መልአኩና ጦብያ ወደ ጤግሮስ ወንዝ እንደ ደረሱና ዓሣ እንደ ያዙ
1በመንገዳቸውም ሲሄዱ ወደ ጤግሮስ ወንዝ ማታ ደረሱ፤ በዚያም አደሩ። 2ያም ልጅ ሊታጠብ ወረደ፤ ከውኃውም ውስጥ ዓሣ ወጥቶ ተወረወረ፤ ያንም ልጅ ይውጠው ዘንድ ወደደ። 3መልአኩም፥ “ያን ዓሣ ያዘው” አለው፤ ያም ልጅ ዓሣውን ያዘው፤ ወደ የብስም አወጣው። 4ያም መልአክ፥ “ዓሣውን እረደው፤ ልቡንና ጉበቱን፥ ሐሞቱንም ያዝ፤ አጥብቀህም ጠብቅ” አለው። 5ያም ልጅ መልአኩ እንዳዘዘው አደረገ፤ ዓሣውንም ጠብሰው በሉ፤ ሁለቱም ገሥግሠው ሄደው፥ ወደ በጣኔስ ደረሱ። 6ያም ልጅ መልአኩን አለው፥ “አንተ ወንድሜ አዛርያ! የዚህ ዓሣ ልቡ፥ ጉበቱና ሐሞቱ ለምንድን ነው?” 7መልአኩም አለው፥ “ልቡና ጉበቱ፦ የሚያሳምም ክፉ ጋኔን ያደረበት ቢኖር፥ ወይም ርኩስ መንፈስ ያደረበት ቢኖር ያን ለዚያ ሰው በፊቱ ያጤሱለታል፤ ሴትም ብትሆን ያጤሱላታል፤ ከዚያም በኋላ አይታመሙም። 8ሐሞቱን ግን በዐይኑ ላይ ብልዝ ያለበትን ሰው ይኩሉታል፤ እርሱም ይድናል።” 9ወደ ራጊስም በቀረቡ ጊዜ፥ 10መልአኩ አለው፥ “አንተ ወንድሜ! ዛሬ በራጉኤል ቤት እናድራለን፤ እርሱም ዘመድህ ነው፤ አንዲት ልጅም አለችው፤ ስሟም ሳራ ይባላል፤ ሚስት ትሆንህ ዘንድ እንዲሰጥህ ስለ እርስዋ እናገራለሁ፤ ለአንተ ውርሷ ይደርስሃልና። 11ከዘመዶችዋም ወገን አንተ አለህ፤ ልጂቱም ደግና ልባም ናት። 12አሁንም ስማኝ፤ ለአባትዋም እነግረዋለሁ፤ ከራጊስም በተመለስን ጊዜ የሠርግ በዓል እናደርጋለን፤ ራጉኤል፦ በሙሴ ሕግ መሠረት ለሌላ ሰው ይሰጣት ዘንድ አይወድድምና፥ ብትሞትም በወደደ ነበር፤ከሰው ሁሉ ይልቅ ውርሷ ላንተ ይደርስሃልና።” 13ያም ልጅ መልአኩን አለው፥ “አንተ ወንድሜ አዛርያ! ያቺን ልጅ ለሰባት ወንዶች እንዳጋቧት እኔ ሰምቻለሁ፤ ሁሉም በሠርጉ ጊዜ ሞቱ። 14አሁንም እኔ ላባቴ ብቸኛ ነኝ፤ ወደ እርሷም በገባሁ ጊዜ እንዳልሞት ፥ ያባቴንና የናቴንም ሕይወት በእኔ ምክንያት በጭንቅ ወደ መቃብር እንዳላወርድ እፈራለሁ፤ የሚቀብራቸውም ሌላ ልጅ የላቸውምና።” 15ያም መልአክ አለው፥ “ከዘመዶችህ ሚስት ታገባ ዘንድ አባትህ ያዘዘህን ቃል አታስብምን? አሁንም አንተ ወንድሜ ስማኝ፤ የጋኔኑ ነገርስ አያሳዝንህ፤ በዚች ሌሊት ከዘመዶችህ ወገን እርሷ ሚስት ሆና ትሰጥሃለችና፤ 16ወደ ጫጕላ ቤትም በገባህ ጊዜ የዕጣን ዕራሪ ውሰድ፤ ከዚህም ዓሣ ከጉበቱና ከልቡ ጨምረህ አጢስበት። 17ጋኔኑም በሸተተው ጊዜ ይሸሻል፤ ለዘለዓለሙም አይመለስም። ወደ እርሷም በገባህ ጊዜ ሁለታችሁ ይቅር ባይ ወደ ሆነው ወደ እግዚአብሔር ጩኹ፤ እርሱም ያድናችኋል፤ ይቅርም ይላችኋል። እንግዲህ አትፍራ፤ ከጥንት ጀምሮ እርሷን አዘጋጅቶልሃልና፤ አንተም ታድናታለህ፤ እርሷም ካንተ ጋራ ትሄዳለች፤ ከእርሷም ልጆችን እንደምትወልድ እነግርሃለሁ፤” ጦብያም ይህን ሰምቶ አደነቀ፤ ልቡም ወደ እርሷ ተሳበ፤ ወደ ባጥናም ደረሱ።