አክዮር ለእስራኤል ተላልፎ መሰጠቱ
1ከዚህ በኋላ በሸንጎው ዙሪያ ያሉ እነዚያ ሰዎች ዝም ባሉ ጊዜ የአሦር ሠራዊት አለቃ ሆሎፎርኒስ አክዮርን በፍልስጥኤም ወገኖችና በሞዓብ ልጆች ሁሉ ፊት እንዲህ አለው፦ 2“አንተ የኤፍሬም ምንደኛ አክዮር! ዛሬ ትንቢት ትናገርልን ዘንድ እግዚአብሔር ያጸናቸዋልና የእስራኤልን ልጆች አትውጓቸው ትለን ዘንድ አንተ ማን ነህ? ያለ ናቡከደነፆርስ እግዚአብሔር ማን ነው? 3እርሱ ኀያላኑን ልኮ ከገጸ ምድር ፈጽሞ ያጠፋቸዋል፤ አምላካቸውም አያድናቸውም፤ እኛም የናቡከደነፆር ባሮች እንደ አንድ ሰው እናጠፋቸዋለን፤ በእነርሱ እንረግጣቸዋለንና የፈረሶቻችንንም ኀይል ሊቋቋሙ አይችሉም። 4ተራሮቻቸውም በደማቸው ይሰክራሉ፤ የልጆቻቸውም ሬሳ ይበዛል፤ የዓለሙ ሁሉ ጌታ ንጉሡ ናቡከደነፆር አጠፋቸዋለሁ ብሏልና ቃሉ ሐሰት እንዳይሆን ከዚህ ዓለም ፈጽመው ይጠፋሉ እንጂ በፊታችን በእግራቸው አይቆሙም። 5“ዛሬ በኀጢአትህ ይህን የተናገርህ የአሞን ምንደኛ አክዮር፥ አንተ ግን ከግብፅ ሀገር የወጡ እስራኤልን ተበቅዬ እስካጠፋቸው ድረስ ከዚህ ቀን ጀምሮ እንግዲህ ወዲህ ፊቴን አታየውም። 6የዚያን ጊዜ የጭፍራዎችና የወገኖች ጦር በጎንህ ይገባል፤ ከሬሳዎቻቸውም ጋራ ትወድቃለህ። 7በተመለስሁም ጊዜ ባሮች ወደ አንባቸው ይወስዱሃል፤ ባቀበቱም ካሉ ከተሞቻቸው ባንዲት ከተማ ያኖሩሃል። 8እስካጠፋቸውም ድረስ አይገድሉህም። 9እንደማንችላቸው በልብህ ትታመናለህና ፊትህ አይውደቅ፤ እኔ ተናግሬአለሁና፤ ከቃሌም የሚወድቅ የለምና።” 10ሆሎፎርኒስም በፊቱ በድንኳኑ ውስጥ የሚቆሙ አሽከሮቹን አክዮርን ይዘው ወደ ቤጤልዋ ይወስዱት ዘንድ፥ ለእስራኤልም ልጆች እርሱን ይሰጧቸው ዘንድ አዘዛቸው። 11አሽከሮቹም ይዘው ከሰፈሩ ውጭ ወደ ምድረ በዳ ወሰዱት፤ ከምድረ በዳውም መካከል ወደ ተራራማው ሀገር ሄዱ፤ ከዚህም በኋላ በቤጤልዋ በታች ወዳሉ ምንጮች ደረሱ። 12የዚያችም ሀገር ሰዎች ባዩአቸው ጊዜ መሣሪያቸውን ይዘው ከከተማ ወደ ተራራው ራስ ሄዱ። ወንጭፍ የያዙ ሰዎችም ሁሉ መግቢያውን ጠበቁ፤ በላያቸውም መርግ ጣሉ። 13የአክዮርንም እግር ብረት ፈቱት፤ በተራራውም በታች አሰሩት፤ በዚያም በተራራው በታች ጣሉት፤ ትተውትም ወደ ጌታቸው ተመለሱ። 14የእስራኤልም ልጆች ከአንባቸው ወርደው ወደ እርሱ ሄዱ፤ ፈትተውም ወደ ቤጤልዋ ወሰዱት። 15በዚያም ወራት የከተሞቻቸው አለቆች በነበሩት ከነገደ ስምዖን በሚካ ልጅ ኦዝያስና በጎቶንያ ልጅ በክብሪስ፥ በመልክያል ልጅ በከርሚስም ዘንድ አስቀመጡት። 16በከተሞቻቸውም ያሉ አለቆችን ሁሉ ጠሩ፤ ሴቶቻቸውና ጐልማሶቻቸውም ሁሉ ሮጠው ወደ ሸንጓቸው ሄዱ፤ አክዮርንም በሁሉ መካከል አቆሙት፤ ኦዝያስም የተደረገውን ሁሉ ጠየቀው። 17እንደ ዶለቱና በአሦር ሠራዊት አለቆች መካከል ነገራቸውን ሁሉ እንደ ተናገሩ፥ ሆሎፎርኒስም በእስራኤል ወገኖች ላይ በትዕቢት እንደ ተናገረ መልሶ የሆሎፎርኒስን ነገር ሁሉ ነገራቸው። 18ሕዝቡም ሁሉ በግንባራቸው ወድቀው ለእግዚአብሔር ሰገዱ፤ እንዲህም እያሉ ጸለዩ፦ 19“አቤቱ የሰማይ አምላክ ሆይ፥ ትዕቢታቸውን ተመልከት፤ የወገኖቻችንንም መከራ አይተህ ይቅር በል፤ በዚችም ቀን ወደ መቅደስህ ተመልከት።” 20አክዮርንም ደስ አሰኙት፤ ፈጽመውም አከበሩት። 21ኦዝያስም ከተሰበሰቡበት ወስዶ ወደ ቤቱ አገባው፤ ለሽማግሌዎችም በዓልን አደረጉ፤ ይረዳቸውም ዘንድ የእስራኤልን አምላክ በዚያች ሌሊት ሁሉ ለመኑት።