1የፀሐይ ስሙ እንደዚህ ነው፤ አንዱ ኦርያሬስ፥ ሁለተኛውም ቶማስስ ይባላል። 2ለጨረቃም አራት ስሞች አሉት፤ አንዱ ስሙ አሶንያ ይባላል፥ ሁለተኛውም ዕብላ ይባላል፥ ሦስተኛው ብናሴ ይባላል፥ አራተኛውም ኤራዕ ይባላል። 3ታላላቅ ብርሃናት እነዚህ ሁለቱ ናቸው፤ ክበባቸውም እንደ ሰማይ ክበብ ነው፤ የሁለቱም መጠኖቻቸው እኩል ናቸው። 4በፀሐይ ሰሌዳም ከጨረቃ ሰባት ክፍለ ብርሃን ይጨመርበታል፥ የፀሐይ ሰባተኛው ክፍል እስኪጨረስ ድረስ በልክ ትቀበላለች። 5በምዕራብ መስኮት ይገባሉ፥ ወደ መስዕም ይዞራሉ፥ በምሥራቅም መስኮት በሰማይ ፊት ይወጣሉ። 6ጨረቃም በወጣ ጊዜ በሰማይ ይታያል፤ የሰባተኛውን ክፍለ ብርሃን እኩሌታም ይቀበላል። 7በዐሥራ አራተኛው ቀንም ብርሃኑን ፈጽሞ ያገኛል፤ ሦስት አምስተኛ ክፍለ ብርሃንም ይጨመርለታል። 8ለዘመን ምልክት ሊሆን እስከ ዐሥራ አምስት ቀን ብርሃኑን ፈጽሞ ያገኛል፤ ሦስት አምስተኛም ይሆናል፤ ጨረቃም በአንድ ሰባተኛ እጅ እኩሌታ ይሆናል። 9በሕፀፁም ጊዜ በመጀመሪያዪቱ ቀን ዐሥራ አራተኛውን እጅ ክፍለ ብርሃን ያጣል፤ በሁለተኛዪቱም ቀን ዐሥራ ሦስተኛዪቱን እጅ ያጣል። 10በሦስተኛውም ቀን ዐሥራ ሁለተኛውን እጅ ያጣል፤ በአራተኛውም ቀን ዐሥራ አንደኛውን እጅ ያጣል። 11በአምስተኛውም ቀን ዐሥረኛውን ክፍል ያጣል፤ በስድስተኛውም ቀን ዘጠነኛውን ክፍል ያጣል። 12በሰባተኛውም ቀን ስምንተኛውን ክፍል ያጣል፥ በስምንተኛውም ቀን ሰባተኛውን ክፍል ያጣል። 13በዘጠነኛውም ቀን ስድስተኛውን ክፍል ያጣል፤ በዐሥረኛውም ቀን አምስተኛውን ክፍል ያጣል። 14በዐሥራ አንደኛውም ቀን አራተኛውን ክፍል ያጣል፤ በዐሥራ ሁለተኛውም ቀን ሦስተኛውን ክፍል ያጣል። 15በዐሥራ ሦስተኛውም ቀን ሁለተኛውን ክፍል ያጣል፤ በዐሥራ አራተኛውም ቀን የሰባተኛውን እጅ እኩሌታ ያጣል። 16በዐሥራ አምስተኛው ቀንም ከብርሃን የቀረ ብርሃኑ ሁሉ ይጨረሳል። 17በታወቁም ወራቶች በእየሃያ ዘጠነኛው ቀን ለጨረቃ ምላት ይሆናል፤ በእየሃያ ስምንተኛው ቀንም ምላት የሚደረግበት ጊዜ አለ። 18መልአኩ ዑርኤልም ብርሃን በጨረቃ በተሣለ ጊዜ ሌላ ሥርዐትን አሳየኝ። 19ጨረቃም ከፀሐይ ብርሃን ከሚጨመርላት ቀን ጀምሮ በምትሄድበት ዘመን ሁሉ ብርሃኗን በፀሐይ ፊት ታገኛለች፤ እስከ ዐሥራ አራተኛው ቀን ድረስም ብርሃኗ በሰማይ ይፈጸማል። 