ለሩፋኤል የታሰበ የአገልግሎት ዋጋ
1ከዚህም በኋላ ጦቢት ጦብያን ጠርቶ፥“ ልጄ ሆይ፥ ከአንተ ጋራ የሄደ የዚህን ሰው ደመወዙን እይለት፤ ዳግመኛም ትጨምርለት ዘንድ ይገባል” አለው። 2ጦብያም አባቱን እንዲህ አለው፥ “ያመጣሁትን የገንዘቤን እኩሌታ ስንኳ ብሰጠው የሚጐዳኝ የለም። 3ወደ አንተ በደኅና መልሶኛልና፥ ሚስቴንም ፈውሷታልና፤ ብሩንም አምጥቶልኛልና፤ እንዲሁም አንተን ፈውሶሃልና።” 4አባቱም፥ “እውነት ተናገርህ” አለው። 5ያንም መልአክ ጠርቶ እንዲህ አለው፥ “ከእናንተ ጋር ካመጣችሁት ሁሉ እኩሌታውን ይዘህ በደኅና ሂድ።” 6ሩፋኤልም ያንጊዜ ሁለቱን ሁሉ ጠራቸው፤ ገለል አድርጎም እንዲህ አላቸው፥ “እግዚአብሔርን አመስግኑት፤ ለእርሱም ተገዙ፤ ለስሙም ምስጋና አቅርቡ፤ ስላደረገላችሁም በጎ ነገር ሁሉ በሰው ሁሉ ፊት እመኑበት፤ እግዚአብሔርን አመስግኑት፤ ስሙንም አመስግኑ፤ የእግዚአብሔርንም ሥራ በክብር ተናገሩ፤ ተአምራቱንም ግለጡ፤ እርሱንም ከማመስገን ቸል አትበሉ። 7የመንግሥትን ምሥጢር ሊሰውሩት፥ የእግዚአብሔርን ሥራ ግን በክብር ሊገልጡት ይገባልና፤ መከራም እንዳታገኛችሁ በጎ ሥራን ሥሯት። 8ጸሎት ከጾም፥ ከምጽዋትና ከጽድቅ ጋር መልካም ነው። ከብዙ የዓመፅ ገንዘብ ጥቂት የእውነት ገንዘብ ይሻላል፤ ወርቅንም ከማድለብ ምጽዋት መስጠት ይሻላል። 9ምጽዋት ከሞት ታድናለች፤ ከኀጢአትም ሁሉ ታነጻለችና፥ ጽድቅንና ምጽዋትን የሚያደርጉም ሁሉ ለራሳቸው ሕይወትን ይሞላሉ። 10የሚበድሉ ግን ሕይወታቸውን ይጠሏታል። 11“እነሆ፥ ነገሩን ሁሉ ከእናንተ አልሰውርም፤ የመንግሥትን ምሥጢር ሊሰውሩት የእግዚአብሔርን ሥራ ግን በክብር ሊገልጡት መልካም እንደ ሆነ እነግራችኋለሁ። 12እነሆ፥ አንተና ምራትህ ሣራ በጸለያችሁ ጊዜ የልመናችሁን መታሰቢያ እኔ በቅዱሱ ፊት አቀረብሁ፤ አንተም ሬሳ በቀበርህ ጊዜ ያንጊዜ እኔ ካንተ ጋራ ነበርሁ። 13ቸል ባላልህ ጊዜ፥ ምሳህንም ትተህ በተነሣህ ጊዜ፥ ሬሳንም ትቀብር ዘንድ በሄድህ ጊዜ፥ በጎ ሥራን መሥራትንም ባልዘነጋህ ጊዜ እኔ ከአንተ ጋር ነበርሁ። 14አሁንም፦ ጌታ እግዚአብሔር አንተን አድንህ ዘንድ፥ ምራትህ ሣራንም ከኀዘኗ አረጋጋት ዘንድ ላከኝ። 15የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ፥ በገናናውና በቅዱሱ ጌትነት ፊት ከሚያቀርቡ ሰባቱ ቅዱሳን መላእክት አንዱ መልአክ እኔ ሩፋኤል ነኝ” አላቸው። 16ይህንም ሰምተው ሁለቱ ደነገጡ፤ ፈርተዋልምና በግምባራቸው ወደቁ። 17መልአኩም እንዲህ አላቸው፥ “አትፍሩ፤ ነገር ግን አምላካችሁ እግዚአብሔርን ፍሩት፥ እግዚአብሔርንም ፈጽማችሁ አመስግኑት፤ 18ምስጋና ለእኔ አይገባኝምና፥ ነገር ግን የአምላካችሁ ፈቃድ አመጣኝ፤ ስለዚህም በዘመናት ሁሉ ለዘለዓለሙ እግዚአብሔርን አመስግኑት። 19እኔም ተገለጥሁላችሁ፤ ነገር ግን እይታን አያችሁ እንጂ ከእናንተ ጋር አልበላሁም፤ አልጠጣሁምም። 20አሁንም በእግዚአብሔር እመኑ፥ ወደ ላከኝም ወደ ላይ እወጣለሁና ይህን ሁሉ በመጽሐፍ ጻፉት” አለ። 21ያን ጊዜም ተነሥቶ ሄደ፤ ከዚያ በኋላም አላዩትም። 22የእግዚአብሔርም መልአክ ስለ ተገለጸላቸው፥ ገናናና ድንቅ በሚሆን በእግዚአብሔር ሥራ ሁሉ አመኑ።