1ከዚህ ሥርዐትም በኋላ ስሙ ጨረቃ የሚባል የታናሹን ብርሃን ሌላ ሥርዐት አየሁ። 2ክበቡም እንደ ሰማይ ክበብ ነው፤ የሚሔድበትንም ሠረገላ ነፋስ ይነዳዋል። 3ብርሃንም በመጠን ይሰጠዋል። 4በወሩም ሁሉ መውጫውና መግቢያው ይለወጣል፤ ቀኑም እንደ ፀሐይ ቀን ነው። 5የብርሃኑ ሁኔታ በተስተካከለም ጊዜ የብርሃኑ መጠን ከፀሐይ ብርሃን ሰባተኛ እጅ ይሆናል። 6እንደዚህም ይወጣል፤ ማጭድነቱም በሠላሳኛው ቀን ወደ ምሥራቅ ሆኖ ይወጣል። 7በዚያችም ቀን ይታያል፤ ለእናንተም ሠርቀ ወርኅ ይሆናል። 8በሠላሳኛው ቀን ሠርቅ ሊያደርግ በሃያ ዘጠነኛው ቀን ፀሐይ በሚወጣበት ደጃፍ ከፀሐይ ጋር ያድራል። 9ሰባተኛ ክፍለ ብርሃን የሚሣልበት እኩሌታው አንዱ ወገን ከብርሃን የራቀ ነው፤ ከዐሥራ አራት እጅ ብርሃን ተለይታ ሰባት ክፍለ ብርሃን ከሚሣልባት ከሰባተኛዪቱ እጅ በቀር ሰሌዳው ሁሉ ብርሃን የሌለበት ባዶ ነው። 10ከብርሃኑ እኩሌታ አንድ ሰባተኛ በሚቀበልበት ቀን ብርሃኑ የእኩሌታው አንድ ሰባተኛ ይሆናል። 11ከፀሐይም ጋር ይገባል፤ ፀሐይም በሚወጣ ጊዜ ጨረቃ ከእርሱ ጋር ይወጣል፤ የብርሃኑንም እጅ ዕኩሌታ ይቀበላል። 12ጨረቃ ሠርቅ ከሚያደርግበት ቀን አስቀድሞ በዚያች ሌሊት ጨረቃ ከፀሐይ ጋር ያድራል። 13በዚያችም ሌሊት ሰባተኛውና ስድስተኛው እጅ፥ እኩሌታዋም እጅ ጨለማ ይሆናል፤ በዚያችም ቀን ሰባተኛውን እጅ ፈጽሞ ተቀብሎ ይወጣል። 14ወጥቶም ከፀሐይ መውጫ ይርቃል፥ በቀረውም ቀኑ ሰባት ሰባት እጅ እየተቀበለ ያበራል።