የሰላም መልእክተኞች
1እንዲህም ብለው የሰላም መልእክተኞችን ወደ እርሱ ላኩ። 2“እነሆ፥ እኛ የገናናው ንጉሥ የናቡከደነፆር ባሮች በፊትህ እንኖራለን። በፊትህም እንደ ወደድህ አድርገን። 3እነሆ፥ ከተሞቻችንና አንባዎቻችንም ሁሉ፥ እርሻችንም ሁሉ፥ መንጋዎቻችንም፥ የመሰማሪያችን ቦታዎች ሁሉ፥ በጎቻችንም በፊትህ ያንተ ናቸው፤ እንደ ወደድህም አድርግ። 4እነሆ ታላላቆች ከተሞቻችን በእነርሱ የሚኖሩ ሰዎች ባሮችህ ናቸው፤ መጥተህም እንደ ወደድህ አድርግ።” 5እነዚያም ሰዎች ወደ ሆሎፎርኒስ ደርሰው ይህን ነገር ነገሩት። 6እርሱም ወደ መንደራቸው ወረደ፤ ሠራዊቱም ከእርሱ ጋር ወረዱ ከፍ ከፍ ያሉ አንባዎችንም አስጠበቀ፥ ከእነርሱም የሚረዱትን የተመረጡ ሰዎችን ወሰደ። 7ወገኖቻቸው ሁሉና እነርሱም አክሊል ደፍተው እየዘፈኑ፥ በገና እየደረደሩና ከበሮ እየመቱ ተቀበሉት። 8እርሱ ግን አውራጃቸውን ሁሉ አጠፋ፤ ጣዖቶቻቸውንም ሰበረ፤ አሕዛብም ሁሉ ናቡከደነፆርን ብቻ እንዲያመልኩት፥ ቋንቋዎችና ነገዶች ሁሉ አምላክ እንዲሉት እርሱ የሰውን ሁሉ ጣዖት ያጠፋ ዘንድ ታዝዞ ነበር። 9በትልቁ በይሁዳ ተራራ አንፃር የገባኢያ ዕጣ ወደሚሆን ወደ ኤስድራሎንም መጣ። 10በሴቅቶን ከተማና በጌባን ሜዳ መካከልም ሰፈረ፤ ለሠራዊቱም ስንቅ ያዘጋጅ ዘንድ በዚያ አንድ ወር ተቀመጠ።