1አሁንም ልጄ ማቱሳላ፥ እነዚህን ሁሉ ለአንተ እናገራለሁ፤ ለአንተም እጽፍልሃለሁ፥ ሁሉንም ገለጥሁልህ፤ የእነዚህንም ሁሉ መጻፎቻቸውን ሰጠሁህ። 2ልጄ ማቱሳላ፥ ለዓለም ትውልድ ታስተላልፍ ዘንድ የአባትህን የእጅ መጻፎች ጠብቅ። 3ለአንተና ለልጆችህ፥ ለአንተም ልጆች ለሚሆኑት ጥበብን ሰጠሁህ። ይህችም ጥበብ ለልጆቻቸውና ለልጅ ልጆቻቸው እስከ ዘለዓለም ያስተላልፉ ዘንድ በሕሊናቸው ትኖራለች። 4ይህችን ጥበብ ይማሯት ዘንድ የሚያስተውሉና በጆሯቸው የሚያደምጡ ሰዎች አያንቀላፉም፥ ለሚበሏትም ካማሩ ምግቦች ይልቅ ትስማማቸዋለች። 5ጻድቃንም ሁሉ ብፁዓን ናቸው፤ በጽድቅ መንገድ የሚሄዱና በዘመናቸው ሁሉ ቍጥር እንደ ኃጥኣን ኀጢአት የሌለባቸውም ብፁዓን ናቸው። 6በሰማይ የሚሄድ ፀሓይ፥ ከሻለቆች ጋር በመስኮቶች ሠላሳ ቀን ይገባል፥ ይወጣልም። 7ከሚጨመሩላቸውና አራቱን ክፍለ ዘመን ከሚለዩ ከሚመሯቸው አራት ከዋክብት ጋራ የከዋክብት ሥርዐታቸው ይህ ነው። 8ከእነርሱም ጋር አራት ቀን ይገባሉ፥ ስለ እነርሱም ሰዎች ይሳሳታሉ፤ በዓለሙ ሁሉ ቍጥርም አይቈጥሯቸውም፥ ይስትWaቸዋልና። 9ሰዎችም ጠንቅቀው አያውቋቸውም፤ በዘመኑ ቍጥር አሉና፥ ለዘለዓለምም በእውነት የተጻፉ ናቸው። 10አንዱ በመጀመሪያዪቱ መስኮት፥ አንዱም በሦስተኛዪቱ መስኮት፥ አንዱም በአራተኛዪቱ መስኮት፥ አንዱም በስድስተኛዪቱ መስኮት ይገባል። 11ዓመቱም በሦስት መቶ ስድሳ አራት ቀን ይፈጸማል፤ ነገሩም እውነት ነው፥ የተጻፈውም ቍጥሩ የተጠነቀቀ ነው። 12የዓለም ፍጥረት ሁሉ ጌታ ስለ ሰማይ ሠራዊት ለእኔ ያዘዘልኝ መልአኩ ዑርኤል ስለ ብርሃናትና ወሮች፥ ስለ በዓላት፥ ስለ አራቱ ክፍለ ዘመኖችና ዓመታት፥ ስለቀኖችም አሳየኝ፤ ዕውቀትንም አሳደረብኝ። 13እርሱም በሰዎች ላይ በሰማይ የፀሐይንና የጨረቃን፥ የከዋክብትንም፥ በክበባቸው የሚመላለሱ የሰማይ ሠራዊትንም ሁሉ ብርሃን ያሳይ ዘንድ በመዓልትና በሌሊት ሥልጣን አለው። 14በቦታዎቻቸውና በዘመኖቻቸው፥ በሱባዔዎቻቸውና በወሮቻቸውም የሚወጡና የሚገቡ የከዋክብት ሥርዐት ይህቺ ናት። 15ምግብናቸውን የሚጠብቁ ከዋክብትን የሚመሩ የከዋክብት ስማቸው ይህ ነው፤ በዘመኖቻቸውና በሥርዐቶቻቸው፥ በጊዜዎቻቸውና በወሮቻቸው፥ በሥልጣኖቻቸውም በመቋሚያዎቻቸውም ይገባሉ። 