አይሁድ ራሳቸውን ለመከላከል ያደረጉት ዝግጅት
1በይሁዳ የሚኖሩ የእስራኤል ልጆች የአሦር ንጉሥ የናቡከደነፆር ቢትወደድ ሆሎፎርኒስ በአሕዛብ ያደረገውን ሁሉ፥ አውራጃዎቻቸውን ሁሉ እንዳጠፋ፥ እነርሱንም እንዳጠፋቸው ሰሙ። 2ከመቅረቡም የተነሣ ስለ ኢየሩሳሌምና ስለ አምላካቸው ስለ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ፈጽመው ፈሩ። 3ከይሁዳ የተመረጡ ወገኖችም ሁሉ በቅርቡ ከምርኮ ከተመለሱ በኋላ ተሰብስበው ነበርና ምሥዋዑንና ንዋየ ቅድሳቱን፥ ቤተ መቅደሱንም ከረከሰ በኋላ አነጹት። 4ስለዚህም ወደ ሰማርያ አውራጃዎችና ወደ ቆና፥ ወደ ቤቶሮንና ወደ ቤልሜን፥ ወደ ኢያሪኮና ወደ ኮባ፥ ወደ ኤሦራና ወደ ሳሌም ሸለቆ ሁሉ ላኩ። 5ከፍ ያሉ የተራራዎቻቸውንም ጫፎች ያዙ። በሚኖሩባቸው መንደሮችም መሸጉ። አዝመራቸውም ቀደም ብሎ ተሰብስቦ ነበርና ለጦርነት ስንቅን አዘጋጁ። 6በዚያም ወራት በኢየሩሳሌም የሚኖር የካህናቱ አለቃ ኢዮአቄም በዶታይም አጠገብ ባለች ምድረ በዳ፥ በኤስድራሎም አንጻር ባለች በቤጦሜስቴምና በቤጤልዋ ለሚኖሩ ሰዎች ጻፈ። 7በዚያም በይሁዳ ላይ መግቢያ ስለአለና መግቢያውም ለሁለት ሰዎች መተላለፊያ ብቻ ነው እንጂ ጠባብ ስለ ሆነ የሚወጡትን ለመከላከል የአንባዎቹን መግቢያ አጽንታችሁ ጠብቁ ብሎ ጻፈ።
የእስራኤል ጸሎት
8የእስራኤልም ልጆች ታላቁ ካህን ኢዮአቄምና በኢየሩሳሌም የሚኖሩ የእስራኤል ወገኖች አለቆች ሁሉ እንዳዘዙአቸው አደረጉ። 9የእስራኤልም ልጆች ከፍ ባለ ቃል ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ ሰውነታቸውንም በጽኑ ኀዘን አሳዘኑ። 10እነርሱም ሚስቶቻቸውና ልጆቻቸው፥ ከብቶቻቸውም፥ ምንደኛውና ስደተኛው ሁሉ፥ በዋጋም የተገዛው ሁሉ ማቅ ለብሰው አለቀሱ። 11የእስራኤልም ወገኖች ሁሉ ሚስቶቻቸውና በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ልጆቻቸውም በቤተ መቅደስ ደጃፍ ወደቁ፤ በራሳቸውም ትቢያ ነሰነሱ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ማቃቸውን አነጠፉ፤ መሠዊያውንም ማቅ አለበሱ። 12ልጆቻቸውን እንዳይነጠቁ፥ ሚስቶቻቸውን እንዳይማረኩ፥ የርስታቸው ከተሞችም እንዳይጠፉ፥ መቅደሳቸውንም እንዳያረክሱ፥ ለአሕዛብም መዘበቻ እንዳያደርጉት ወደ እስራኤል አምላክ በአንድነት ፈጽመው ጮኹ። 13እግዚአብሔርም መከራቸውን አይቶ ልመናቸውን ሰማ፤ ሕዝቡም በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ሁሉን በሚችል በእግዚአብሔር መቅደስ ፊት ብዙ ቀን ጾሙ። 14በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙ ታላቁ ካህን ኢዮአቄምና ካህናቱ፥ የእግዚአብሔርንም ሥራ የሚሠሩ ሰዎች በወገባቸው ማቅ ታጠቁ፤ የዘወትሩን መሥዋዕት፥ የስእለቱንና ሕዝቡ በፈቃድ የሚያቀርቡትን መሥዋዕት አገቡ። 15በራሳቸውም ዐመድ ነሰነሱ፤ በፍጹም ኀይላቸውም ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ “የእስራኤልንም ወገን በምሕረት ተመልከት” አሉ።