነሣ በአንደበቴ ነገር ተነገረ፥ “ምድር ጠፋች” ብዬ እጮህ ጀመር። 8አያቴ መላልኤልም እኔ በእርሱ ዘንድ ተኝቼ ሳለሁ አስነሣኝ፤ “ልጄ፥ እንደዚህ ለምን ትጮሃለህ? እንደዚህስ ለምን ታለቅሳለህ?” አለኝ። 9እኔም ያየሁትን ራእይ ሁሉ ነገርሁት። 10እርሱም አለኝ- “ልጄ፥ በአእምሮ የጸናህ እንደ መሆንህ አየህ፥ በምድር የተሰወረውን ሁሉ ኀጢአት በሕልም ማየትህ በረታ፤ ምድርም በጥልቁ ትሰጥም ዘንድ አላት፥ ታላቅ ጥፋትንም ትጠፋለች። 11አሁንም ልጄ፥ አንተ የታመንህ ነህና በምድር ላይ ቅሬት እንዲተርፍ፥ ምድርንም እንዳያጠፋት ተነሥተህ የክብር ባለቤት ጌታን ለምነው። 12ልጄ፥ ይህ ሁሉ ከሰማይ ወርዶ በምድር ይሆናል፥ በምድርም ላይ ጽኑዕ ጥፋት ይሆናል።” 13ከዚህም በኋላ ተነሥቼ ጸለይሁ፥ ማለድሁ፤ ለመንሁም፥ ጸሎቴንም ለልጅ ልጅ ዘመን ሊሆን ጻፍሁት። 14ልጄ ማቱሳላ! ሁሉን አሳየሁህ፤ አንገቴን ደፍቼ በወጣሁ ጌዜ ሰማይን አየሁት፥ ፀሐይንም በምሥራቅ ሲወጣ አየሁ። 15ጨረቃም በምዕራብ ሲገባ አየሁ፤ የጥቂቶችን ከዋክብትና የምድርን ሁሉ ማነስ አየሁ፤ ሁሉንም ዐወቅሁ፥ በመጀመሪያም የፍርድ ባለቤት ጌታን አመሰገንሁት። 16ከምሥራቅ መስኮትም ፀሐይን አውጥትWaልና ምስጋና አቀረብሁለት፤ ፀሐይም ወጥቶ በሰማይ ላይ አበራ፥ ተነሥቶም በታየችለት ጎዳና ይሄዳል። 17በእውነትም እጆቼን ከፍ ከፍ አደረግሁ፥ ቅዱሱንና ገናናውንም አመሰገንሁት፤ 18አምላክ ይናገሩበት ዘንድ ለሰው ልጆች በፈጠረው በአፌ እስትንፋስና በሥጋዊ አንደበቴ ተናገርሁ፥ ይናገሩበትም ዘንድ እስትንፋስን፥ አንደበትንና አፍን ሰጣቸው። 19ጌታ ሆይ፥ አንተ ቡሩክ ነህ፤ ንጉሥ፥ ገናና፥ ኀያል፥ በገናናነትህም የሰማይ ፍጥረት ሁሉ ጌታ ነህ፥ የነገሥታት ንጉሥና የዓለሙ ሁሉ አምላክ ነህ። 20አገዛዝህና መንግሥትህ፥ ገናናነትህም ለዘለዓለም ይኖራል፤ ሥልጣንህም ለልጅ ልጅ ሁሉ ነው። 21ሰማዮችም ሁሉ ለዘለዓለሙ መኖሪያህ ናቸው፤ ምድርም ሁላ ለዘለዓለም የእግሮችህ መረገጫ ናት። 22አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና፥ አንተም ሁሉን ትገዛለህና አንዱ ስንኳ ሥራ አይሳንህም፤ አንዲት ጥበብም አትሰወርህም፤ ዙፋንህም ከአኗኗርዋ አትለወጥም፥ አንተም ከባሕርይህ አትለወጥም። 23አንተም ሁሉን ታውቃለህ፥ ታያለህም፥ ትሰማለህም፥ ሁሉንም ታያለህና ከአንተ የሚሰወር የለም። 24አሁንም የሰማያትህ መላእክት 25አሁንም አምላክ፥ ጌታና ገናና ንጉሥ ሆይ፥ በምድር የልጅ ልጅ ታስቀርልኝ ዘንድ ልመናዬን እንድትሰማኝ ፈጽሜ እለምናለሁ። 26ሰውን ሁሉ አታጥፋ፥ ምድርንም ባዶዋን አታስቀራት፥ ለዘለዓለምም ጥፋት አይሁን። 27አሁንም ጌታዬ ሆይ፥ አንተን ያሳዘነችህ ሰውነትን ከምድር አጥፋ። 28የጽድቅና የቅንነት ሰውነትንም ለዘለዓለም ዘር ተክል አጽና። አቤቱ ከእኔ ከባሪያህም ልመና ፊትህን አትመልስ።