መጽሐፈ ጦቢት 1
1ከንፍታሌም ነገድ ከአሳሄል ወገን የገባኤል ልጅ የጦብኤል ልጅ የጦቢት የነገሩ መጽሓፍ ይህ ነው። 2እርሱም፦ ከአሴር በላይ ካለች ከገሊላ ንፍታሌም ክፍል ከቄዴዎስ በስተቀኝ ካለችው ከታስቢ በአሦር ንጉሥ በአሜኔሴር ዘመን የተማረከው ነው።
የጦቢት መልካም ሕይወት
3እኔ ጦቢት በሕይወቴ ዘመን በጽድቅና በቅንነት መንገድ ሄድሁ፤ ወደ አሶር ከተማ ወደ ነነዌ ከእኔ ጋር ለመጡ ወንድሞችና ወገኖች ብዙ ምጽዋትን አደረግሁ። 4እኔም ሕፃን ሆኜ ከእስራኤል ልጆች ጋር በሀገሬ ሳለሁ የአባቴ የንፍታሌም ወገኖች ሁሉ፥ እስራኤልም ሁሉ በእርሷ ይሠዉ ዘንድ እግዚአብሔር ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ከመረጣት የልዑል ቤተ መቅደስ ለትውልድ ሁሉ ለዘለዓለም ከታነጸባትና ከተቀደሰባት ከኢየሩሳሌም ወጥተው ካዱ። 5የካዱ ሰዎችም ሁሉ ደማሊ ለሚባል ጣዖት ሠዉ፤ የአባቴም የንፍታሌም ወገኖች ሁሉ ከእነርሱ ጋር ተባበሩ። 6እኔ ግን በዘለዓለማዊ ትእዛዝ ለእስራኤል ሁሉ እንደ ተጻፈ በበዓላት ቀን ብቻዬን ብዙ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም እሄድ ነበር፤ በመጀመሪያም ከሸለትሁት ከበጎች ፀጕር ለአሮን ልጆች ለካህናቱ ወደ መሠዊያው እወስድላቸው ነበር። 7እህሉንና መጀመሪያውን ዐሥራት ሁሉ በኢየሩሳሌም ለሚያገለግሉ ለአሮን ልጆች እሰጣቸው ነበር፤ ሁለተኛውን እጅ ዐሥራት ግን እሸጠው ነበር፤ ምጽዋቱንም አውጣጥቼ በየዓመቱ ወደ ኢየሩሳሌም እሄድ ነበር። 8ሦስተኛውንም እጅ ዐሥራት የአባቴ እናት ዲቦራ እንዳዘዘች ለድሆች እሰጥ ነበር። አባቴና እናቴ በድኃአደግነት ትተውኛልና፤ 9አካለ መጠን ባደረስሁም ጊዜ ከዘመዶች ዘር ሚስት አገባሁ፤ ከርስዋም ጦብያን ወለድሁ።
የጦቢት ወደ ነነዌ መማረክ
10ወንድሞችና ዘመዶች ሁሉ ወደ ነነዌ በተማረኩ ጊዜ ከአሕዛብ እህል በሉ። 11እኔ ግን የአሕዛብን እህል እንዳልበላ ሰውነቴን ጠበቅሁ፤ 12እግዚአብሔርን በፍጹም ልቡናዬ አስበዋለሁና። 13እግዚአብሔርም በአሜኔሴር ፊት ክብርንና ባለሟልነትን ሰጠኝ፤ እርሱም መጋቢ አድርጎ ሾመኝ። 14ወደ ምድያምም ሄድሁ፤ በምድያም ክፍል በራጊስ ያለ የጋብርያስ ወንድም ገባኤልንም ዐሥር መክሊት አደራ አስጠበቅሁት። 15አሚኔሴርም በሞተ ጊዜ በእርሱ ፋንታ ልጁ ሰናክሬም ነገሠ፤ ሥራውም ክፉ ነበር፤ ከሹመቴም ሻረኝ፤ እንግዲህም ወዲህ ወደ ምድያም መሄድን አልቻልሁም።
የጦቢት መልካም ሥራ
16በአሚኔሴርም ዘመን ለወንድሞች ብዙ ምጽዋትን አደረግሁ። 17እህሌንም ለተራቡ፥ ልብሴንም ለተራቆቱ ሰጠሁ። ከወገኖችም የሞተ ሰውን በነነዌ ግንብ ሥር ወድቆ ባየሁ ጊዜ እቀብረው ነበር። 18ንጉሥ ሰናክሬም ከይሁዳ ሸሽቶ በተመለሰ ጊዜ የገደላቸውን ሰዎች እኔ በስውር እቀብራቸው ነበር። እርሱ ተቈጥቶ ብዙዎችን ገድሎ ነበርና። ንጉሡም ሬሳቸውን አስፈለገ፥ አላገኘምም። 19ከነነዌ ሰዎችም አንዱ ሰው ሄዶ እንደ ቀበርኋቸው ነገር ሠርቶ ከንጉሡ ጋር አጣላኝ፤ እኔም ተሰወርሁ፤ ሊገድሉኝ እንደሚፈልጉኝም ባወቅሁ ጊዜ ፈርቼ ገለል አልሁ። 20ባጡኝም ጊዜ ገንዘቤን ሁሉ ዘረፉኝ፤ ከሚስቴ ሐናና ከልጄ ጦብያ በቀር ያስቀሩልኝ የለም። 21ሁለቱ ልጆቹ እስኪገድሉት ድረስ፥ ሸሽተውም ወደ አራራት ተራራ እስኪሄዱ ድረስ አምሳ አምስት ቀን ከቤቴ አልወጣሁም። ልጁ አስራዶንም በእርሱ ፋንታ ነገሠ፤ የወንድሜ ልጅ የአናሔል ልጅ አኪአኪሮስንም በአባቱ ቤት ሁሉና በሥራታቸው ሁሉ ላይ ሾመው። 22አኪአኪሮስም ማለደልኝ፤ ወደ ነነዌም መለሰኝ። አኪአኪሮስም የማኅተምና የቤቱ ንብረት ጠባቂ ነበር። አስራዶንም ዳግመኛ ሾመው።