በምዕራብ በኩል በሚገኙ ሕዝቦች የተደረገ ጦርነት
1በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት በጨረቃ አቈጣጠር በመጀመሪያው ወር በሰባተኛው ቀን እንደ ተናገረው ሀገሩን ሁሉ ይበቀል ዘንድ በአሦር ንጉሥ በናቡከደነፆር ቤተ መንግሥት ምክር ተመከረ። 2ሹሞቹንና አለቆቹን ሁሉ ጠርቶ ከእነርሱ ጋር የምክሩን ምሥጢር ተነጋገረ፤ በሀገሩ ሁሉ ክፉ ነገርን ተናገረ። 3በአንደበቱ የተናገረውን ትእዛዝ ያልተቀበሉትን ሰዎች ሁሉ ያጠፋቸው ዘንድ ምክር ጨረሱ። 4ከዚህም በኋላ ምክሩን በጨረሱ ጊዜ የአሦር ንጉሥ ናቡከደነፆር ከእርሱ በታች ያለ ቢትወደዱ ሆሎፎርኒስን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ 5“የአገሩ ሁሉ ጌታ ገናናው ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ መቶ ሃያ ሺህ በኀይላቸው የታመኑ እግረኞች ሰዎችን መቶ ሃያ ሺህ ፈረሰኞችንም ከፈረሶቻቸው ጋራ ካንተ ጋራ ይዘህ እነሆ በፊቴ ትወጣለህ። 6በአንደበቴ ለተናገርሁት ነገር መታዘዝን እንቢ ብለዋልና በምዕራብ በኩል ወዳለች ሀገር ትወጣለህ። 7በእነርሱ ተቈጥቼ እወጣለሁና፥ ምድርንም በሠራዊቴ እግር እሸፍናታለሁና፥ ገንዘባቸውንም እዘርፋቸዋለሁ፥ እበረብራቸዋለሁምና ውኃውንና ሀገሩን ያዘጋጁልኝ ዘንድ ለእነርሱ አዋጅ ትነግራለህ። 8ቍስለኞቻቸውም በሸለቆውና በፈሳሹ ይመላሉ፤ ወንዙም ሬሳቸውን ተመልቶ ይፈስሳል፤ 9ምርኳቸውንም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ እበትነዋለሁ። 10አንተ ግን ቀድመህ አውራጃዎቻቸውን ሁሉ ያዝልኝ፤ ራሳቸውን ወዳንተ ቢመልሱ በእነርሱ እስከምፈርድበት ቀን ለእኔ ትጠብቃቸዋለህ። 11ዐመፀኞችን ታጠፋቸው ዘንድ፤ በሄድህበትም ሁሉ ትዘርፋቸው ዘንድ ዐይንህ አትራራላቸው። 12እኔ ሕያው ነኝና እንደ ተናገርሁም ይኽን በእጄ አደርግ ዘንድ መንግሥቴ ጽኑዕ ነውና። 13እንዳዘዝሁህ አድርግ እንጂ አንተም ከእኔ ከጌታህ ቃል አንዲት ስንኳ የምትተወው አይኑር፤ ይህንም ፈጥነህ አድርግ።”
የሆሎፎርኒስ ዘመቻ
14ሆሎፎርኒስም ከጌታው ፊት ወጥቶ ኀያላኑን፥ አዛዦችንና የአሦር ሠራዊት አለቆችን ሁሉ ጠራቸው። 15ጌታውም እንዳዘዘው መቶ ሃያ ሺህ የተመረጡ እግረኞች አርበኞችንና ዐሥራ ሁለት ሺህ ፈረሰኞች ቀስተኞችን ቈጠረ። 16ፈጽመው ይዋጉ ዘንድ አዘዛቸው። 17ስንቃቸውንም የሚጭኑባቸው እጅግ ብዙ የሆኑ ግመሎችንና አህዮችን፥ በቅሎዎችንም፥ ምግብም ሊሆኗቸው ቍጥር የሌላቸው በሬዎችንና በጎችን፥ ፍየሎችንም ወሰደ። 18ለብዙ ሰዎችና ለሠራዊቱ ሁሉ ከንጉሡ ቤት እጅግ ብዙ የሆነ ብርና ወርቅን ስንቅ አድርጎ ሰጣቸው። 19እርሱም ከሠራዊቱ ሁሉ ጋር ወጣ፤ በፈረሶችና በሠረገላዎች፥ በተመረጡ አርበኞችም በምዕራብ አንጻር ያለ ምድርን ሁሉ ይሸፍን ዘንድ ከንጉሡ አስቀድሞ ዘመተ። 20ከእነርሱም ጋር አንድ የሆኑ፥ ብዛታቸውም እንደ አንበጣና እንደ ባሕር አሸዋ የሆኑ ብዙ ሰዎች ከእነርሱ ጋር ወጡ። ከብዛታቸውም የተነሣ ቍጥር የላቸውም። 21ከነነዌም ወጥተው በበቄጤሊት ሜዳ አንጻር የሦስት ቀን ጎዳና ሄዱ፤ ከላይኛው ቂልቅያ በስተግራ በኩል ባለው ተራራ አጠገብ በበቄጤሊት አንጻር ሰፈሩ። 22ከዚያም ሆሎፎርኒስ ሠራዊቱን ሁሉ፥ ፈረሰኞችንና እግረኞችንም፥ ሠረገላዎችንም ይዞ ወደ ተራራማው ሀገር ሄደ። 23ፌድንና ሎድንም ወጋቸው፤ የሬስስን ልጆችን ሁሉ፥ በኤሌዎን ግራ አንጻር ባለ ሜዳ የሚኖሩ የእስማኤልንም ልጆች ማረካቸው። 24ኤፍራጥስንም ተሻግሮ ወደ መስጴጦምያ ሄደ፤ ወደ ባሕርም እስኪደርስ ድረስ በአርባኒ ወንዞች ላይ ያሉ ታላላቅ ከተሞችን ሁሉ አፈረሰ። 25የቂልቅያንም አውራጃ ያዘ፤ ጠላቱንም ሁሉ አጠፋ፤ በምዕራብም አንጻር በዐዜብ በኩል እስከ ያፌት አውራጃ ድረስ ሄደ። 26የምድያምንም ልጆች ሁሉ ከበባቸው፤ ከብታቸውንም ዘረፈ፤ ቤታቸውንም አቃጠለ። 27በስንዴ አዝመራ ጊዜም በደማስቆ ወዳለ ሜዳ ወርዶ አዝመራቸውን ሁሉ አቃጠለ፤ የላሞቻቸውንና የበጎቻቸውንም መንጋዎች ይዘርፏቸው ዘንድ አዘዘ፤ አምባቸውንም አፈረሰ፤ ልጆቻቸውንም ማረከ፥ ጎልማሶቻቸውንም ሁሉ በጦር ገደለ። 28ከእነርሱም የተነሣ መፍራትና ድንጋጤ በባሕሩ ዳርቻ በጢሮስና በሲዶና በሚኖሩ፥ በአቂናና በሴይርም፥ በያምኒያም በሚኖሩ ሰዎች ላይ ወደቀ። በአስቀሎናና በአዛጦንም የሚኖሩ ሰዎች ከርሱ መምጣት የተነሣ ፈጽመው ፈሩ።