መልአኩ ሩፋኤል ከጦብያ ጋር እንደ ሄደ
1ጦብያም መለሰ እንዲህም አለ፥ “አባቴ! ያዘዝኸኝን ሁሉ አደርጋለሁ። 2ነገር ግን ከማላውቀው ሰው ያን ብር መቀበል እንዴት እችላለሁ?” 3እርሱም ደብዳቤ ሰጠው፤ እንዲህም አለው፥ “ከአንተ ጋር የሚሄድ ሰው ፈልግ፤ እኔም በሕይወት ሳለሁ ደመወዙን እሰጠዋለሁ፤ ሄደህም ያንን ብር ተቀበል።” 4እርሱም ሰውን ሊፈልግ ሄዶ መልአኩን ሩፋኤልን አገኘው፤ ነገር ግን መልአክ እንደ ሆነ አላወቀም። 5እርሱም አለው፥ “ሀገሩን ታውቅ እንደ ሆነ ወደ ሜዶን ክፍል ወደ ራጊስ ከኔ ጋራ መሄድ ትችላለህን?” 6መልአኩም እንዲህ አለው፥ “ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፤ መንገዱንም ዐውቃለሁ፤ በገባኤልም ዘንድ ነበርሁ።” 7ጦብያም፥ “ላባቴ እስክነግረው ድረስ ቈየኝ” አለው። 8እርሱም፥ “ሂድ፤ አትቈይ” አለው፤ ለአባቱም፥ “ከእኔ ጋር የሚሄድ እነሆ አገኘሁ” አለው። እርሱም፥ “ከማን ወገን እንደ ሆነ፥ ካንተም ጋራ ለመሄድ የታመነ እንደ ሆነ ዐውቅ ዘንድ ወደ እኔ ጥራው” አለው። 9ጠራውና ገባ፤ እርስ በርሳቸውም እጅ ተነሣሡ። 10ጦቢትም፥ “አንተ ወንድሜ! ከማን ወገን ነህ? ከወዴትስ ሀገር ነህ?” አለው። 11መልአኩም፥ “ወገኔንና ሀገሬን ትመረምር? ወይስ ከልጅህ ጋራ የምሄድበትን ዋጋ ትሰጠኝ?” አለው። ጦቢትም፥ “አንተ ወንድሜ ዘመድህንና ስምህን ዐውቅ ዘንድ እወዳለሁ” አለው። 12እርሱም፥ “እኔስ የወንድምህ የታላቁ አናንያ ዘመድ አዛርያ ነኝ” አለው። 13ጦቢትም አለው፥ “አንተ ወንድሜ ደኅና ነህን? ወገንህንና ሀገርህን ዐውቅ ዘንድ መርምሬአለሁና አትንቀፈኝ፤ ነገር ግን አንተ በእውነቱ ከደግና ከተባረከ ወገን ነህ፤ እኔም የታላቁ የሴምዩን ልጆች አናንያንና ኢታያንን ዐውቃቸዋለሁ፤ እንሰግድ ዘንድ ከእነርሱ ጋር አብረን ወደ ኢየሩሳሌም ሄደን ነበር፤ በኵራቱንና የእህላችንን ዐሥራት ወስደን ነበር፤ ነገር ግን በአባቶቻችን በደል አልበደልንም። 14ወንድሜ አንተ ግን ከደግ ቤተ ሰብ ነህ፤ ነገር ግን ንገረኝ፤ ደመወዝህን ምን እንስጥህ? በየቀኑ አንድ ድራህማ እንስጥህን? ምግብህስ ከልጄ ጋር ይሁን? 15በደኅና ከተመለሳችሁ በደመወዝህ ላይ እጨምርልሃለሁ፤” እንደዚህም ጨረሱ። 16ጦብያንም አለው፥ “ትሄዱ ዘንድ፥ ትከናወኑም ዘንድ ተዘጋጁ።” ልጁም ለመንገድ ስንቃቸውን አዘጋጀ፤ አባቱም አለው፥ “ከዚህ ሰው ጋር ሂድ፤ በሰማያት የሚኖር እግዚአብሔር መንገዳችሁን ያቅናላችሁ፤ መልአኩም አብሮአችሁ ይሂድ፤” ሁለቱም ወጥተው ሄዱ፤ ሌላው ልጃቸውም ተከተላቸው። 17እናቱ ሐናም አለቀሰች፤ ጦቢትንም እንዲህ አለችው፥ “ልጄን ለምን ላክኸው? እርሱ በፊታችን የሚወጣና የሚገባ፥ በእጃችን ያለ ምርኩዛችን አይደለምን? 18ብሩስ ይጥፋ የልጄም ቤዛ ይሁን! 19የምንኖርበት እግዚአብሔር የሰጠን ይበቃናልና።” 20ጦቢትም አላት፥ “እኅቴ አትጨነቂ፤ በደኅና ይመለሳል፤ በዐይኖችሽም ታይዋለሽ። 21ቸር መልአክ በፊቱ ይሄዳልና፥ ጎዳናውንም ያቃናለታልና፥ በደኅናም ይመለሳልና።” 22ሐናም ልቅሶዋን ተወች።