1ስለ እናንተ እና በሎዶቅያ ስላሉ፥ ፊቴንም በሥጋ ስላላዩት ምእመናን ሁሉ ምን ያህል እንደምጋደል ልታውቁ እወዳለሁ። 2ይኸውም ልቡናቸው ደስ ይለው ዘንድ፥ ትምህርታቸውም በማወቅ፥ በፍቅርና ፍጹምነት ባለው ባለጸግነት፥ በጥበብና በሃይማኖት፥ ስለ ክርስቶስም የሆነውን የእግዚአብሔርን ምክር በማወቅ ይጸና ዘንድ ነው። 3የተሰወረ የጥበብና የምክር መዝገብ ሁሉ በእርሱ ዘንድ አለ። 4ይህንም የምላችሁ በሚያባብል ነገር የሚያስታችሁ እንዳይኖር ነው። 5እኔ በሥጋ ከእናንተ ዘንድ ባልኖርም እንኳን፥ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝ፤ እነሆ ጠባያችሁንና ሥርዐታችሁን፥ በክርስቶስም ያለ የእምነታችሁን ጽናት ስለ አየሁ ደስ ይለኛል። 6እንግዲህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ተቀበላችሁት፥ በእርሱ ተመላለሱ። 7በእርሱ ተመሥርታችሁ ታነጹ፤ በምስጋናው ትበዙ ዘንድ፥ በተማራችሁት ሃይማኖት ጽኑ። 8ለዚህ ዓለም ስሕተት፥ በክርስቶስ ሕግ ያይደለ፥ በሰው ሠራሽ ሥርዐት ለከንቱ የሚያታልሉ ሰዎች በነገር ማራቀቅ እንዳያታልሉአችሁ፥ ተጠንቀቁ። 9በእርሱ ፍጹም መለኮቱ በሥጋ ተገልጦ ይኖራልና። 10እናንተም በእርሱ ፍጹማን ሁኑ፤ እርሱ ለአለቅነት ሁሉና ለሥልጣን ሁሉ ራስ ነውና። 11የኀጢአትን ሰውነት ሸለፈት በመግፈፍ በክርስቶስ መገረዝ በሰው እጅ የአልተደረገ መገረዝን በእርሱ ሆናችሁ ተገረዛችሁ። 12በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችኋል፤ በእርስዋም ከሙታን ለይቶ ባስነሣው በእግዚአብሔር ረዳትነትና በሃይማኖት ከእርሱ ጋር ተነሥታችኋል። 13እናንተም በኀጢአታችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን ነበራችሁና፥ ከእርሱ ጋር ሕያዋን አደረጋችሁ፤ ኀጢአታችሁንም ሁሉ ይቅር አላችሁ። 14ከባላጋራችን የተነሣ በትእዛዝ የተጻፈውን የዕዳችንን ደብዳቤ ደመሰሰልን፤ ከመካከላችንም አራቀው፤ በመስቀሉም ቸነከረው። 15አለቆችንና ገዢዎችን በመግፈፉ በግልጥ አሳያቸው፤ ራቁቱን በመሆኑም አሳፈራቸው። 16እንግዲህ በመብልም ቢሆን፥ በመጠጥም ቢሆን፥ በልዩ ልዩ በዓላትም ቢሆን፥ በመባቻም ቢሆን፥ በሰንበትም ቢሆን የሚነቅፋችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ። 17ይህ ሁሉ ይመጣ ዘንድ ላለው ጥላ ነውና። አካሉ ግን የክርስቶስ ነው። 18በመታለልና ራስን ዝቅ በማድረግ ለመላእክት አምልኮ ትታዘዙ ዘንድ ወድዶ፥ በአላየውም በከንቱ የሥጋው ምክር እየተመካ የሚያሰንፋችሁ አይኑር። 19ሥጋ ሁሉ ጸንቶ በሚኖርበት፥ በሥርና በጅማትም በሚስማማበት፥ በእግዚአብሔርም በሚያድግበትና በሚጸናበት፥ በሚሞላበትም በራስ አይጸናም።