የዮዲት ትውልድና ተግባር
1በዚያም ወራት የእስራኤል ልጅ የሰለስዳይ ልጅ፥ የሰላምያል ልጅ፥ የናትናኤል ልጅ፥ የኤልያብ ልጅ፥ የኤልያስ ልጅ፥ የሐቂቆ ልጅ፥ የራወይል ልጅ፥ የጋዴዮን ልጅ፥ የአናንዮ ልጅ፥ የሕልቅያ ልጅ፥ የኦዝያል ልጅ፥ የዮሴፍ ልጅ፥ የሆክስ ልጅ፥ የሜራሪ ልጅ ዮዲት ሰማች። 2ባልዋም ከነገድዋና ከሀገርዋ የሆነ ምናሴ ነበር፤ የገብስ አዝመራ በደረሰበት ወራትም ሞተ። 3ነዶ ከሚያስሩ ሰዎች ጋራ በእርሻ ውሏልና ራሱን ምች መታው፤ ታምሞ ተኛ፤ በሀገሩ በቤጤልዋም ሞተ፤ እንደ አባቶቹም በሀገሩ በዶታይምና በበላሞን ባለ ቦታ ቀበሩት። 4ዮዲትም መበለት ሆና ሦስት ዓመት ከአራት ወር በቤትዋ ተቀመጠች። 5በቤትዋም ሰገነት ላይ የብሕትውና ክፍል አዘጋጀች፤ በወገቧም ማቅ ታጠቀች፤ የመበለትነት ልብሷንም ለበሰች። 6በመበለትነትም በኖረችበት ወራት ሁሉ ትጾም ነበር። በሰንበት ዋዜማና በሰንበት፥ በመባቻ ዋዜማና በመባቻ፥ በበዓላትና በእስራኤል የደስታ ቀኖች ካልሆነ በቀር አትበላም ነበር። 7መልከ መልካምና እጅግ ደመ ግቡ ነበረች፤ ባሏ ምናሴም ብሩንና ወርቁን፥ ሴቶችና ወንዶች አሽከሮችን፥ ከብቶቹንም፥ እርሻውንም ትቶላት ነበር፥ በእነርሱም ላይ ትኖር ነበር። 8ፈጽማ እግዚአብሔርን ትፈራ ነበርና በእርሷ ክፉ ቃልን የሚናገር አልነበረም።
ዮዲትና የእስራኤል ሽማግሌዎች
9ውኃው ስላለቀ ሰውነታቸው ተጨንቃለችና ሕዝቡ በአለቃቸው ላይ የተናገሩትን ክፉ ነገር ሰማች፤ ዮዲትም ዖዝያን ለሕዝቡ የነገራቸውን ቃል ሁሉ፥ ከአምስት ቀን በኋላም ሀገራቸውን ለአሦር ሰዎች እንዲሰጡ እንደ ማለላቸው ሰማች። 10ገንዘቧን ሁሉ የምትጠብቅ ሞግዚትዋንም ልካ ዖዝያንን፥ ከብሪኒንና ከርሜኒን፥ የከተማዋንም ሽማግሌዎች ጠራቻቸው። 11እነርሱም ወደ እርስዋ መጡ፤ እርስዋም “ዛሬ በሕዝቡ ፊት የተናገራችሁት በጎ ነገር አይደለምና በቤጤልዋ የሚኖሩ ሰዎች ሹሞች ሆይ! ስሙኝ እግዚአብሔር በእነዚህ በአምስቱ ቀኖች ባይረዳችሁ ሀገራችሁን ለጠላቶቻችሁ አሳልፋችሁ ትሰጡ ዘንድ በእግዚአብሔርና በእናንተ መካከል የተማማላችሁትን መሐላ በዚህ አጸናችሁ። 12አሁንም በዚች ቀን እግዚአብሔርን የምትፈታተኑት፥ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል የተነሣችሁ እናንተ፥ ምንድን ናችሁ? 13አሁንም እርሱ እግዚአብሔር ይመረምራል፤ እናንተ ግን እግዚአብሔር ሁልጊዜ የሚያደርገውን አታውቁም። 14በሰው ልቡና ያለ ረቂቅ ምሥጢርን የማታውቁ፥ የልቡናውንም አሳብ የማታስተውሉ ይህን ሁሉ ያደረገ እግዚአብሔርን እንዴት ትመረምራላችሁ? ልቡናውንስ መርምራችሁ ታውቁ ዘንድ እንዴት ትወዳላችሁ? ምክሩንስ መርምራችሁ ታገኙ ዘንድ እንዴት ትመረምራላችሁ? ወንድሞች ሆይ፥ ለእናንተ አግባባችሁ አይደለም፤ አምላካችን እግዚአብሔርንም አታሳዝኑት። 15በእነዚህ በአምስቱ ቀኖች ይረዳን ዘንድ ባይፈቅድ በማንኛውም ቀን ቢሆን በፈቀደ ጊዜ ሊያድነን፥ ወይም በጠላቶቻችን ፊት ሊያጠፋን ሥልጣን አለው። 16እግዚአብሔር እንደ ሰው የሚጨክን አይደለምና እንደ ሰውም የሚቀየም አይደለምና፥ እናንተ አምላካችን እግዚአብሔርን አትፈታተኑት። 