የቤጤልዋ መከበብ
1በማግሥቱም ሆሎፎርኒስ ወደ ቤጤልዋ ይጓዙ ዘንድ፥ ቀድመውም የአንባዎቹን መግቢያ ይይዙና የእስራኤልን ልጆች ይዋጓቸው ዘንድ ከእርሱ ጋራ የተሰለፉ ጭፍሮቹንና ወገኖቹን ሁሉ አዘዛቸው። 2በዚያም ቀን ጽኑዓን አርበኞች የሆኑ ኀይለኞች ሰዎች ሁሉ ወረዱ፤ እነዚያም ጓዝ ከሚጠብቁ ካልከበቡ ከብዙ አርበኞች ሰዎች በቀር መቶ ሰባ ሺህ እግረኞችና ዐሥራ ሁለት ሺህ ፈረሰኞች ነበሩ። 3በቤጤልዋ አጠገብ፥ በአውሎን በውኃው ምንጭ አጠገብ ሰፈሩ፤ የሰፈራቸውም አቆልቋዩ እስከ ዶታይምና ቤጤልዋ ድረስ፥ ወርዱም በአሴዴራሎም አንጻር ከቤጤልዋ እስከ ቅያሞስ ደረሰ። 4የእስራኤልም ልጆች ብዛታቸውን በአዩ ጊዜ እጅግ ደነገጡ፤ እርስ በርሳቸውም፥ “እነዚህ ሰዎች ዛሬ ምድርን ሁሉ ይሸፍኗታል፤ ተራራም ቢሆን፥ ኮረብታም ቢሆን፥ ቈላም ቢሆን ብዛታቸውን የሚችል የለም” ተባባሉ። 5ሁሉም መሣሪያቸውን ያዙ፤ ባንባቸውም እሳት አነደዱ፤ በዚያችም ሌሊት ሁሉ ሲጠብቁ አደሩ። 6በሁለተኛውም ቀን ሆሎፎርኒስ በቤጤልዋ ባሉ በእስራኤል ልጆች ፊት ፈረሶቹን ጫነ። 7የከተሞቻቸውን መግቢያ ያዩ ዘንድ፥ የውኃቸውንም ምንጭ ይከቡ ዘንድ፥ ወደዚያም አርበኞች ሰዎች ቀድመው ይደርሱና ይከቡ ዘንድ ጕበኞችን ላከ። 8እርሱም ከሠራዊቱ ጋር ፈጥኖ ሄደ፤ አርበኞች የሆኑ የኤሳው ልጆች አለቆችም ሁሉ የሞዓብ ወገኖች ሹሞች ሁሉና የባሕር ዙሪያ ገዢዎች ወደ እርሱ መጡ። 9እንዲህም አሉት፥ “አቤቱ በሠራዊትህ ላይ ጥፋት እንዳይሆን ቃላችንን ስማ። 10እነዚህ የእስራኤል ልጆች ወገኖች በሚኖሩባቸው አንባዎቻቸውና ኮረብታዎቻቸው ነው እንጂ በጦራቸው የሚተማመኑ አይደሉም፤ ለአንባዎቻቸው መውጫ የላቸውምና፤ 11አቤቱ አሁንም በሰልፍ ሥርዐት አቷጋቸው፤ ከሠራዊትህ አንድ ሰው ስንኳ የሚሞት አይኑር። 12ነገር ግን አንተ ከሠራዊትህ ጋር በሰፈር ጠብቃቸው፤ አሽከሮችህና የሠራዊትህ አርበኞች ሁሉ ከተራራው በታች የሚፈልቅ የውኃቸውን ምንጮች ሁሉ አጽንተው ይጠብቁ። 13በቤጤልዋ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ከዚህ ውኃ ስለሚቀዱ ውኃ ጥም ይገድላቸዋል፤ ሀገራቸውንም ለአንተ ያሰገዛሉ፤ ሠራዊቶቻችንና እኛም ላንባቸው ቅርብ ወደ ሆነ ቦታ ወደ ኮረብታቸውም ራስ እንወጣለን ካንባቸው አንድ ሰው ስንኳ የሚወጣ እንዳይኖር በዚያ ሰፍረን እንጠብቃቸዋለን። 14እነርሱ፥ ሚስቶቻቸውና ልጆቻቸውም በረኃብ ይጠፋሉ፤ ሳይዋጓቸውም ባገራቸው ጎዳና ይወድቃሉ። 15ከድተዋልና፥ በሰላምም አልተቀበሉህምና ጽኑ በቀልን ትበቀላቸዋለህ።” 16በሆሎፎርኒስ ፊትና በሠራዊቱ ሁሉ ፊት ቃላቸው ደስ አሰኘ፤ እንደ ተናገሩም ያደርጉ ዘንድ አዘዘ። 17የአሞን ልጆች ሠራዊትም ተጓዙ፤ አምስት ሺህ የሚሆኑ የአሦር ሠራዊትም ከእነርሱ ጋር ነበሩ፤ በአውሎኒም ሰፈሩ፤ የእስራኤልንም ልጆች ምንጮችና ውኃቸውን አስቀድመው ያዙ። 18የኤሳውና የአሞን ልጆችም ወጥተው በዶታይም አንጻር ባሉ ተራሮች ሰፈሩ፤ ከእነርሱም በምኩር ወንዝ ባለ በኩሲ አጠገብ ባለ በኤቄሬቢን አንጻር ወደ ደቡብና ወደ ምሥራቅ ሰዎችን ላኩ። የቀሩት የአሦር ሠራዊቶች ግን በምድረ በዳ ሰፈሩ፤ ሀገሩንም ሁሉ አለበሱት፤ ከዚህም በኋላ ጓዛቸውን ከእነርሱ የሚበዛ የሌለ ሠራዊታቸውንና ብዙ ገንዘባቸውን አጓዙ።
