መጽሐፈ ጦቢት 8
የጋኔኑ ከሣራ መውጣት
1ተመግበውም በጨረሱ ጊዜ ጦብያን ወደ እርሷ አገቡት። 2ወደ እርሷም በገባ ጊዜ የሩፋኤልን ነገር አሰበ፤ የዕጣን ዕራሪ ወሰደ፤ ከዚያም ዓሣ ከልቡና ከጉበቱ ጨምሮ አጤሰው። 3ሽታውም ያን ጋኔን በሸተተው ጊዜ እስከ ላይኛው ግብፅ አውራጃ ድረስ ሸሸ። ያም መልአክ ጋኔኑን አሰረው።
የጦብያ ጸሎት
4ሁለቱም በተዘጋባቸው ጊዜ ጦብያ ከአልጋው ተነሥቶ፥ “እኅቴ ተነሽ፤ እግዚአብሔር ይቅር ይለን ዘንድ እንጸልይ” አላት። 5ጦብያም እንዲህ ይል ጀመረ፥ “አቤቱ የአባቶቻችን አምላክ አንተ ቡሩክ ነህ፤ ቅዱስ ስምህም ይባረክ፤ ለዘለዓለሙም ይመሰገናል። ሰማያትና የፈጠርሃቸው ሁሉ ያመሰግኑሃል። 6አንተ አባታችን አዳምን ፈጠርኸው፤ ትረዳውና ታሳርፈውም ዘንድ ሔዋንን ሰጠኸው፤ ከእነዚያም የሰው ዘር ተወለደ፤ አንተም አልህ፦ ‘ሰው ብቻውን ይኖር ዘንድ መልካም አይደለምና የሚረዳውን እንፍጠርለት።’ 7አሁንም ይህቺን እኅቴን የማገባት በሚገባ ነው እንጂ ስለ ዝሙት አይደለምና አቤቱ አብረን ወደ ሽምግልና እንድንደርስ እንረዳዳ ዘንድ ለእኔና ለእርሷ ይቅርታን ላክልን።” 8እርሷም ከእርሱ ጋር “አሜን” አለች። 9ሁለቱም በዚያች ሌሊት አብረው አደሩ። 10ከዚህም በኋላ ራጉኤል ተነሥቶ ሄደ፤ እርሱም “ምናልባት ይሞት ይሆናል” ብሎ መቃብር ቈፈረ። 11ራጉኤልም ወደ ቤቱ ተመለሰ። 12ሚስቱ አድናንም አላት፥ “ደኅና እንደ ሆነ ታየው ዘንድ አንዲት ልጅ ላኪ፤ ሞቶም እንደ ሆነ ማንም ሳያውቅ እንቀብረዋለን።” 13ያቺም ልጅ ሄዳ ደጃፉን ከፈተች፤ ሁለቱም ተኝተው አገኘቻቸው። 14ተመልሳም እርሱ ደኅና እንደ ሆነ ነገረቻቸው። 15ራጉኤልም እግዚአብሔርን አመሰገነው፤ እንዲህም አለ፥ “አቤቱ አንተ የተመሰገንህ ነህ፤ ንጽሕትና ቅድስት በሆነች ምስጋና ሁሉ የተመሰገንህ ነህ። ጻድቃንህ፦ በሠራኸው ሥራ ሁሉ ያመሰግኑሃል፤ መላእክትህና የመረጥኻቸውም ሁሉ ለዘለዓለም ያመሰግኑሃል። 16ደስ አሰኝተኸኛልና አቤቱ አንተ የተመሰገንህ ነህ፤ እንደ ጠረጠርሁት አልተደረገብኝም፤ ነገር ግን እንደ ቸርነትህ ብዛት አደረግህልኝ። 17አንተ ቡሩክ ነህ፤ ሁለቱን ብቸኞች ይቅር ብለሃቸዋልና፥ ዘመናቸውን በደኅንነትና በደስታ፥ በቸርነትህ ይፈጽሙ ዘንድ አቤቱ በጎነትን አድርገህላቸዋልና።” 18ከዚያም በኋላ ራጉኤል ያን መቃብር ይደፍኑ ዘንድ አገልጋዮቹን አዘዛቸው።
የሰርጉ በዓል
19ከዚህም በኋላ ዐሥራ አራት ቀን በዓል አደረገላቸው። 20ራጉኤልም የሠርጉ ዐሥራ አራት የበዓል ቀን እስኪፈጸም ድረስ ወጥቶ እንዳይሄድ ጦብያን አማለው። 21ከዚህም በኋላ ሄዶ የገንዘቡን እኩሌታ ይወስድ ዘንድ፥ ወደ አባቱም በደኅና ይሄድ ዘንድ፥ የተረፈውን ግን እርሱና ሚስቱ ከሞቱ በኋላ ይወስድ ዘንድ አስማለው።