የዮዲት ጸሎት
1ዮዲት ግን በግንባሯ ተደፍታ በምድር ላይ ወደቀች፤ በራሷም ላይ ትቢያ ነሰነሰች፤ የምትለብሰውንም ማቅ አሳየች፤ በኢየሩሳሌምም ባለው በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሠርክ ዕጣን በሚቀርብበት ጊዜ ዮዲት በታላቅ ቃል ወደ እግዚአብሔር ጮኸች፤ እንዲህም አለች፦ 2“በማኅፀን ያለ ጽንስን ያጠፉ፥ ድንግልንም ያጐሰቈሉ፥ ልብሷንም የገፈፉ፥ በከተማም በአራቱ ማዕዘን ለመገዳደር ማኅፀንን ያሳደፉ ጠላቶችን ይበቀል ዘንድ በእጁ ሰይፍን የሰጠኸው የአባቴ የስምዖን አምላክ ሆይ፥ አንተ እንዲህ አይደለም አልህ፤ እነርሱ ግን አደረጉት። 3ስለዚህም አለቆቻቸውን ለመገደል አሳልፈህ ሰጠሃቸው፤ መኝታቸውም በተገደሉት ባሮች ደም ተነከረ፤ ባሮችን ከጌቶቻቸው ጋር፥ ጌቶችንም በዙፋኖቻቸው ላይ ገደልሃቸው። 4ሚስቶቻቸውና ልጆቻቸው ተማረኩ፤ በአንተ ዘንድ የተወደዱ፥ ለአምላክነትህም የቀኑ፥ የረከሰ ደማቸውንም የተጸየፉ፥ ትረዳቸውም ዘንድ የለመኑ የልጆችን ምርኮ ሁሉ ተካፈሉ፤ አምላኬ እግዚአብሔር ሆይ፥ እኔን መበለቲቱን ስማኝ። 5ከዚህ አስቀድሞና ከዚያም በኋላ የሆነውን አንተ አድርገሃልና የዛሬውንና የሚመጣውንም ታውቀዋለህ፤ አንተም በምታውቀው ሆነ። 6ምክርህ የቀና ነው፤ ሥርዐትህ የተዘጋጀ ነውና፥ ፍርድህንም አስቀድመህ ባወቅህ ፈርደሃልና እነሆ፥ መጣን ይሉሃል፤ 7“እነሆ፥ የአሦር ሰዎች ከሠራዊታቸው ጋር በዝተዋልና፥ በፈረሶቻቸውም ላይ ከፍ ከፍ ብለዋልና፥ በፈረስም የተቀመጡ ሰዎች በኀይላቸው ታምነዋልና፥ አርበኞችም በጽናታቸው፥ በቀስታቸውና በጦራቸው፥ በምድር ነጎዳቸውም ታምነዋልና አንተ አርበኞችን የምታጠፋ አምላክ እንደ ሆንህ አላወቁህምና ስምህም አሸናፊ እንደ ሆነ አልተገነዘቡም። 8አንተ ከሠራዊታቸው ጋር በከሃሊነትህ አጥፋቸው፤ ቤተ መቅደስን ያጐሰቍሉ ዘንድ፥ የስምህ ጌትነት ማደሪያ የሆነች ደብተራ ኦሪትንም ያሳድፉ ዘንድ መክረዋልና፥ በብረትም የመሠዊያህን ቀንዶች አፍርሰዋልና በቍጣህ ኀይላቸውን አጥፋ። 9ትዕቢታቸውን ተመልከት፤ በራሳቸውም ላይ ቍጣህን አምጣ። እንደ አሰብሁት እፈጽም ዘንድ በእኔ በመበለቲቱ እጅ ኀይልን አድርግ። 10በአንደበቴ ጥበብ ሎሌውን ከጌታው፥ ጌታውንም ከሎሌው ጋር ግደል። ግርማቸውን በእኔ በሴቲቱ እጅ አጥፋ። 11ብርታትህ በብዙዎች አይደለምና፥ ኀይልህም በኀያላን ሰዎች አይደለምና፤ ነገር ግን አንተ የትሑታን አምላክ ነህ፤ የጥቂቶች ረዳት ነህ፤ የበሽተኞችም ፈዋሽ አንተ ነህ፤ ለጠፉትም ጠባቂያቸው አንተ ነህ፤ ተስፋ የቈረጡ ሰዎችንም የምታድናቸው አንተ ነህ። 12አወን አቤቱ የአባቴ አምላክ፥ የእስራኤልም የርስታቸው አምላክ፥ የሰማይና የምድር አምላክ፥ ውኃውን የፈጠርህ፥ የፍጥረታት ሁሉ ንጉሥ አንተ ጸሎቴን ስማ። 13የቃሌንም ጥበብ በሕግህና በቤተ መቅደስህ በደብረ ጽዮንና በልጆችህ ንብረት ቤት ላይ ክፉ ነገርን የመከሩ ጠላቶችን እንዲያቈስላቸውና እንዲያጠፋቸው አድርግ። 14የብርታትና የኀይል ሁሉ አምላክ አንተ እግዚአብሔር እንደ ሆንህ፥ የእስራኤልንም ወገን ከአንተ በቀር ሌላ የሚያጸናቸው እንደ ሌለ ለሕዝቡና ለአሕዛቡ ሁሉ እንዲያውቁት አድርግ።”