1የወሮቹን መንገድ በሚያደርግበት በዚያ ትእዛዝ ሁለተኛ መሄጃውንና ትእዛዙን አየሁለት። 2የሁሉም መሪያቸው የሆነው ቅዱስ መልአክ ዑርኤል ሁሉን አሳየኝ፤ 3እንዳሳየኝም ቦታቸውን ጻፍሁ። 4ጸንተው እንደሚኖሩም ወራታቸውን ጻፍሁ፤ የብርሃናቸውንም መልክ ጻፍሁ። 5ዐሥራ አምስቱ ቀን እስኪፈጸም ድረስ በአንድ ቀን አንድ ሰባተኛ ክፍለ ብርሃን እየተቀበለ ብርሃኑን ሁሉ በምሥራቅ ፈጽሞ ያገኛል፤ አንድ ሰባተኛ ክፍለ ብርሃንም እየተነሣው ጨለማውን ሁሉ በምዕራብ ፈጽሞ ያገኛል። 6በታወቁም ወራቶች መግቢያዎቹን ይለውጣል፤ በታወቁም ወራቶች አንድ አንድ ክፍለ ብርሃን እየተሰጠው መንገዱን ይሄዳል። 7ጨረቃም በሕፀፁ በሁለቱ ከፀሐይ ጋር ይገባል፤ በመካከል ባሉ በእነዚያ በሁለቱ መስኮቶች በአራተኛዪቱና በሦስተኛዪቱ መስኮት ሰባት ቀን ይወጣል። 8ዳግመኛም ዙሮ ተመልሶ ፀሐይ በሚወጣበት መስኮት ይወጣል፤ በዚያም መስኮት ብርሃኑን ሁሉ ፈጽሞ ያገኛል። 9ከፀሐይም ይርቃል፤ ፀሐይ ከእርሷ በሚወጣባት በስድስተኛዪቱም መስኮት ስምንት ቀን ይገባል። 10ፀሐይም ከአራተኛዪቱ መስኮት በሚወጣ ጊዜ ከአምስተኛዪቱ መስኮት እስኪወጣ ድረስ በአራተኛዪቱ መስኮት ሰባት ቀን ይወጣል። 11ዳግመኛም ተመልሶ በአራተኛዪቱ መስኮት ሰባት ቀን ይወጣል፤ ብርሃኑንም ሁሉ ፈጽሞ ያገኛል። 12ይርቃል፥ በመጀመሪያዪቱም መስኮት ስምንት ቀን ይገባል፤ ዳግመኛም ተመልሶ ፀሐይ ከእርሷ በሚወጣባት በአራተኛዪቱ መስኮት ሰባት ቀን ይወጣል። 13በየወራታቸው ሥርዐት ፀሐይ እንደሚወጣና እንደሚገባ አኗኗራቸውን እንዲህ አየሁ። 14በእነዚያም ወራቶች አምስት ዓመት ይጨመራል፤ ለፀሐይም ሠላሳ ቀን ይደርሰዋል። 15ለአንዱ ዓመትም ቀኖች ሁሉ ይደርሱታል፤ ከእነዚህም ከአምስቱ ዓመታት ተውጣጥተው ቀኖቹ ሦስት መቶ ስሳ አራት ቀን ይሆናሉ። 16ለፀሐይና ለከዋክብትም ስድስት ቀን ይደርሳቸዋል፤ ከአምስቱ ዓመትም ስድስት ስድስት ቀን ወጥቶ ሠላሳ ቀን ይደርሳቸዋል። 17ጨረቃም ከፀሐይና ከከዋክብት ሠላሳ ቀን ይጐድላል። 18ጨረቃም ዓመታትን ጠንቅቆ ያስቈጥራቸዋል። 19ሁሉም ለዘለዓለም እንደሚኖሩ አንዲት ቀን አያተርፉም፤ አያጐድሉምም። ነገር ግን ሦስት መቶ ስድሳ አራት ቀን እየሆነ በጥንቃቄ በእውነት ዓመቱን ይለውጣሉ። 20የሦስቱ ዓመት ቀን ሺህ ዘጠና ሁለት ነው፤ የስምንቱ ዓመት ቀን ሁለት ሺህ ዘጠኝ መቶ ዐሥራ ሁለት ቀን ይሆን ዘንድ የአምስቱ ዓመት ቀን ሺህ ስምንት መቶ ሃያ ቀን ነው። 21ለጨረቃም ለብቻው ይደርሰዋል፤ የሦስቱም ዓመት ቀኑ ሺህ ስድሳ ሁለት ቀን ነው። 22በስድሳ ሁለቱ ቀን ላይ ወደ ላይ በመውጣቱ ለፀሐይ ቀን ይጨመርለታልና ጨረቃ ለአምስቱ ዓመት አምሳ ቀን ይጐድላል። 23ለጨረቃ የስምንቱ ዓመት ቀኑ ሁለት ሺህ ስምንት መቶ ሠላሳ ሁለት ቀን ይሆን ዘንድ የአምስቱ ዓመት ቀኑ ሺህ ሰባት መቶ ሰባ ቀን ይሆናል። 24በስምንቱ ዓመት የሚያንሰው ቀኑ ሰማንያ ቀን ነውና ከስምንቱም ዓመት የጐደለባቸው ቀኖች ሰማንያ ቀኖች ናቸው። 25እነርሱ እንደሚኖሩበት፥ ፀሐይም እንደሚኖርበት መጠን ዘመኑ እንዲህ በእውነት ይፈጸማል። 26ከዋክብት ከሚወጡባቸው መስኮቶች ፀሐይ ሠላሳ ቀን ይወጣል፥ ይገባልም።