1ልዑል በጌትነት በኖረ ጊዜ ለቅዱሳን የገለጠው የመሐላ ራስ የክስብኤል የስሙ ቍጥር ይህ ነው። 2ስሙም ቤቃ ይባላል፤ ይኸውም ቅዱስ ሚካኤልን እንዲህ አለው- “ያን የተሰወረ ስሙን ያውቁት ዘንድ የተሰወረውን ስም ግለጥላቸው። 3የተሰወረውንም ሁሉ ለሰው ልጆች ያሳዩ ከዚህ ስምና መሐላ የተነሣ እንዲንቀጠቀጡ በመሐላ ጊዜ ይጠሩት ዘንድ ግለጥላቸው። 4ኀይለኛ ነውና፥ የጸናም ነውና የዚህ መሐላ ኀይሉ ይህ ነው። 5ይህን አካዕ የተባለውንም ስም በቅዱስ ሚካኤል እጅ አኖረው። የዚህ ስም የተሰወሩ ምሥጢሮቹም እነዚህ ናቸው። በስሙም ጸኑ። 6በዚያም ስም ሰማይ ጸና፤ ያም ስም ዓለም ሳይፈጠር ነበር፤ እስከ ዘለዓለምም ይኖራል፥ ምድርም በእርሱ በውኃው ላይ ተመሠረተች። 7ከተራሮች ስውር ቦታዎች ውስጥ ከጥንት ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ የጣፈጡ ውኃዎች ይመነጫሉ። 8በዚያም ስም ባሕር ተፈጠረች፤ በተቈጣችም ጊዜ- ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ ከወሰንዋ እንዳታልፍ የአሸዋ መሠረት አኖረላት። 9በዚያም ስም ጥልቆች ሁሉ ጸንተው ቆሙ፤ ከጥንትም ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ ከቦታቸው አይናወጡም። 10በዚያም ስም ፀሐይና ጨረቃ ጎዳናቸውን ይጨርሳሉ፤ ከጥንት ጀምሮ እስከ ዘለዓለሙ ድረስ ከታዘዙት ትእዛዝ አያልፉም። 11በዚያም ስም ከዋክብት ጎዳናቸውን ይጨርሳሉ፤ ስማቸውንም ይጠራል፤ እነርሱም ከጥንት ጀምሮ እስከ ዘለዓለሙ ድረስ ይመልሱለታል። 12እንደዚሁም ለውኃዎች አካላት ሕይወታቸው ነፋሳት ናቸው፤ የሁሉም አካሎቻቸውና መተላለፊያዎቻቸው ከነፋሳት ኅብር ሁሉ ነው። 13በዚያም የነጐድጓድ የቃሉ መዛግብትና የመብረቅ ብርሃን ይጠበቃሉ። 14በዚያም የበረድና የውርጭ መዛግብት፥ የጉም መዛግብትና የዝናምና የጠል መዛግብትም ይጠበቃሉ። 15እነዚያም ሁሉ በመናፍስት ጌታ ፊት አምነው ያመሰግናሉ፤ በፍጹም ኀይላቸውም ያመሰግናሉ። 16ሁልጊዜም ምግባቸው ምስጋና ናት፤ ለዘለዓለም የሚኖር የመናፍስት ጌታ ስሙንም ያመሰግናሉ፤ ያከብራሉም፤ ከፍ ከፍም ያደርጋሉ። 17ይህም ስም በእነርሱ ላይ ጸና፤ በእርሱም ይጠበቃሉ፤ መንገዶቻቸውም ይጠበቃሉ፤ መተላለፊያዎቻቸውም አይጠፉም። 18ታላቅ ደስታም ሆነላቸው፤ የሰው ልጅ ስሙ ስለ ተገለጠላቸውም አመሰገኑ፤ አከበሩም፤ ከፍ ከፍም አደረጉ። 19በጌትነቱ ዙፋን ላይም ተቀመጠ፤ ለሰው ልጅም የፍርድ ሥልጣን ተሰጠው። 20ከገጸ ምድርም ኃጥኣንን ያሳልፋል፤ ያጠፋልም፤ ዓለምን ያሳቱም በሰንሰለት ይታሰራሉ። 21በጥፋት ማኅበራቸውም ይጋዛሉ፥ ሥራቸውም ሁሉ ከገጸ ምድር ያልፋል። 22ከእንግዲህ ወዲህም ፈርሶ በስብሶ የሚቀር የለም፤ ያ የሰው ልጅ ተገልጦ በጌትነቱ ዙፋን ተቀምጦአልና። ክፉ ነገርም ሁሉ ከፊቱ ይጠፋልና። 23ሄደውም ለዚያ ለሰው ልጅ ይነግሩታል፤ በመናፍስት ጌታ ፊትም ይጸናል፤ ሦስተኛው የሄኖክ ምሳሌ ይህ ነው። 24ከዚህ በኋላም እንዲህ ሆነ፤ በመናፍስት ጌታ ዘንድ የሰው ልጅ ሕያው ስሙ በምድር ላይ ከሚኖሩ ሰዎች ይልቅ ከፍ ከፍ አለ። 25በመንፈስ ሠረገላዎችም ከፍ ከፍ አለ፤ ስሙም በመካከላቸው ወጣ። 