20ሁሉም 21ፀሐይ ወደ ምዕራብ በሚገባበትም ቀን ብርሃኑ በጥንቃቄ ይጨረሳል፥ በሌሊትም ከምሥራቅ ይወጣል። 22ፀሐይም በፊቱ እስኪወጣ ድረስ ጨረቃ መላ ሌሊቱን ያበራል፤ ጨረቃም በፀሐይ ፊት ይተያያል። 23የጨረቃ ብርሃን ከወጣበት ጀምሮ ብርሃኑ ሁሉ እስኪጨረስ ድረስ ዳግመኛ ከዚያ ይጐድላል። 24ጨረቃም የሚያበራበት ወር ያልፋል፥ ሰሌዳውም ብርሃን የሌለበት ባዶ ይሆናል። 25ሦስት ወር ምላት በሚያደርግበት ዘመኑ በሠላሳኛው ቀን ሕፀፅ ያደርጋል። ሦስቱንም ወር ሕፀፅ በሚያደርግባቸው ቀኖች በእየሃያ ዘጠነኛው ቀን ሕፀፅ ያደርጋል። 26በመጀመሪያው ዘመን፥ በመጀመሪያው መስኮት በመቶ ሰባ ሰባት ቀን፥ በመወለጃውም ዘመን ሦስቱን ወር በየሠላሳኛው ቀን ይታያል። ሦስቱንም ወር በእየሃያ ዘጠነኛው ቀን ይታያል። 27ያለ ፀሐይ ብርሃን ሌላ ብርሃን ምንም የላትምና በእየሃያኛው ቀን በሌሊት ሰው መስሎ፥ በቀንም ሰማይ መስሎ ይታያል። 28አሁንም ልጄ ማቱሳላ ሆይ፥ ሁሉን አሳየሁህ፤ የሰማይ ከዋክብት ሥርዐት ሁሉ ተፈጸመ። 29በእየቀኑ ሁሉና በእየዘመኑ ሁሉ፥ በእየሹመታቸውም ሁሉ፥ በእየዓመቱም ሁሉ፥ በመውጫውና በታዘዘበት ሁሉ፥ በወሩ ሁሉና በሱባዔው ሁሉ የሚሆነውን የእነዚህን ሥርዐት አሳየኝ። 30በዚች በስድስተኛዪቱ መስኮት ብርሃኑ ጨርሶ ይጠፋልና በስድስተኛዪቱ መስኮት የሚደረግ የጨረቃንም ሕፀፅ አሳየኝ። 31ከዚያም በኋላ የወር መባቻ ይሆናል፤ ሕፀፅ በሚያደርግበትም ዘመን በመጀመሪያዪቱ መስኮት የሚደረገውን ሕፀፅ አሳየኝ። 32መቶ ሰባ ሰባት ቀን እስኪፈጸም ድረስ በሱባዔው ሥርዐት ቢቈጥሩት ሃያ አምስት ሱባዔ ከሁለት ቀን ይሆናል። 33ጨረቃ በአንዱ ዓመት ከፀሐይና ከከዋክብት ሥርዐት የሚያንሰው በጥንቃቄ ቢቈጠር አምስት ቀን ይሆናል። 34ይህም የምታየው አንቀጽ በተፈጸመ ጊዜ መሪያቸው ታላቁ መልአክ ዑርኤል ካሳየኝ ከብርሃን ሁሉ የሚበልጥ እንደዚህ ያለ አርኣያና ምሳሌን ታያለህ። 35በዚያም ወራት መልአኩ ዑርኤል ሄኖክ ሆይ፥ “እነሆ፥ ሁሉን አሳየሁህ” ብሎ መለሰልኝ። 36ይህን ፀሐይ፥ ይህንም ጨረቃ ታየው ዘንድ፥ የሰማይ ከዋክብትን የሚመሯቸውን፥ 37ሥራቸውንና ዘመናቸውንም፥ መውጫቸውንም የሚለውጡትን ሁሉ ታያቸው ዘንድ ገለጥሁልህ።