ወደ ቆላስይስ ሰዎች 4
1ጌቶች ሆይ፥ ለአገልጋዮቻችሁ ትክክለኛውን አድርጉላቸው፤ እውነትንም ፍረዱ፤ በሰማይ ጌታ እንዳላችሁ ታውቃላችሁና።
ስለ ወንጌል መስፋፋት መጸለይ እንደሚገባ
2በምስጋና እየተጋችሁ ለጸሎት ፅሙዳን ሁኑ። 3ስለ እርሱ የታሰርሁለትን የእግዚአብሔርን ምሥጢር እንድንናገር፥ እግዚአብሔር የቃሉን በር ይከፍትልን ዘንድ ለእኛም ደግሞ ጸልዩልን፤ ለምኑልንም፤ 4ልናገርም እንደሚገባኝ እገልጠው ዘንድ ጸልዩልኝ። 5ዘመኑን እየዋጃችሁ ከሃይማኖት ወደ ተለዩ ሰዎች በማስተዋል ሂዱ። 6ለእያንዳንዱ እንዴት እንደምትመልሱ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ በጨው እንደ ተቀመመ በጸጋ ይሁን።
የመምህሩ ዜና በደቀ መዝሙሩ
7የተወደደ ወንድማችንና የታመነ አገልጋይ፥ በጌታ ሥራም ተባባሪያችን የሆነ ቲኪቆስ የእኔን ዜና ይነግራችኋል። 8ስለዚህ ሥራ ወደ እናንተ የላክሁት ዜናዬን ታውቁ ዘንድ፥ ልባችሁንም ያጽናና ዘንድ ነው። 9ወገናችሁ ከሆነው ከምንወደውና ከታመነው ወንድማችን ከአናሲሞስ ጋር፥ እነርሱ ሥራችንንና ያለንበትን ያስረዱአችኋል።
ሰላምታ ለደቀ መዛሙርት
10ከእኔ ጋር የተማረከው አርስጥሮኮስ፥ ወደ እናንተ በሚመጣ ጊዜ ትቀበሉት ዘንድ ስለ እርሱ ያዘዝኋችሁ የበርናባስ የአባቱ ወንድም ልጅ ማርቆስም፥ 11ኢዮስጦስ የተባለ ኢያሱም፥ ከግዙራን ሰዎች ወገን የሚሆኑ እነዚህ ሰላም ይሏችኋል። በእግዚአብሔር መንግሥት ሥራ ረዳቶች እነዚህ ብቻ ናቸው፤ እነርሱም እኔን አጽናንተውኛል። 12ከእናንተ ወገን የሚሆን ኤጳፍራስም ሰላም ይላችኋል፥ እርሱ የክርስቶስ አገልጋይ ነው፤ እግዚአብሔር በሚወደው ነገር ሁሉ ምሉኣንና ፍጹማን እንድትሆኑ፥ ስለ እናንተ ዘወትር ይጸልያል፤ ይማልዳልም። 13እጅግ እንደሚወዳችሁና ስለ እናንተ በሎዶቅያና በኢያራ ከተማ ስላሉትም እንደሚቈረቈር እኔ ምስክሩ ነኝ። 14ወዳጃችን ባለ መድኃኒቱ ሉቃስም ሰላም ብሎአችኋል፤ ዴማስም ሰላም ይላችኋል። 15በሎዶቅያ ላሉት ወንድሞቻችንና ለንምፋን፥ በቤቱም ላለች ቤተ ክርስቲያን ሰላምታ አቅርቡልኝ። 16ይህችን መልእክት እናንተ አንብባችሁ፥ በቤተ ክርስቲያን ያነብቡአት ዘንድ ወደ ሎዶቅያ ላኩአት፤ ዳግመኛም እናንተ ከሎዶቅያ የጻፍኋትን መልእክት አንብቡአት። 17አክርጳንም “ከእግዚአብሔር የተሾምህባትን መልእክትህን እንድትፈጽማት ተጠንቀቅ” በሉት። 18እኔ ጳውሎስ በእጄ ጽፌ ሰላም አልኋችሁ፤ እስራቴን አስቡ፤ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን፤ አሜን።