1በኃጥኣንም ወራት ክረምቶች ያጥራሉ፤ በእርሻቸውና በመሰምሪያቸው ያለ አዝመራቸውም በኋላ ይደርሳል። 2በምድር ላይ ያለ ሥራ ሁሉ ይለወጣል፥ በዘመኑም አይታይም፤ ዝናምም ይከለከላል፥ ሰማይም ዝናምን ታቆማለች። 3በእነዚያም ዘመኖች የምድሩ ፍሬ ኋለኛ ይሆናል፥ በዘመኑም አይበቅልም፤ የዛፉም ፍሬ በዘመኑ ከማፍራት ይከለከላል። 4ጨረቃም ሥርዐቱን ይለውጣል፥ በዘመኑም ሲያበራ አይታይም። 5በእነዚያም ወራቶች ሰማይ ጠርቶ ይታያል፤ ድርቅም በምዕራብ በኩል በታላቅ ሠረገላ ዳርቻ ሁኖ ይደርሳል፥ ሰማይም ከብርሃን ሥርዐት ይልቅ ፈጽሞ ያበራል። 6ብዙዎች የትእዛዝ ከዋክብት አለቆችን ይስታሉ፤ እኒህም መንገዳቸውንና ግብራቸውን ይለውጣሉ፥ በታዘዙላቸው ዘመኖቻቸውም አይታዩም። 7የከዋክብት ሥርዐትም ሁሉ በኀጢአተኞች ላይ ይለወጥባቸዋል፥ በምድር ላይም የሚኖሩ ሰዎች በእነርሱ ላይ አእምሮአቸውን ይለውጣሉ። 8ከመንገዳቸውም ሁሉ ይለወጣሉ፥ ይስታሉ፥ አማልክትንም ያስመስሏቸዋል። 9መከራም ይበዛባቸዋል፥ መቅሠፍትም ሁሉን ያጠፋቸው ዘንድ ይመጣባቸዋል። 10እንዲህም አለኝ- “ሄኖክ ሆይ! በሰማይ ሰሌዳ የተጻፈውን መጽሐፍ ተመልከት፥ በእነርሱም የተጻፈውን አንብብ። እያንዳንዱንም ሁሉ መርምረህ ዕወቅ።” በሰማይ ሰሌዳ የተጻፈውንም ተመለከትሁ፤ የተጻፈውንም ሁሉ አነበብሁ፥ ሁሉንም ዐወቅሁ። 11መጽሐፊቱንም አነበብኋት፥ በእርሷም የተጻፈውን የሰዎችን ሥራ ሁሉ ተመለከትሁ፤ እስከ ዓለም ትውልድ ድረስ በምድር ላይ ያለ ከሥጋ የተወለደውንም ሁሉ አየሁ። 12ከዚህም በኋላ ያንጊዜ የዓለሙን ሥራ ሁሉ እንደ ሠራ ታላቁን የዘለዓለማዊ ክብር ንጉሥ ጌታን አመሰገንሁት። 13ስለ ትዕግሥቱም ጌታን አከበርሁ፤ አመሰገንሁም፥ በአዳም ልጆችም ላይ አለቀስሁ። 14ያንጊዜም እንዲህ አልሁ- “ጻድቅና ቸር ሳለ የሚሞት፥ የበደልም ደብዳቤ ሁሉ ያልተጻፈበት፥ በፍርድ ቀንም በእርሱ ላይ በደል ያልተገኘበት ሰው ብፁዕ ነው።” 15እነዚያም ሦስቱ ቅዱሳን 16እንዲህም አሉኝ- “ለልጅህ ለማቱሳላ ይኽን ሁሉ ንገር፤ በጌታ ፊትም ሥጋዊ ሰው ሁሉ እንደማይጸድቅ ለልጆችህ ሁሉ ይህን ገልጠህ አስተምር፥ እርሱ ፈጥሮአቸዋልና። 17ልጆችህን ታስተምራቸው ዘንድ፥ ትጽፍላቸውም ዘንድ፥ ለልጆችህም ሁሉ ታዳኝባቸው ዘንድ ዳግመኛ እስክታዝዛቸው ድረስ በልጆችህ ዘንድ አንድ ዓመት እንተውሃለን። 18በሁለተኛው ዓመት ግን ከእነርሱ መካከል ይወስዱሃል፤ ደጎች ለደጎች እውነትን ያስተምራሉና ልቡናህ ይጽና። 19ጻድቅ ከጻድቅ ጋር ደስ ይለዋል፥ እርስ በርሳቸውም ሰላምታ ይሰጣጣሉ፤ ኃጥእም ከኃጥእ ጋር ይሞታል፥ ወደ ኀጢአትም የተመለሰ ወደ ኀጢአት ከተመለሰው ጋራ ይሰጥማል። 20ጽድቅንም የሚሠሩ ሰዎች በክፉ ሰዎች ሥራ ይሞታሉ፥ ስለ ክፉ ሰዎች ሥራም ይሰበሰባሉ። 21በእነዚያም ወራቶች ከእኔ ጋር መነጋገራቸውን ጨረሱ፥ የዓለማትንም ጌታ እያመሰገንሁ ወደ ዘመዶቼ ተመለስሁ።