ሆሎፎርኒስ በእስራኤል ላይ ለመዝመት የጠራው ስብሰባ
1“የእስራኤል ልጆች ለሰልፍ ተዘጋጁ፤ የኮረብታቸውንም በሮች ዘጉ። የአምባውንም ራሶች አጠሩ፤ መንገዱንም ጐፃጕፅ አደረጉ” ብለው ለአሦር ሠራዊት አለቃ ለሆሎፎርኒስ ነገሩት። 2እርሱም ፈጽሞ ተቈጣ፤ የሞአብን አለቆችና የአሞንን ሹሞች፥ በባሕር ዙሪያ ያሉ ገዢዎችንም ጠራቸው። 3እንዲህም አላቸው፥ “የከነዓን ልጆች ሆይ! ንገሩኝ፤ በተራሮች የሚኖሩ እነዚህ ወገኖች ምንድን ናቸው? በከተሞች የሚኖሩ፥ ሠራዊታቸውም ብዙ የሆኑ እኒያስ ወገኖች ምንድን ናቸው? ጽናታቸውስ ምን ያህል ነው? በእነርሱስ ላይ የነገሠ ንጉሥ ማን ነው? ወይስ ሹማቸው? ወይስ አለቃቸው ማን ነው? 4በምዕራብ ከሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ጋር ይቀበሉኝ ዘንድ እንዴት አልመጡም?”
የአክዮር ንግግር
5የአሞን ልጆች ሹም አክዮርም እንዲህ አለ፥ “ከእኔ ከባርያህ አንደበት ይህን ነገር ስማ፤ ከእኔ ከባሪያህ አንደበት ሐሰት ነገር አይወጣምና፥ በእነዚህ አንባዎች፥ በአቅራቢያህም ስለሚኖሩ ስለእነዚህ ወገኖች እውነት ነገርን እነግርሃለሁ። 6እነዚህ ወገኖች ከከላውዴዎን መጡ። 7በከላውዴዎን ሀገር የሚኖሩ የአባቶቻቸውን ጣዖቶች ያመልኩ ዘንድ አልወደዱምና አስቀድመው በመስጴጦምያ ይኖሩ ነበረ። 8የወገኖቻቸውንም መንገድ ትተዋልና ላወቁት ከጣዖቶቻቸው ፊት ላወጣቸው ለሰማይ አምላክ ለእግዚአብሔርም ሰግደዋልና ወደ መስጴጦምያ ሸሽተው በዚያ ብዙ ዘመን ኖሩ። 9ፈጣሪያቸውም ከተሰደዱበት ሀገር ይወጡና ወደ ከነዓን ይሄዱ ዘንድ አዘዛቸው፤ በዚያም ብዙ ዘመን ኖሩ፤ ብርንና ወርቅን፥ ብዙ ከብቶችንም ፈጽመው አበዙ። 10ረኃብ በከነዓን ሀገር ሁሉ ጸንትዋልና ወደ ግብፅ ወረዱ፤ በዚያም እየተመገቡ ኖሩ፤ በዚያም በዝተው ሞሉ፤ ለወገኖቻቸውም ቍጥር አልነበራቸውም። 11የግብፅ ንጉሥም በጠላትነት ተነሣባቸው፤ ተተነኰለባቸውም፤ መከራም አጸናባቸው፤ ጡብ በማሠራትም ገዛቸው፤ ባሮችም አደረጋቸው። 12ወደ አምላካቸውም ጮኹ፤ እርሱም መድኀኒት በሌለው መቅሠፍት የግብፅ ሀገርን ሁሉ አጠፋ፤ ግብፃውያንም ከፊታቸው አስወጡአቸው። 13እግዚአብሔርም በፊታቸው የኤርትራን ባሕር አደረቃት። 14ወደ ሲና ተራራና ቃዴስ በርኔ ወሰዳቸው፤ በምድረ በዳ የሚኖሩትንም ሁሉ አወጣቸው። 15በአሞራውያን ሀገርም ኖሩ፤ የሐሴቦንንም ሰዎች ሁሉ በኀይሉ አጠፋ ዮርዳኖስንም ተሻግረው ተራራማውን ሀገር ሁሉ ወረሱ። 16ከናኔዎንን፥ ፌርዜዎንን፥ ኢያቡሴዎንን፥ ሴኬምን፥ ጌርጌሴዎንንም ሁሉ ከፊታቸው አስወጣቸው፤ በዚያም ብዙ ዘመን ኖሩ። 17“በፈጣሪያቸውም ፊት ባልበደሉ ጊዜ መልካም ነገር ሁሉ ሆነላቸው፤ በደልን የሚጠላ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ነበረና። 18ያዘዛቸውን ሥርዐት በተዉ ጊዜ ግን ፈጽሞ በብዙ ጦር አጠፋቸው፤ ወደ ባዕድ ሀገርም ተማረኩ፤ የፈጣሪያቸው ማደሪያ ቤተ መቅደስም ፈረሰ፤ ምድረ በዳም ሆነ፤ ከተሞቻቸውንም ጠላቶቻቸው ያዙባቸው። 19ዛሬ ግን ወደ ፈጣሪያቸው ተመለሱ፤ ከተበተኑበትም ሀገር ከዚያ ተሰበሰቡ፤ ቤተ መቅደስ ባለበት በኢየሩሳሌም ኖሩ፤ ምድረ በዳም ነውና በተራራው ኖሩ። 20አሁንም አቤቱ ጌታዬ እነዚህ ወገኖች በደል እንዳለባቸው፥ ፈጣሪያቸውንም በድለው እንደ ሆነ ይህ መሰናክላቸው ነውና አንድ ጊዜ እናረጋግጥ፤ ከዚያ በኋላ ወጥተን እንዋጋቸዋለን። 21በእነዚህ ወገኖች በደል ከሌለባቸው ግን ጌታዬ እለፋቸው፤ እነሆ ጌታቸው ያጸናቸው ይሆናል፤ ወይም አምላካቸው ይቆምላቸው ይሆናል፤ እኛም በሀገሩ ሁሉ ኀፍረት እንሆናለን።” 22ከዚህ በኋላ አክዮር ይህን ነገር ተናግሮ በጨረሰ ጊዜ በሰፈሩ ዙሪያ የቆሙ ወገኖች ሁሉ አንጐራጐሩ፤ የሆሎፎርኒስ ሹሞች፥ በባሕር ዙሪያና በሞዓብ የሚኖሩ ሰዎችም ሁሉ “አክዮርን እንግደለው” አሉ። 23“ከጽኑ አርበኛ ጋር ይዋጉ ዘንድ ብርታትና ኀይል የሌላቸውን ወገኖች የእስራኤልን ልጆች የምንፈራቸው አይደለም። 24ስለዚህ ግን ጌታችን ሆሎፎርኒስ ሆይ፥ እንዝመት፤ እነርሱም ለጭፍራዎችህ ሁሉ ምግብ ይሆናሉ” አሉ።