26ከዚያችም ቀን በኋላ በመካከላቸው አልተቈጠርሁም። 27ለተመረጡና ለጻድቃን ቦታን ይሰፍሩልኝ ዘንድ መላእክት ገመዶችን በተቀበሉበት በሁለቱ ማዕዘናት በመስዕና በምዕራብ መካከል አኖሩኝ። 28በዚያም ከጥንት ጀምሮ በዚያ ቦታ የሚኖሩ የቀደሙ አባቶችንና ጻድቃንን አየሁ። 29ከዚህም በኋላ እንዲህ ሆነ፤ ልቡናዬ ትራቀቅ ጀመረች፤ ከሰማያት በላይ ወዳለች ወደ ሰማይም ትወጣ ጀመረች። 30የቅዱሳን መላእክት ልጆችንም በእሳት ወላፈን ላይ ቁመው አየኋቸው። ቀሚሳቸውና መጐናጸፊያቸውም ነጭ ነው፤ የፊታቸውም ብርሃን እንደ በረዶ ነው። 31ሁለት የእሳት ፈሳሾችንም አየሁ፤ የዚያም እሳት ብርሃን እንደ ዕንቍ ያበራል፤ በመናፍስት ጌታ ፊትም በግንባሬ ወደቅሁ። 32ከመላእክት አለቆች አንዱ መልአክ ሚካኤል ቀኝ እጄን ይዞ አነሣኝ፤ ምሕረት ወደ አለበት፥ ጽድቅም ወደ አለበት የተሰወረ ቦታ አወጣኝ። 33በሰማይ ዳርቻ የተሰወሩትንም ሁሉ፥ የከዋክብትንና የብርሃናትንም መዛግብት ሁሉ በቅዱሳን ፊት ከሚወጡበት አሳየኝ። 34መንፈስም ሄኖክን ከሰማያት በላይ ባለ ሰማይ ሰወረው። 35በዚያም በብርሃን መካከል በዕንቍ የተሠራ ቤት እንዳለ አየሁ። 36በእነዚያም ድንጋዮች መካከል የሕያው እሳት ላንቃዎች አሉ። 37መንፈሴም እሳት የሚከበው የዚያን ቤት ዙሪያ አየች፤ በዚያም በአራቱ ማዕዘን ሕያው እሳትን የተመሉ ወንዞች አሉ። ያንም ቤት ይዞሩታል። 38ሱራፌልና ኪሩቤል፥ አፍኒንም በዙሪያው አሉ። እነዚህም የማያንቀላፉ ናቸው፥ የጌትነቱንም ዙፋን ይጠብቃሉ። 39የማይቈጠሩ ብዙ፥ የብዙ ብዙ የሚሆኑ መላእክትን አየሁ፥ ያንም ቤት ይከብቡታል። 40ሚካኤልና ገብርኤል፥ ሩፋኤልና ፋኑኤል፥ በሰማያት ያሉ ቅዱሳን መላእክትም በዚያ ቤት ይገቡና ይወጡ ነበር። 41ከዚያም ቤት ሚካኤልና ገብርኤል፥ ሩፋኤልና ፋኑኤል፥ ቍጥር የሌላቸው ብዙዎች ቅዱሳን መላእክትም ይወጡ ነበር። 42ብሉየ መዋዕልም ከእነርሱ ጋር አለ፤ ራሱም እንደ ባዘቶ ነጭ ነው፥ ንጹሕም ነው፤ ልብሱም የማይተረጐም ነው። 43እኔም በግንባሬ ወደቅሁ፥ ሥጋዬም ሁሉ ቀለጠ፥ አእምሮዬም ተለወጠ። 44በታላቅ ቃልና በኀይል መንፈስም ጮህሁ፥ አመሰገንሁ፥ አከበርሁ፥ ከፍ ከፍም አደረግሁ። 45ከአፌ የወጡ እኒህ ምስጋናዎችም በዚያ ብሉየ መዋዕል ፊት የተወደዱ ሆኑ። 46ያም ብሉየ መዋዕል ከሚካኤልና ከገብርኤል፥ ከሩፋኤልና ከፋኑኤል፥ ቍጥር ከሌላቸው ብዙ፥ የብዙ ብዙ ከሚሆኑ መላእክትም ጋር መጣ። 47ያም መልአክ ወደ እኔ መጣ፥ በቃሉም ሰላም አለኝ። 48እንዲህም አለኝ- “ለእውነት የተወለድህ የሰው ልጅ አንተ ነህ፤ ጽድቅም በአንተ አደረ፤ የብሉየ መዋዕል ቸርነትም አይለይህም።” 49እንዲህም አለኝ- “ከጥንት ጀምሮ ሰላም በዚያ ተገኝትWaልና፥ ለዘለዓለም የሚሆን ሰላምን በስሙ ይጠራልሃል። 50እንደዚሁም ለዓለም፥ ለዘለዓለም ይሆንልሃል፥ ሁሉም ይደረግልሃል፤ ጽድቅም ለዘለዓለም ሳይለይህ ሁሉ በመንገድህ ይሄዳል። 51ማደሪያቸውም ከአንተ ጋር ይሆናል፥ ዕድል ፋንታቸውም ከአንተ ጋር ነው፤ ከአንተም ለዓለም ለዘለዓለም አይለዩም። 52እንደዚህም ከዚያ የሰው ልጅ ጋር ብዙ ዘመን ይሆናል። 53ለጻድቃንም ሰላም ይሆናል፤ መንገዱም በመናፍስት ጌታ ስም ለጻድቃን ለዘለዓለም የቀና ነው።”