የጦቢት የመጨረሻ ምክር
1ከዚህ በኋላ ጦቢት ከመጸለይ ዝም አለ፤ 2ዐይኑም በጠፋ ጊዜ አምሳ ስምንት ዓመት ሆኖት ነበር። ከስምንት ዓመት በኋላም አየ፤ ምጽዋትም መጸወተ፤ ጌታ እግዚአብሔርን መፍራትንም ጨመረ፤ በእርሱም አመነ። 3ፈጽሞ አረጀ፤ ልጁንና የልጁንም ልጆች ጠራቸው፤ እንዲህም አላቸው፥ “አርጅቻለሁና፥ ለሞትም ደርሻለሁና ልጆችህን አምጣቸው።” 4ልጄ፥ ወደ ሜዶን ሂድ፤ ትጠፋ ዘንድ እንዳላት ነቢዩ ዮናስ በነነዌ የተናገረውን ነገር ሁሉ አውቃለሁና፤ በሜዶን ግን እስከ ዘመኑ ድረስ ሰላም ይሆናል። ወንድሞቻችንም ከተባረከች ምድር ሁሉ ወደየሀገሩ ይበተኑ ዘንድ አላቸው፤ ኢየሩሳሌምም ምድረ በዳ ትሆናለች፤ በእርስዋም ያለ የእግዚአብሔር ቤት ይቃጠላል፤ እስከ ዘመኑም ድረስ ምድረ በዳ ይሆናል። 5ዳግመኛም እግዝአብሔር ይቅር ብሎ ወደ ሀገራቸው ይመልሳቸዋል፤ ማደሪያው ቤተ መቅደስንም ይሠራሉ፤ የዘመኑ ቍጥር እስከሚፈጸም ነው እንጂ እንደ ቀድሞው አይደለም፤ ከዚህም በኋላ ከተማረኩበት ይመለሳሉ፤ ኢየሩሳሌምንም በክብር ይሠሯታል፤ በእርሷም የእግዚአብሔርን ቤት እስከ ልጅ ልጅ ዘመን ድረስ በዕብነ በረድ ይሠራሉ። 6አሕዛብም ሁሉ በእውነት ወደ እርሱ ይመለሳሉ፤ እግዚአብሔርንም ይፈሩታል፤ ጣዖቶቻቸውንም ይጥላሉ። 7አሕዛብ ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል። ሕዝቡም በእርሱ ያምናሉ፤ እግዚአብሔርም ወገኖቹን ከፍ ከፍ ያደርጋቸዋል። በእውነትና በቅንነት እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ሁሉ ደስ ይላቸዋል፤ ለወንድሞቻቸውም ቸርነትን ያደርጋሉ። 8“ልጄ ሆይ! አሁንም ከነነዌ ውጣ፤ ነቢዩ ዮናስ የተናገረው ነገር በግድ ይደረጋልና። 9አንተ ግን ትእዛዙንና ሕጉን ጠብቅ፤ ይቅር ባይም ሁን፤ በጎ ይደረግልህ ዘንድ እውነትን ውደድ። 10አክብረህ ቅበረኝ፤ እናትህንም ከእኔ ጋር ቅበራት። ልጄ፥ በነነዌ አትቈይ። ሐማ በዘመድህ በአኪአክሮስ ያደረገውን፥ ከብርሃን ወደ ጨለማ እንዳገባው፥ ፍዳውንም እንደ ተቀበለ፥ አኪአክሮስም እንደ ዳነ እይ። እርሱ ግን ፍዳውን ተቀበለ፤ እርሱ ወደ ጨለማ ወረደ። ምናሴ ምጽዋትን አደረገ፤ እውነትንም አደረገ፤ ከመከሩበት ከሞት መቅሠፍትም ዳነ። ሐማ ግን በዚያች ወጥመድ ወደቀና ሞተ።
የጦቢትና የሚስቱ ሞት
11“አሁንም ልጄ፥ ምጽዋት የምታደርገውን እይ፤ ከሞት ታድናለች፤ ታጸድቃለችም።” ጦቢትም ይህን ተናግሮ ሞተ፤ ባልጋው ላይ ሳለም ነፍሱ ከሥጋው ተለየች። መቶ አምሳ ስምንት ዐመትም ሆኖት ነበር። በክብርም ቀበሩት፤ 12እናቱ ሐናም በሞተች ጊዜ ካባቱ ጋራ ቀበራት። ጦብያም ከሚስቱና ከልጆቹ ጋር አማቱ ራጉኤል ወዳለበት ወደ ባጥና ሄደ። 13ራጉኤልና ሚስቱ አድናም አርጅተው ሞቱ። አማቶቹንም አክብሮ ቀበራቸው። ገንዘባቸውንም ሁሉ ወረሰ። የአባቱን የጦቢትን ገንዘብም ወረሰ። 14ጦብያም በመቶ ሃያ ሰባት ዓመቱ ሞተ፤ የሜዶን ክፍል በምትሆን በባጥናም ተቀበረ። 15አባቱም እንደ ነገረው ሳይሞት የነነዌን ጥፋት ሰማ። ናቡከደነፆርና አሕሻዊሮስም የነነዌን ጥፋት ሰምተው ደስ አላቸው።