የጦቢት ዐይን እንደ በራ
6ሩፋኤልም አለው፥ “ያባትህ ዐይኖች እንዲበሩ አውቃለሁ፤ 7አንተ ግን ያን ሐሞት ያባትህን ዐይን ኳለው፤ በተኳለም ጊዜ ዐይኖቹን ያሻል፤ ብልዙም ከዐይኑ ይወጣል፤ በደኅናም ያያል።” 8ሐናም ሮጣ የልጅዋን አንገት አቅፋ፥ “ልጄ ሆይ፥ ካየሁህ እንግዲህ ልሙት” አለችው፤ ሁለቱም አለቀሱ። 9ጦቢትም ወደ ደጅ ወጣ፤ ተሰነካከለም፤ ልጁም ሮጦ አባቱን አነሣው። 10የአባቱንም ዐይኖች በዚያ ሐሞት ኳለና፥ “አባቴ ሆይ፥ እንደምትድን ታመን” አለው። 11በኳለውም ጊዜ ዐይኖቹን አሸ። 12ብልዙም ከዐይኑ ብሌን ተገፈፈ፤ ልጁንም አየው፤ አንገቱንም አቅፎ አለቀሰ። 13እንዲህም አለ፥ “ጌታ ሆይ፥ የተመሰገንህ ነህ፤ ስምህም ለዘለዓለሙ ይመስገን፤ ቅዱሳን መላእክትህም ሁሉ ቡሩካን ናቸው፤ ገርፈህ ይቅር ብለኸኛልና። 14እነሆም፥ ልጄ ጦብያን አየሁት፤” ከዚህም በኋላ ልጁ ደስ እያለው ገባ፤ ለአባቱም በሜዶን የተደረገለትን ታላላቅ ነገር ሁሉ ነገረው። 15ጦቢትም ደስ እያለው ወጥቶ ምራቱን ተቀበላት፤ እግዚአብሔርንም በነነዌ አደባባይ አመሰገነው፤ ሲሄድም ያዩት ሰዎች፥ “እንዴት አየ?” ብለው አደነቁት። 16ጦቢት ግን በፊታቸው እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ እግዚአብሔር ይቅር ብሎታልና። ጦቢትም ወደ ምራቱ ወደ ሣራ በደረሰ ጊዜ፥ “ልጄ! እንኳን በደኅና ገባሽ!” ብሎ መረቃት፤ ወደ እኛ ያመጣሽ እግዚአብሔርም ይመስገን፤ አባትሽንና እናትሽንም ይባርክ” አላት። በነነዌም ለሚኖሩ ለወንድሞቹ ሁሉ ታላቅ ደስታ ሆነ። 17አኪአክሮስም መጣ፤ የወንድሙ ልጅ ነሳቦስም መጣ። 18ሰባት ቀንም በደስታ የሰርግ በዐል አደረጉ።