የጦቢት ጸሎት
1ከዚህም በኋላ በልብ ጭንቀት ተከዝሁ፤ አልቅሼም ጸለይሁ። 2እንዲህም አልሁ፥ “አቤቱ በሥራህ ሁሉ በቸርነትና በፍርድ፥ በሚገባ ጽድቅም አንተ እውነተኛ ነህ፤ አቤቱ አንተ በሚገባ ዓለምን ትገዛለህ። 3አስበኝ፤ ተመልከተኝም፤ በራሴ ኀጢአትና አንተን በበደሉ፥ ትእዛዝህንም ባልሰሙ በአባቶች ኀጢአት አትበቀለኝ። 4ለመበርበርና ለመማረክ፥ ለመገደልም አደረግኸን፤ በዓለሙ ሁሉና በውስጣቸው በተበተንባቸው በአሕዛብም ዘንድ መተረቻና መዘባበቻ ሆንን። 5አሁንም እውነተኛ ፍርድህ ብዙ ነው፤ የእኔ ኀጢአትና የአባቶች ኀጢአትም እንዲሰረይ አድርግልኝ፤ ትእዛዝህን አላደረግንምና፥ በፊትህም በእውነት አልሄድንምና። 6አሁንም በፊትህ ደስ የሚያሰኝህን በእኔ አድርግ፤ ከመኖር መሞት ይሻለኛልና በሞት እሰናበት ዘንድ፥ መሬትም እሆን ዘንድ ነፍሴን የሚቀበላትን እዘዝልኝ። በሐሰትና በውርደት ተግዳሮትን ሰምቻለሁና፥ ኀዘንም በእኔ ላይ በዝትዋልና ከመከራዬ እሰናበት ዘንድ፥ ወደ ዘለዓለማዊ ቦታም እሄድ ዘንድ እዘዝ፤ ፊትህንም ከእኔ አትመልስ።” 7በዚያችም ቀን በሜዶን ክፍል በጣኔስ የራጉኤል ልጅ ሣራን ከአባትዋ ሴቶች አገልጋዮች ተግዳሮት አገኛት። 8ለሰባት ወንዶች አጋብተዋት እንደ ወንድና ሴት ሳይቃረቡ አስማንድዮስ የሚባል ክፉ ጋኔን ገድሏቸዋልና፤ እንዲህም አሏት፥ “ባሎችሽ እየታነቁ እንደሚሞቱ አታውቂምን፦ እነሆ ሰባቱ አገቡሽ፤ ከእነርሱም አንዱ ስንኳ አልተከተለሽም። 9እንግዲህ ስለ እነርሱ ምን አሳዘነን? እነርሱ ሞተዋልና ከእነርሱ ጋር ሂጂ፤ ከአንቺ ወንድ ወይም ሴት ልጅ እስከ ዘለዓለሙ ድረስ አንይ።” 10ይህንም በሰማች ጊዜ ለመታነቅ እስከምትመኝ ድረስ እጅግ አዘነች። እንዲህም አለች፥ “እኔ ለአባቴና ለእናቴ አንዲት ነኝ፤ እንደዚህም ባደርግ ተግዳሮት እሆንበታለሁ፤ ሽምግልናውንም፥ ሰውነቱንም በጭንቅ ወደ መቃብር አወርዳታለሁ።”
የሣራ ጸሎት
11በመስኮቱም በኩል ጸለየች፤ እንዲህም አለች፥ “አቤቱ አንተ ፈጣሪዬ ቡሩክ ነህ፤ ቅዱስና ክቡር ስምህም ለዘለዓለም ይመስገን፤ ሥራህም ሁሉ ለዘለዓለሙ ክቡር ነው። 12አቤቱ አሁንም ዐይኖችንና ፊቴን ለአንተ ሰጠሁ። 13እንግዲህ ወዲህ ተግዳሮትን እንዳልሰማ ከዚህ ዓለም አሰናብተኝ አልኹህ። 14ከወንድ ጋር ከሚሠራው ኀጢአት ሁሉ እኔ ንጽሕት እንደ ሆንኹ አቤቱ አንተ ታውቃለህ። 15በተማረክሁበትም ሀገር ስሜንና ያባቴን ስም አላሳደፍሁም፤ እኔም ለአባቴ አንዲት ነኝ። ወንድም የለኝም፤ ሚስት እሆንለት ዘንድ የምጠብቀው የቅርብ ዘመድም የለኝም፤ ሰባቱ ባሎች ሙተውብኛልና እንግዲህ ለምን እኖራለሁ? ልትገድለኝ ባትወድ ግን ወደ እኔ ተመልክተህ ራራልኝ፤ ተግዳሮትንም እንዳልሰማ እዘዝልኝ።” 16የሁለቱም ጸሎታቸው በእግዚአብሔር በገነነ ጌትነቱ ፊት ተሰማ። 17ሩፋኤልንም ላከው፤ ሁለቱን ያድናቸው ዘንድ፥ ከጦቢትም ዐይን ብልዙን ያጠፋለት ዘንድ፥ የራጉኤል ልጅ ሳራንም ሚስት ልትሆነው ለጦቢት ልጅ ለጦብያ ይሰጣት ዘንድ፥ ክፉ ጋኔን አስማንድዮስንም ይሽረው ዘንድ፥ ጦብያ ይወርሳታልና። በዚያም ወራት ጦቢት ተመልሶ ወደ ቤቱ ገባ፤ የራጉኤል ልጅ ሳራም ከሰገነቷ ወረደች።