1ወደ ሀገሬም በተመለስሁ ጊዜ ሚስቴን ሐናንና ልጄን ጦብያን መለሰልኝ። በሰባተኛው ሱባኤ በተቀደሰችው የበዓለ ኀምሳ ዕለት ለእኔ መልካም ነገር አደረጉልኝ፤ እበላም ዘንድ ተቀመጥሁ። 2ምግቡም እጅግ ብዙ እንደ ሆነ ባየሁ ጊዜ ልጄን እንዲህ አልሁት፥ “ሄደህ ከወንድሞቻችን ያገኘሃቸውን ድኆች ባልንጀሮችን አምጣ። እግዚአብሔርን አስቤዋለሁና። እነሆ እኔም እጠብቅሃለሁ።” 3በተመለሰ ጊዜም እንዲህ አለኝ፥ “አባቴ! ከወገኖቻችን የተገደለ አንድ ሰው አገኘሁ፤ ሬሳውም በገበያ ወድቆአል።” 4እኔም እህል ሳልቀምስ ተነሣሁ፤ ፀሐይም እስኪገባ ድረስ ወደ አንዱ ቤት አገባሁት። 5ወደ ቤቴም ተመልሼ ታጥቤ ምግቤን በኀዘን በላሁ። 6አሞፅም፥ “በዓላችሁ ወደ ኀዘን፥ ደስታችሁም ወደ ልቅሶ ይመለሳል” ያለውን አስታወስሁ። 7ከዚህም በኋላ አለቀስሁ፤ ፀሐይም በገባ ጊዜ ሄጄ መቃብር ቆፍሬ ቀበርሁት። 8ጎረቤቶችም ሳቁብኝ፤ እንዲህም አሉ፥ “ይህ ሰው ስለዚህ ሥራ እገደላለሁ ብሎ አይፈራምን? ንጉሥ የገደላቸውን ይቀብራልና።”
የጦቢት ዐይን እንዴት እንደ ታወረ
9በዚያችም ሌሊት ከቀብር ተመለስሁ፤ ረክሼም ስለነበር በዕድሞው ሥር አደርሁ፤ ዓይኖች ግን ተገልጠው ነበር። 10በዕድሞው ላይም ወፎች እንዳሉ አላወቅሁም፤ ፊቴም ተገልጦ ሳለ እነዚያ ወፎች በዐይኔ ላይ የሚያቃጥል ኩስ ጣሉብኝ፤ በዐይኔም ብልዝ ወጣብኝ፤ እኔም ወደ ባለ መድኀኒት ሄድሁ፥ ነገር ግን የጠቀመኝ የለም፤ ብቻዬን ወደ ኤልማድያ እስክሄድ ድረስ አኪአክሮስ ይመግበኝ ነበር። 11ሐናም በሴቶች ቤት ታገለግል ነበር። 12ወደ እመቤቶችዋም ላከች፤ እነርሱም ደመወዟን ሰጧት፤ የበግ ጠቦትም ጨመሩላት። 13ወደ እኔም በመጣች ጊዜ ትጮህ ጀመር፤ እኔም እንዲህ አልኋት፥ “ይቺ ጠቦት ከወዴት ናት? የሰረቅሻት ከሆነችም ወደ ጌቶችዋ መልሻት። የተሰረቀ መብላት አግባብ አይደለምና።” 14እርሷም አለችኝ፥ “በደመወዜ ላይ ሰጡኝ፤” እኔ ግን አላመንኋትም፤ ለባለቤቶቹም መልሺ ብዬ ከእርሷ ጋር ተከራከርሁ፤ እርሷም መልሳ፥ “ጸሎትህና ምጽዋትህ ወዴት ነው? እነሆ በላይህ ያለው ሁሉ ታወቀ” አለችኝ።