የእስራኤላውያን መጨነቅ
19ጠላቶቻቸው ስለ ከበቧቸው፥ ከመካከላቸውም መውጫ ስለሌላቸው ሰውነታቸው ተጨንቃለችና የእስራኤል ልጆች ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። 20አሦራውያንም ከሠራዊቶቻቸው ሁሉ ጋር አርበኞቻቸውም በፈረሶችና በሰረገላ የተቀመጡ ሰዎችም ከበዋቸው ሠላሳ አራት ቀን ተቀመጡ፤ በቤጤልዋ የሚኖሩ ሰዎችም በዕቃቸው ያለ ውኃቸው ሁሉ አለቀ። 21የሚጠጡት ላንድ ቀን የሚያረካቸው ውኃ አልነበራቸውም፤ በመስፈሪያ እየመጠኑ ወደ መጠጣትም ተመለሱ። 22ልጆቻቸውና ሚስቶቻቸው፥ ጐልማሶቻቸውም ተጨነቁ፤ በውኃ ጥም አለቁ፤ በከተማውም አደባባይና በበሩ ጎዳና ወደቁ፤ ከዚህም በኋላ ምንም ኀይል አልነበራቸውም። 23ሕዝቡ ሁሉ፥ ጐልማሶችና የከተማው አለቆችም፥ ልጆችና ሴቶችም ወደ ዖዝያን ተሰበሰቡ፤ ቃላቸውንም አሰምተው ጮኹ። በአለቆቻቸውም ፊት እንዲህ አሉ፦ 24“በእኛ ላይ ታላቅ ጉዳትን ታደርሱብን ዘንድ ከአሦር ሰዎች አሽከሮች ጋራ በሰላም በጎ ነገር ባልተናገራችሁ በእናንተና በእኛ መካከል እግዚአብሔር ይፍረድ። 25አሁንም የሚረዳን አጣን፤ በፊታቸውም በውኃ ጥምና በጽኑ ጥፋት እንጠፋ ዘንድ እግዚአብሔር በእጃቸው ጣለን። 26አሁንም ተገዙላቸው፤ ይዘርፉም ዘንድ ከተሞቻችሁን ሁሉ ለሆሎፎርኒስ ወገኖችና ሠራዊት አሳልፋችሁ ስጧቸው። 27ሰውነታችን እንድትድን፥ የልጆቻችንንም ሞት በዐይኖቻችን እንዳናይ በውኃ ጥም ከምንሞት ቢዘርፉንና ብንገዛላቸው ይሻለናልና፥ የሚስቶቻችንና የልጆቻችን ሰውነትም አልቃለችና። 28እነሆ፥ ዛሬ በዚች ቀን ይህን ነገር እንዳታደርጉ ሰማይንና ምድርን እንዳባቶቻችን ኀጢአትና እንደ ኀጢአታችን የሚፈርድብን ያባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔርን እናዳኝባችኋለን።” 29በማኅበሩም መካከል ጽኑ ልቅሶ ሆነ፤ ሁሉም በአንድነት አለቀሱ፤ ቃላቸውንም አሰምተው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። 30ዖዝያንም አላቸው፥ “ወንድሞቻችን ሆይ! ሁልጊዜ በመከራው የሚጥለን አይደለምና ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ቸርነቱን እስኪመልስልን ድረስ እመኑ፤ ዳግመኛም አምስት ቀን ታገሡ። 31እነዚህ አምስት ቀኖች ካለፉ በኋላ ረድኤቱ ካልመጣልን እንደ ተናገራችሁት እናደርጋለን።” 32ሕዝቡንም ወደየሰፈራቸው በተናቸው፤ እነርሱም ወደ ከተማቸው ግንብና አንባ ሄዱ፤ ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውንም ወደ ቤታቸው ላኩ፤ በከተማም ፈጽመው የተጨነቁ ነበሩ።