16አራቱን ክፍለ ዓመት የሚለዩ አራቱ መሪዎቻቸው አስቀድመው ይገባሉ። 17ከእነርሱም ቀጥሎ ሠላሳውን ቀንና ሦስት መቶ ስድሳ አራት ቀን የሚሆን ዓመቱን የሚለዩ ሥርዐታት የሚባሉ ኮከቦችን የሚመሩ ዐሥራ ሁለት የወር መጋቢዎች፥ ሰባቱን ዕለታትና አራቱን ክፍለ ዘመን በሚለዩ በዘጠና አንድ መጋቢዎች ላይ የሚጨመሩ አራቱንም ጳጉሜን ከሚለዩ ከሺ አለቆች ጋር ይገባሉ። 18እነዚያም የሺህ አለቆቹ በመሪና በተመሪ መካከል ናቸው፥ አንዱም በአንዱ መቋሚያ በኋላ ይጨመራል፤ መሪዎቻቸውም ሠላሳውን ቀን ይለያሉ። 19የተሠሩ አራቱን ክፍለ ዘመን የሚለዩ የእነዚህ መጋቢዎች 20የሺህ አለቆችን የሚመሯቸው የወር መጋቢዎች ስማቸው አንድርናኤል፥ ኢየሱሳኤል፥ ኢይሉማኤልም ናቸው። 21ሥርዐታት የሚባሉ የሻለቆችን የሚመሩ መጋቢዎችን 22አንዱም- አራቱን ክፍለ ዘመን የሚለዩ ምቅዋማትን 23ስሙ ተመዓኒና 24በምግብናው የሚመግባቸው ቀኖችም ሁሉ ዘጠና አንድ ቀኖች ናቸው። 25በእርሱ ምግብና ወራትም በምድር ላይ ይታዩ ዘንድ ያላቸው እነዚህ የቀኖቹ ምልክቶች ላብ፥ ዋዕይና ኀዘን ናቸው። 26ዛፎችም ሁሉ ያፈራሉ፤ ቅጠልም በዛፎች ሁሉ ላይ ይወጣል፤ የስንዴውም መከርና ጽጌረዳውም፥ ሌሎች አበባዎችም ሁሉ በሜዳው ያብባሉ፤ በክረምት የሚለመልሙ ዛፎችም ይደርቃሉ። 27በበታቾቻቸው ያሉ የመሪዎቻቸው ስሞች ብርክኤልና ዘሓብሳኤል ናቸው፤ 28ከእነርሱ ጋር የሚጨመር ሌላው የሻለቃ ስሙ ሄሉያሴፍ ነው። 29የዚህ የምልክኤል የምግብናው ወራት ተፈጸመ፤ ከእርሱም ቀጥሎ ሁለተኛው መጋቢ ስሙን ብሩህ ፀሐይ ብለው የሚጠሩት ሕልመልመሌክ ነው። 30የሚያበራበትም ቀን ሁሉ ዘጠና አንድ ቀን ነው፤ በምድር ላይ የሚመግብባቸው ወራቶች ምልክቶች ሙቀትና ድርቅ ናቸው። 31ዛፎችም ፈጽሞ የበሰለ ፍሬያቸውን ያወጣሉ፥ የደረቀ ፍሬያቸውንም ይሰጣሉ፤ በጎችም ይንጠላጠላሉ፥ ይፀንሳሉም። 32ሰዎችም የምድር ፍሬን ሁሉ፥ በእርሻውም ያለውን ፍሬ ሁሉ፥ በወይኑ ዐውድማ ያለውን ፍሬ ሁሉ ይሰበስባሉ፥ በምግብናውም ወራት ይህ ሁሉ ይደረጋል። 33ስማቸውና ሥርዐቶቻቸውም እነዚህ ናቸው፤ በበታቻቸው ያሉ የዕለት መጋቢዎችን የሚመሩ የሻለቆችም ስማቸው ጊዳኤልና ኪኤል፥ ሄኤልም ናቸው። 34ከእነርሱም ጋር የሚጨመር የሺህ አለቃ ስሙ አስፋኤል ነው፥ የምግብናውም ወራት ተፈጸመ።