ጦቢት ለእግዚአብሔር ያቀረበው ምስጋና
1ጦቢትም የደስታ መጽሐፍን ጻፈ፤ እንዲህም አለ፥ “ለዘለዓለሙ ሕያው የሚሆን፥ መንግሥቱም ለዘለዓለሙ የሆነ እግዚአብሔር ይመስገን። 2እርሱ ይገርፋል፤ ይቅርም ይላል፤ እርሱ ወደ ሲኦል ያወርዳል፤ ያወጣልም፤ ከእጁም የሚያመልጥ የለም። 3እናንተ የእስራኤል ልጆች ሁሉ፥ እርሱ በመካከላቸው በበተነን በአሕዛብ ሁሉ ፊት ተገዙለት። 4በዚያም ገናናነቱን ገለጠላችሁ፤ በሰው ሁሉ ፊትም አክብሩት፤ እርሱ ጌታችን ነውና፥ እርሱ እግዚአብሔር ለዘለዐለም አባታችን ነውና። 5በኀጢአታችን ይገርፈናል፤ ዳግመኛም ይቅር ይለናል፤ በመካከላቸው ከበተነን ከአሕዛብም ሁሉ ይሰበስበናል። 6“በፊቱ እውነትን ትሠሩ ዘንድ በፍጹም ልባችሁ፥ በፍጹም ነፍሳችሁም ወደ እርሱ ከተመለሳችሁ ያን ጊዜ እርሱ ወደ እናንተ ይመለሳል። ፊቱንም ከእናንተ አይሰውርም። ከእናንተ ጋር ያደረገውን ታያላችሁ። በፍጹም ልባችሁ፥ በፍጹም ነፍሳችሁም እመኑበት፤ ጻድቅ እግዚአብሔርን አመስግኑት፤ የዘለዓለምን ንጉሥ በተማረካችሁበት ሀገር ከፍ ከፍ አድርጉት፤ እኔም በተማረክሁበት ሀገር አምንበታለሁ፤ ኀጢአተኞች ለሆኑ ለአሕዛብም ኀይሉንና ገናናነቱን እናገራለሁ። እናንተ ኀጢአተኞች፥ ተመልሳችሁ በፊቱ እውነትን ሥሯት፤ ወድዶም ቸርነቱን ለእናንተ ያደርግላችሁ እንደ ሆነ ማን ያውቃል? 7ፈጣሪዬን ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ። ሰውነቴም የሰማይን ንጉሥ እግዚአብሔርን ታመሰግነዋለች። 8ገናናነቱንም በሁሉ ዘንድ እናገራለሁ። 9“ቅድስት ከተማ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ በልጆችሽ ኀጢአት በመከራ አይቀሥፍሽምን? ዳግመኛም ደጋግ ለሆኑ ልጆችሽ ይራራላቸዋል። 10በበጎ ሥራ ለእግዚአብሔር ተገዢ፤ ባንቺም ዘንድ ድንኳኑ በደስታ እንድትሠራ የዘለዓለሙን ንጉሥ አመስግኚ፤ በዚያም ያሉ የተማረኩ ሰዎች ደስ ይላቸዋል። በዘለዓለማዊ ትውልድም ሁሉ የተጠሉ በአንቺ ምክንያት ይወደዳሉ። 11“ብዙ አሕዛብ ከሩቅ ወደ ፈጣሪ እግዚአብሔር ስም ይመጣሉ፤ ለሰማይ ንጉሥም እጅ መንሻን ያመጣሉ፥ ትውልድም ሁሉ ያመሰግኑሃል፤ ለስምህም ምስጋናን ያቀርባሉ። 12የሚጠሉህ ሁሉ የተረገሙ ናቸው፤ የሚወድዱህ ሁሉ ግን ለዘለዓለሙ የተባረኩ ናቸው። 13በጻድቃን ልጆች ደስ ይልሃል፤ አቤቱ፥ በአንድነት ተሰብስበው የጻድቃንን ጌታ አንተን ያመሰግናሉና፥ የሚወድዱህ ብፁዓን ናቸውና፤ በሰላምህም ደስ ይላቸዋል። 14ስለ መከራህ የሚያዝኑ ሁሉ ብፁዓን ናቸው፤ ክብርህን ሁሉ አይተው በአንተ ደስ ይላቸዋልና፤ ለዘለዓለሙም ደስ ይላቸዋል። 15“ሰውነቴ ገናና ንጉሥ እግዚአብሔርን ታመሰግነዋለች። 16ኢየሩሳሌም ሰንፔር በሚባል ዕንቍ ትሠራለችና፥ ግድግዳዋ በመረግድና በከበረ ዕንቍ፥ አዳራሽዋና በሮችዋ በጠራ ወርቅ ይሠራሉና። 17የኢየሩሳሌም አደባባይም በቢሬሌ፥ በአትራኮስ ዕንቍና በሶፎር ዕንቍ ይሠራልና። 18በጎዳናዋ ሁሉ ሃሌ ሉያ ይላሉ፤ እያመሰገኑም እንዲህ ይላሉ፥ “እግዚአብሔር ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይመስገን።”