17ነገር ግን ከእርሱ የምትገኝ ድኅነትን ደጅ ጥኑ፤ ቃላችንንም ሰምቶ ይረዳን ዘንድ ይፈቅድ እንደ ሆነ ለምኑት። 18“በዘመናችን ወይም ዛሬ በቀድሞ ዘመን እንደ ተደረገ ከእኛ መካከል ወገንም ቢሆን፥ ነገድም ቢሆን፥ ከተማም ቢሆን፥ መንደርም ቢሆን በሰው እጅ ለተሠሩ ጣዖታት ለመስገድ የተነሣ የለምና። 19ስለዚህም ነገር አባቶቻችን ለመበርበርና ለጦር ሆኑ፤ በጠላቶቻቸውም ፊት ጽኑ አወዳደቅን ወደቁ። 20እኛ ግን ያለእርሱ ሌላ አምላክ አናውቅም፤ ስለዚህ እኛን ወይም ወገኖቻችንን ቸል እንደማይለን በእርሱ እናምናለን። 21እኛ በተያዝን ጊዜ ይሁዳ ሁሉ ይያዛል፤ ንዋየ ቅድሳታችንም ይዘረፋል፤ በመቅደሱም መርከስ ከአንደበታችን ይመረመራል። 22የወንድሞቻችን መገደል፥ የሀገራችንም መዘረፍ፥ የርስታችንም ምድረ በዳ መሆን በሚገዙን አሕዛብ ዘንድ በእኛ ላይ ይመለሳል፤ ገንዘብ በሚያደርጉን ፊትም በዚያ የተሰነካከልንና መገዳደሪያ እንሆናለን። 23መገዛታችንም ያለ ምስጋና ይሆናልና፥ አምላካችን እግዚአብሔር መዋረዳችንን አላየምና። 24“አሁንም ወንድሞቻችን ሆይ፥ ለባልንጀሮቻችን ንገሩአቸው፤ እኛን ያዳምጣሉና፥ ልቡናቸውም ወደ እኛ ተሰቅሏልና፥ መሠዊያዉና ቤተ መቅደሱም በእኛ ጸንቶ ይኖራልና። 25አባቶቻችንን እንደ ፈተናቸው የሚፈትነን አምላካችን እግዚአብሔርን በዚህ ሁሉ እናመስግነው። 26ለአባቶቻችን ያደረገውን ሁሉ አብርሃምን እንደ ፈተነው፥ ይስሐቅንም እንደ ፈተነው፥ ያዕቆብንም የእናቱን ወንድም የላባን በጎች ሲጠብቅ በሶርያ መስጴጦምያ እንደ ፈተነው አስቡ። 27እነርሱንም በፈተናቸውና ልቡናቸውን በመረመረ ጊዜ እኛን የበደለን አይደለም፤ እግዚአብሔር የሚቀርቡትን ሰዎች ይቅር ይላቸው ዘንድ ነው እንጂ፥ ሊያጠፋቸው አይደለምና።” 28ዖዝያንም አላት፥ “የተናገርሽውን ሁሉ በበጎ ልቡና ተናገርሽ፤ ቃልሽንም የሚቃወመው የለም። 29ጥበብሽ የተሰማው ከዛሬ ጀምሮ አይደለምና፥ ከመጀመሪያው ዘመንሽ ጀምሮ ሰው ሁሉ በጥበብሽ ዐወቀሽ እንጂ፥ የልቡናሽ ተፈጥሮ ደግ ነውና። 30ነገር ግን ሕዝቡ ፈጽመው ተጠምተዋልና እንዳሉን እናደርግ ዘንድ ዘበዘቡን፤ ልንለውጠው የማይቻለንን መሐላ አመጡብን። 31አሁንም አንቺ እግዚአብሔርን የምትፈሪ ሴት ነሽና እግዚአብሔር ዝናምን ያዘንምልን ዘንድ፥ ኵሬያችንም ይመላ ዘንድ፥ እንግዲህ ወዲህም እንዳንጠማ ለምኝልን።” 32ዮዲትም አለቻቸው፥ “ስሙኝ ለልጅ ልጅ የሚነገር ሥራን እሠራለሁ። 33እናንተ ግን በዚች ሌሊት በበሩ ቁሙ፤ እኔም ከብላቴናዬ ጋር እወጣለሁ፤ ሀገራችንን አሳልፈን ለጠላቶቻችን እንሰጣለን በምትሉበት በእነዚያም ወራቶች የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር በእጄ ይረዳል። 34እናንተ ግን የምሠራውን ሥራ አትመርምሩኝ፤ እኔ የምሠራው ሥራ እስኪፈጸም ድረስ አልነግራችሁምና።” 35ዖዝያንና አለቆቻቸውም፥ “በሰላም ሂጂ፤ እግዚአብሔርም በፊትሽ ይሁን፤ ጠላቶቻችንንም ይበቀል” አሏት። 36ተመልሰውም ወደ ባልንጀሮቻቸው ሄዱ።