ዮዲት ወደ ሆሎፎርኒስ ለመሄድ እንደ ተዘጋጀች
1ከዚህም በኋላ ወደ እስራኤል አምላክ መለመኗን ከጨረሰችና ይህንም ነገር ሁሉ ከፈጸመች በኋላ፥ 2ከወደቀችበት ቦታ ተነሣች፤ ብላቴናዋንም ጠርታ በሰንበታትና በበዓላት ቀኖች ወደምትቀመጥበት ቤትዋ ወረደች። 3የለበሰችውንም ማቅ አወለቀች፤ የመበለትነትዋንም ልብስ ለበሰች፥ ሰውነትዋንም በውኃ ታጠበች፤ ጠጕርዋንም ያማረ ሽቱ ተቀባች፤ ጠጕርዋንም ተሠራች፤ አጌጠችም፤ ከዚህም በኋላ ባሏ ምናሴ በሕይወት በነበረ ጊዜ የምትለብሰውን የደስታ ልብሷን ለበሰች። 4ጫማዋንም ተጫማች፤ አልቦዋንና ቀለበትዋን፥ አምባርዋንና ጉትቻዋንም አደረገች፤ ጌጡንም ሁሉ አጌጠች፤ የሚያዩአትንም ወንዶች ሁሉ ዐይን እስክታስት ድረስ ፈጽማ አጌጠች። 5የወይኑን ገንቦና የዘይቱን ማሰሮ ትሸከም ዘንድ ለብላቴናዋ ሰጠቻት፤ ስልቅ በሶውን፥ የስንዴ አምባሻውንና በለሱን በስልቻዋ መላች፤ ገንዘብዋንም ሁሉ አንግታ አሸከመቻት። 6ወደ ቤጤልዋ ከተማ በርም ሄደች፤ ዖዝያንን፥ ያገር ሽማግሌዎችን ከርሚንና ከብሪምንም በዚያ ቆመው አገኘቻቸው። 7ፊትዋ ተለውጦ፥ በሚያስደንቅ ሁኔታ ልብሷን ለብሳ ባዩአት ጊዜ ከደም ግባቷ ማማር የተነሣ እጅግ ተደነቁ፤ እንዲህም አሏት፦ 8“ለኢየሩሳሌም ልዕልናና ለእስራኤል ልጆች ክብር በልብሽ ያሰብሽውን ታደርጊ ዘንድ የአባቶቻችን አምላክ ሞገስን ይስጥሽ።” እርሷም ለእግዚአብሔር ሰገደች። 9እንዲህም አለቻቸው፥ “አሁንም ከእናንተ ጋራ የተናገርሁትንነገር ወጥቼ አደርግ ዘንድ የከተማውን በር የሚከፍትልኝ ሰው እዘዙልኝ፤” እንደ ጠየቀችም ይከፍቱላት ዘንድ ጐልማሶችን አዘዙአቸው። 10ይህንም በአደረጉ ጊዜ ዮዲት ወጣች፤ ብላቴናዋም ከእርሷ ጋር ወጣች፤ የከተማው ሰዎችም ካንባው ወርዳ ከሸለቆው እስክታልፍ ድረስ ያዩአት ነበር፤ ከዚህ በኋላ ግን አላዩአትም። 11በቀጥታም በሸለቆው ሄደች፤ የአሦራውያንም ዘበኞች አገኙአት። 12ይዘውም መረመሩአት፤ እንዲህም አሏት፥ “አንቺ ማን ነሽ? ከየት መጣሽ? ወዴትስ ትሄጃለሽ?” እርስዋም አለቻቸው፥ “እኔ ከዕብራውያን የተወለድሁ ነኝ፤ ሀገራቸውን ለእናንተ አሳልፈው ሊሰጡ በወደዱ ጊዜ ከእነርሱ ኰብልዬ መጣሁ። 13እኔ እውነተኛ ነገርን እነግረው ዘንድ፥ የምትሄዱበትንም ጎዳና አሳየው ዘንድ ወደ ቢትወደዳችሁ ወደ ሆሎፎርኒስ አስቀድሜ መጣሁ፤ አውራጃቸውንም ሁሉ ገንዘብ ታደርጋላችሁ፤ ከሰዎቻችሁ አንድ ሰው ስንኳ የሚቈስል የለም።” 14እነዚያም ሰዎች ቃልዋን በሰሙ ጊዜ፥ ፊትዋንም ባዩ ጊዜ፥ ደም ግባትዋም ፈጽሞ የተደነቀ እንደ ሆነ ባዩ ጊዜ እንዲህ አሏት፦ 15“ወደ ጌታችን ፈጥነሽ የወረድሽ አንቺ ሕይወትሽን አዳንሽ። አሁንም ወደ ድንኳኑ ሂጂ፤ ወደ እርሱ የሚያደርስሽን ሰው ከእኛ እንልካለን። 16በፊቱም በቆምሽ ጊዜ ይህን ነገርሽን ንገሪው እንጂ ልቡናሽ አይፍራ፤ በጎ ነገርን ያደርግልሻል።” 17ከእርስዋና ከብላቴናዋ ጋር የሚሄዱ አንድ መቶ ሰዎችን መረጡ፤ ወደ ሆሎፎርኒስ ድንኳንም አደረሷት። 18ሕዝቡም ሁሉ ተሰበሰቡ፤ በድንኳኑ ፊት እንዳለች ዜናዋ በሰፈሩ ተሰምቶ ነበርና መጥተው ስለ እርሷ እስኪነግሩት ድረስ ከሆሎፎርኒስ ድንኳን ውጭ ከብበዋት ቆሙ። 19ደም ግባትዋንም አደነቁ፤ ስለ እርስዋም የእስራኤልን ልጆች አደነቁ፤ እርስ በርሳቸውም፥ “እንደ እነዚህ ያሉ ሴቶች ያሉትን ሕዝብ የሚንቅ ማን ነው? ዓለሙን ሁሉ ሊተነኰሉ ስለሚችሉ ከእነዚህ ሰዎች አንድ ሰውስ እንኳ ይቀር ዘንድ መልካም አይደለም” ተባባሉ። 20በሆሎፎርኒስ አጠገብ የተቀመጡ አሽከሮቹም ሁሉ መጥተው ወደ ድንኳኑ አገቧት። 21ሆሎፎርኒስም በወርቅ፥ በመረግድና ዋጋው ብዙ በሆነ ዕንቍ የተሠራ ነጭ ሐር በተነጠፈበት በዙፋኑ ላይ በድንኳኑ ውስጥ ተኝቶ ነበር። 22የእርሷንም ነገር ነገሩት፤ ወደ አደባባይም ወጣ፤ በፊቱም የብር መቅረዝ ፋና ይበራ ነበር። 23ዮዲትም ወደ እርሱ በቀረበች ጊዜ አሽከሮቹ ቆመው ነበር፤ ከመልኳ ደም ግባት የተነሣ ሁሉም ተደነቁ፤ እርሷም በግንባሯ በምድር ላይ ወድቃ ሰገደችለት፤ አሽከሮቹም አነሡአት።