1ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ በአለበት በላይ ያለውን ሹ። 2የላይኛውን አስቡ፤ በምድር ያለውንም አይደለም። 3እናንተ ፈጽማችሁ ሞታችኋልና፤ ሕይወታችሁም ከክርስቶስ ጋራ በእግዚአብሔር ዘንድ የተሠወረች ናትና። 4ሕይወታችሁ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ፥ ያንጊዜ ከእርሱ ጋር በፍጹም ክብር ትገለጣላችሁ። 5ምድራዊ ሰውነታችሁንም ከዝሙትና ከርኵሰት፥ ከጥፋትና ከክፉ ምኞት፥ ጣዖት ማምለክ ከሆነው ከቅሚያም ግደሉት። 6በእነርሱም ምክንያት በማይታዘዙ ልጆች ላይ የእግዚአብሔር መቅሠፍት ይመጣል። 7እናንተም ቀድሞ በዚህ ሥራ በነበራችሁ ጊዜ የሄዳችሁበት ነው። 8አሁንም ቍጣንና ብስጭትን፥ ክፋትንና ስድብን፥ የሚያሳፍረውንም ነገር ተዉ፤ ከንቱ ነገርም ከአፋችሁ አይውጣ። 9አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ተዉት እንጂ፤ ወንድሞቻችሁን አቷሹ። 10ፈጣሪውን ለመምሰል በዕውቀት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ልበሱት። 11በእርሱ ዘንድ አይሁዳዊ፥ ግሪካዊም፥ የተገዘረ፥ ያልተገዘረም፥ አረመኔም፥ ባላገርም፥ ቤተ ሰብእና አሳዳሪ ማለት የለም ነገር ግን ክርስቶስ ለሁሉ በሁሉም ዘንድ ነው። 12እንግዲህ እግዚአብሔር እንደ መረጣቸው ቅዱሳንና ወዳጆች፥ ምሕረትንና ርኅራኄን፥ ቸርነትንና ትሕትናን፥ የውሀትንና ትዕግሥትን ልበሱት። 13ባልንጀሮቻችሁን ታገሡአቸው፤ እርስ በርሳችሁ ይቅር ተባባሉ፤ ባልንጀሮቻችሁን የነቀፋችሁበትን ሥራ ተዉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም እንዲሁ አድርጉ። 14ከዚህም ሁሉ ጋር ዘወትር ተፋቀሩ፤ የመጨረሻው ማሰሪያ እርሱ ነውና። 15በአንድ አካል የተጠራችሁለት የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ጸንቶ ይኑር፤ ክርስቶስንም በማመስገን ኑሩ። 16በጥበብ ሁሉ እንድትበለጽጉ የእግዚአብሔር ቃል በእናንተ ዘንድ ይጽና፤ በመንፈስም ራሳችሁን አስተምሩ፤ ገሥፁ፤ መዝሙርንና ምስጋናን፥ የቅድስና ማሕሌትንም በልባችሁ በጸጋ ለእግዚአብሔር ዘምሩ። 17በቃልም ቢሆን፥ ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አድርጉ፤ ስለ እርሱም እግዚአብሔር አብን አመስግኑት።
ስለ ቤተ ሰብእ አስተዳደር
18ሚስቶች ሆይ ለእግዚአብሔር እንደምትታዘዙ ለባሎቻችሁ ታዘዙ። 19ባሎች ሆይ ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ አትንቀፉአቸውም። 20ልጆች ሆይ ለወላጆቻችሁ በሁሉ ታዘዙ፤ እንዲህ ማድረግ ይገባልና፤ ይህም እግዚአብሔርን ደስ ያሰኛልና። 21አባቶች ሆይ እንዳያዝኑ ልጆቻችሁን አታበሳጩ። 22አገልጋዮች ሆይ በቅን ልብ እግዚአብሔርን በመፍራት እንጂ ለሰው ደስ እንደምታሰኙ ለታይታ የምትገዙ ሳትሆኑ፥ በሥጋ ጌቶቻችሁ ለሆኑ በሁሉ ታዘዙ። 23ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉ የምታደርጉትን ሁሉ ከልብ አድርጉት። 24ከእግዚአብሔር ዋጋችሁን እንደምትቀበሉ ታውቃላችሁ፤ ለክርስቶስ ትገዛላችሁና፤ 25የሚበድል ግን ፍዳውን ያገኛል፤ እርሱም አያደላለትም።