መልአኩና ጦብያ ወደ ራጉኤል ቤት እንደ ደረሱ
1ወደ ራጉኤልም ቤት ደረሱ፤ ሣራም ተቀብላ ደስ አሰኘቻቸው፤ እንዲሁ እነርሱም እርሷን ደስ አሰኙአት፤ ወደ ቤትም አስገባቻቸው። 2ራጉኤልም ሚስቱ አድናን፥ “ይህ ልጅ ድንቅ ነው፤ ከዘመዶች ወገን የሆነ ጦቢትን ይመስለዋል” አላት። 3ራጉኤልም፥ “ወንድሞቻችን! እናንተ ከወዴት ናችሁ?” አላቸው፤ እነርሱም፥ “ወደ ነነዌ ከተማረኩት ከንፍታሌም ልጆች ነን” አሉት። 4ራጉኤልም፥ “ወንድሜ ጦቢትን ታውቁታላችሁን?” አላቸው፤ እነርሱም፥ “እናውቀዋለን” አሉት። እርሱም፥ “በሕይወት አለን? ደኅና ነውን?” አላቸው። 5እነርሱም፥ “አዎ ደኅና ነው” አሉት፤ ጦብያም፥ “አባቴ ነው” አለው። 6ራጉኤልም ተነሥቶ ሳመው፤ አለቀሰም። 7“አንተ የደግ ሰው ልጅ ነህ” ብሎ መረቀው፤ የጦቢትም ዐይኖች እንደ ጠፉ ነገረው። የጦቢትም ዐይኖች እንደ ጠፉ በሰማ ጊዜ አዝኖ አለቀሰ። 8ሚስቱ አድናና ልጁ ሣራም አለቀሱ፤ በደስታም ተቀበሉዋቸው፤ በግ አርደውም፥ ማዕድ አቀረቡላቸው፤ እጅግም መሸ። ጦብያም አዛርያን፥ “አንተ ወንድሜ አዛርያ በጎዳና ያልኸኝን ነገር ተናገር፤ ነገሩም ይለቅ፥” አለው። 9ራጉኤልም ጦብያ መልአኩን እንደሚያነጋግረው ሰምቶ ጦብያን አነጋገረው፦ እንዲህም አለው፥ “አንድ ጊዜ ብላ፤ ጠጣ፤ ደስም ይበልህ፤ 10ልጄ ለአንተ ትገባለችና፥ አንተም ታገባታለህና። 11እኔም እውነቱን እነግርሃለሁ፤ ይህችን ልጄን ለሰባት ወንዶች አጋባኋት፤ ወደ እርሷም እንደ ገቡ በሌሊት ይሞታሉ፤ ነገር ግን አንድ ጊዜ ደስ ይበልህ፤” ጦብያም፥ “ነገሩን ለኔ እስክትጨርሱልኝ ድረስ፥ ነገሬንም እስክታጸኑልኝ ድረስ በዚህ ምንም አልቀምስም” አለ። 12ራጉኤልም አለው፥ “ከአሁን ጀምሮ እንደ ሥርዐቱ ውሰዳት፤ አንተ ወንድሟ ነህና፥ እርሷም እኅትህ ናትና፤ ይቅር ባይ እግዚአብሔርም የሚበጀውን ያከናውንላችሁ።” 13ልጁ ሣራንም ጠራት፤ እጅዋንም ይዞ ሚስት ልትሆነው ለጦብያ ሰጣት፤ “እነሆ በሙሴ ሥርዐት ውሰዳት፤ ወደ አባትህም ቤት አግባት” ብሎ መረቃቸው። 14ሚስቱ አድናንም ጠራት፤ ወረቀትም ወስዶ ጻፈና አተማት። 15ከዚህም በኋላ ይበሉ ጀመሩ። 16አድናንም ጠርቶ፥ “አንቺ እኅቴ ሌላ የጫጕላ ቤት አዘጋጂ፤ ወደዚያም አግቢያት” አላት። 17እንዳላትም አደረገች፤ ወደዚያም አገባቻት፤ አለቀሰችም፤ የልጅዋንም እንባ ጠረገች። 18“ስለዚች ኀዘንሽ ፋንታ የሰማይና የምድር ጌታ ደስታን እንደሚሰጥሽ እመኝ” አለቻት።