ጦቢት ለልጁ የሰጠው ምክር
1በዚያችም ቀን ጦቢት በሜዶን ክፍል በራጌስ ለገባኤል አደራ ስላስጠበቀው ብር አሰበ። 2አስቦም እንዲህ አለ፥ “እነሆ ልሙት ብዬ ለመንሁ፤ እንግዲህ ልጄን ጦብያን ጠርቼ ሳልሞት የማልነግረው ለምንድን ነው?” 3ጠርቶም እንዲህ አለው፥ “ልጄ በሞትሁ ጊዜ በመልካሙ ቅበረኝ፤ እናትህንም ጠብቃት፤ በሕይወትህም ዘመን ሁሉ አክብራት፤ የወደደችውንም አድርግላት፤ አታሳዝናትም። 4ልጄ፥ በማኅፀን ባንተ ብዙ መከራ እንደ ተቀበለች አስብ፤ በሞተችም ጊዜ በእኔ ዘንድ ባንድ መቃብር ቅበራት። 5ልጄ ሆይ! በዘመኑ ሁሉ ፈጣሪህ እግዚአብሔርን አስበው፤ በደልንና ትእዛዙን መካድን አትውደድ፤ በሕይወትህም ዘመን ሁሉ ጽድቅን ሥራ፤ በዐመፅ መንገድም አትሂድ። 6ጽድቅን ከሠራሃት በመንገድህ ሁሉና በሠራኸው ሥራ ሁሉ ትከናወናለህ፤ ጽድቅንም ለሚሠሩዋት ሁሉ ይከናወንላቸዋል። 7ከገንዘብህ ምጽዋት ስጥ፤ ምጽዋትንም በምትመጸውት ጊዜ በገንዘብህ አትንፈግ፤ ከድኃም ፊትህን አትመልስ። እግዚአብሔርም ፊቱን ከአንተ አይመልስም። 8ባለህ መጠን የሚቻልህን ያህል ምጽዋት አድርግ። 9ጥቂትም ቢሆን ለመስጠት አትፈር፤ ምጽዋት መስጠት መልካም ድልብን ታደልብልሃለችና። 10ምጽዋት በመከራ ቀን ከሞት ታድናለችና፤ ወደ ጨለማም ከመሄድ ትጠብቅሃለችና። 11ምጽዋትም ለሚያደርጋት ሁሉ በልዑል ፊት መልካም ስጦታ ናት። 12“ልጄ! ራስህን ከዝሙት ጠብቅ፤ ከአባቶችህ ዘር ሁሉ አስቀድመህ ሚስት አግባ። ከዘመዶችህ ካልሆነች ከባዕድ ወገን ግን አታግባ። እኛ ከጥንት ጀምረው ከነበሩ ከነቢያት ከኖኅና ከአብርሃም ፥ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ልጆች ወገን ነንና፤ ልጄ ሆይ፥ ሁሉም ከአባቶቻቸው ትውልድ ሚስት እንዳገቡ አስብ፤ በልጆቻቸውም እንደ ተባረኩ፥ ዘሮቻቸውም ምድርን እንደ ወረሷት አስብ። 13አሁንም ልጄ ሆይ፥ ባልንጀራህን ውደድ፤ በባልንጀራህ፥ በወገኖችህ ወንዶች ልጆችና በወገኖችህ ሴቶች ልጆች ልብህን አታስታብይ፤ ከእነርሱም ወገን ሚስት አግባ። ትዕቢት ባለችበት ዘንድ ውርደት አለችና፥ ብዙ ሁከትም አለና፤ ስንፍናም ባለችበት ዘንድ ችግር አለች፤ ታላቅ ድህነትም አለ፤ ስንፍና የረኃብ እናት ናትና። 14የተገዛልህ ሁሉ ደመወዝ ባንተ ዘንድ አይደር፤ በጊዜው ስጠው እንጂ። ለእግዚአብሔር ብትገዛ ዋጋህ ይበዛልሃልና፤ ራስህን ዕወቅ፤ በሥራህና በጠባይህ ሁሉ ጠቢብ ሁን። 15ለራስህ የምትጠላውን ለማንም አታድርግ፤ ለመስከርም ወይንን አትጠጣ፤ ከሰካራሞችም ጋር በጎዳና አትሂድ። 16ከእህልህም ለተራበ፥ ከልብስህም ለተራቈተ ስጥ፤ ከተረፈህም ሁሉ ለምጽዋት አድርግ። 17እህልህንም በጻድቃን መቃብር ላይ ዝራ፤ ለኀጥኣን ግን አትስጥ። 18በጠቢባን ዘንድ ምክርን ፈልግ፤ የምትረባህንም ምክር አታቃል። 19በየጊዜውም ፈጣሪህ እግዚአብሔርን አመስግነው፤ ጎዳናህም የቀና ይሆን ዘንድ ወደ እርሱ ጸልይ፤ በሥራህ ሁሉና በጎዳናህ ሁሉ ያከናውንልሃል። በጎውን ሁሉ ከሚሰጥ ከእርሱ ከእግዚአብሔር በቀር ከእግዚአብሔር ያልሆነ አሕዛብ ሁሉ የሚመክሩት ምክር ከንቱ ነውና። የወደደውን ያዋርደዋል፤ እርሱም እንደ ወደደ ይሆናል። አሁንም ልጄ ሆይ ትእዛዜን አስብ፤ ከልብህም አይጥፋ።