1ነፋሳት ከእነርሱ የሚወጡባቸውና በምድር ላይ የሚነፍሱባቸው፥ ለነፋስት ሁሉ የተከፈቱ ዐሥራ ሁለት መስኮቶችን በምድር ዳርቻ አየሁ። 2ከእነርሱም ሦስቱ በምሥራቅ፥ ሦስቱም በምዕራብ፥ ሦስቱም በሰሜን፥ ሦስቱም በደቡብ የተከፈቱ ናቸው። 3መጀመሪያዎቹ ሦስቱ በምሥራቅ፥ ሦስቱም በመስዕ፥ በኋላ በግራ በኩል ያየኋቸው ሦስቱ በአዜብ፥ ሦስቱም በምዕራብ ናቸው። 4ከእነርሱም በአራቱ የበረከትና የሰላም ነፋሶች ይወጣሉ፤ ከእነዚያም ከስምንቱ የመቅሠፍት ነፋሶች ይወጣሉ። 5እነዚህም በተላኩ ጊዜ ምድርን ሁላ ያጠፏታል፤ በእርሷም ላይ ያለውን ውኃ፥ በእርሷም ላይ የሚኖሩትን ሁሉ፥ በውኃና በየብስ ላይ ያለውንም ሁሉ ይደመስሳሉ። 6ከእነዚህም መስኮቶች ለአዜብ በምትቀርብ በምሥራቅ በኩል ባለች በመጀመሪያዋ መስኮት ስሙ ጽባሓይ የሚባል መጀመሪያው ነፋስ ይወጣል፤ ከእርስዋም የምድር ድምሳሴ፥ ድርቅና ጥፋት ይወጣል። 7በመካከል ባለች በሁለተኛዪቱ መስኮትም ቅንነት ይወጣል፤ ከእርሷም ዝናብ፥ ፍሬም፥ ሰላምና ጠልም ይወጣል። 8በመስዕ በኩል ባለች በሦስተኛዪቱ መስኮትም ውርጭ፥ ድርቅም ይወጣል። 9ከእነዚህም ነፋሳት በኋላ በደቡብ በኩል ያሉ ነፋሳት በመጀመሪያዎቹ በሦስቱ መስኮቶች ይወጣሉ። 10ከእነርሱም ለምሥራቅ በምትቀርብ በመጀመሪያዪቱ መስኮት የድርቅ ነፋስ ይወጣል። 11በእርስዋ አጠገብ ባለች በመካከለኛዪቱ መስኮትም ከእርስዋ መልካም ሽቱ፥ ጠልና ዝናም፥ ሰላምና ሕይወት ይወጣል። 12በምዕራብ በኩል ባለች በሦስተኛዪቱ መስኮትም ከእርስዋ ጠልና ዝናም፥ ኩብኩባና ድምሳሴም ይወጣል። 13ስሙ ባሕር በሚባል በመስዕ በኩል ካሉ ነፋሶች በኋላ ከሦስቱ መስኮቶች ለአዜብ በምትቀርብ በምሥራቅ በኩል ባለች በሰባተኛዪቱ መስኮት ከእርስዋ ጠልና ዝናም፥ ኩብኩባና ድምሳሴም ይወጣል። 14በቀጥተኛዪቱ በመካከለኛዋ መስኮትም ከእርስዋ ዝናምና ጠል፥ ሕይወትና ሰላም ይወጣል። 15ለመስዕ በምትቀርብ በምዕራብ በኩል ባለች በሦስተኛዪቱ መስኮትም ከእርስዋ ጉምና ውርጭ፥ ዋግና ጠል፥ ዝናምና ኩብኩባም ይወጣል። 16በምዕራብ በኩል ካሉ ከእነዚህ ከአራቱ ነፋሳት በኋላ ለመስዕ በቀረበች በመጀመሪያዪቱ መስኮት ከእርስዋ ጠልና ዝናም፥ የረጋውና የተበተነው ውርጭ፥ ዋግና ቀቅም ይወጣል። 17ከመካከለኛዪቱ መስኮትም ጠልና ዝናም፥ ሰላምና በረከትም ይወጣል። 18በአዜብ በኩል ባለች በሁለተኛዪቱ መስኮትም ከእርስዋ ድርቅና ድምሳሴ፥ ዋዕይና ጥፋት ይወጣል። 19በአራቱ የሰማይ ማዕዘን ያሉ ዐሥራ ሁለቱ መስኮቶች ተፈጸሙ። ልጄ ማቱሳላ! ትእዛዛቸውን ሁሉና መቅሠፍታቸውን ሁሉ፥ ሰላማቸውንም ሁሉ አሳየሁህ። 20መጀመሪያ ነውና መጀመሪያውን ነፋስ ስሙን ጽባሓዊ ብለው ይጠሩታል። 21በዚያ ልዑል 22የሰማይ ብርሃናት ሁሉ በዚያ ይጐድላሉና፥ ወደዚያም ይወርዳሉና ከምዕራብ የሚነፍሰውንም ነፋስ ጐደሎ ብለው ይጠሩታል። 23ስሙ መስዕ የሚባል አራተኛው ነፋስ ከሦስት ይከፈላል፤ ከእነርሱም አንዱ ለሰው ማደሪያ ነው፤ ሁለተኛውም በውኃ ባሕሮችና በጥልቆች፥ በዛፍና በወንዞችም፥ በጨለማና በጉምም የተሾመ ነው። ሦስተኛውም ክፍል በጽድቅ ገነት የተሾመ ነው። 24በምድር ካሉ ተራሮች ሁሉ የሚረዝሙ ሰባት ረጃጅሞች ተራሮችንም አየሁ። 25ከእነርሱም ውርጭ ይወጣል፤ ቀኑም፥ ዘመኑም፥ ዓመቱም ያልፋል፥ ይሄዳልም። 26ከፈሳሾች ሁሉ የሚበልጡ ሰባት ፈሳሾችን በምድር ላይ አየሁ፤ ከእነርሱም አንዱ ከምዕራብ መጥቶ ሰፊ ወደ ሆነው ውቅያኖስ ውኃውን ያፈስሳል። 27እነዚያም ሁለቱ ከመስዕ እስከ ባሕር ድረስ መጥተው ውኃቸውን ከወደ ምሥራቅ በኤርትራ ባሕር ያፈስሳሉ። 28የቀሩትም አራቱ የእነርሱ ባሕር እስከሚሆነው እስከ ኤርትራ ባሕር ድረስ በመስዕ አጠገብ ይፈስሳሉ። 29ሁለቱ ፈሳሾችም ወደ ታላቁ ባሕር ይጨመራሉ፤ በዚያም ይከማቻሉ። 30በባሕርና በየብስ ሰባት ታላላቅ ደሴቶችን አየሁ፤ ከእነዚያም ሁለቱ በየብስ፥ አምስቱም በታላቁ ባሕር ናቸው።