ዮዲት ከሆሎፎርኒስ ጋር ያደረገችው የመጀመሪያ ትውውቅ
1ሆሎፎርኒስም አላት፥ “አንቺ ሴት እመኝ፤ ለዓለሙ ሁሉ ንጉሥ ለናቡከደነፆር ይገዛ ዘንድ ራሱን ወደ እርሱ በመለሰ ሰው እኔ ክፉ ነገርን አላደርግምና ልቡናሽ አይፍራብሽ። 2አሁንም በአንባ የሚኖሩ እነዚህ ወገኖችሽ የወነጀሉን ባይሆኑ ኖሮ በእነርሱ ላይ ጦሬን ባላነሣሁም ነበር፤ ነገር ግን ይህን ነገር እነርሱ አደረጉት። 3አሁንም ንገሪኝ፤ ከእነርሱ ዘንድ ስለምን ነገር ኰብልለሽ ወደ እኛ መጣሽ? ነገር ግን ለሕይወትሽ መጥተሻልና በዚህ ሌሊት ለሁልጊዜም እንድትድኚ እመኝ። 4ለንጉሡ ለጌታችን ለናቡከደነፆር አሽከሮች እንደምናደርግ ላንቺ ከምናደርገው በጎ ነገር በቀር በአንቺ ክፉ ነገር የሚያደርግ የለም።” 5ዮዲትም አለችው፥ “የእኔን የባሪያህን ቃል ተቀበል፤ እኔ ባሪያህ በፊትህ እነግርሃለሁ፤ በዚች ሌሊት እኔ ለጌታዬ ሐሰት ነገርን አልነግርህም። 6የእኔን የአገልጋይህን ቃል ከተከተልህ እግዚአብሔር ለአንተ ፍጹም ሥራ ይሠራልሃል፤ አንተ ጌታዬ ካሰብኸው ነገር የሚወድቅ የለም። 7የምድር ሁሉ ንጉሥ ናቡከደነፆር በሕይወት ይኑር! ፍጥረቱን ሁሉ ታቀና ዘንድ አንተን የላከ ኀይሉ ይኑር። በምድረ በዳ የሚኖሩ አውሬዎችና እንስሳ፥ በሰማይ የሚበሩ ወፎችም በኀይልህ ከናቡከደነፆርና ከቤቱ በታች ይኖራሉ እንጂ በዘመንህ ሰዎች ብቻ የሚገዙለት አይደለም። 8ሥራህንና የልቡናህን ጥበብ ሰምተናልና በመንግሥቱ ሁሉ አንተ ብቻ ቸር እንደ ሆንህ፥ በአገሩ ሁሉ ተሰምትዋልና፥ በሥራህም ሁሉ አንተ ብርቱ ነህና፥ በሰልፍህም ሁሉ አንተ የተደነቅህ ነህና። 9“አሁንም አክዮር በጉባኤያችሁ የአላችሁን ነገር ሰማን፤ ለአዳኑት የቤጤልዋ ሰዎችም ለአንተ የነገረህን ነገር ሁሉ ነገራቸው። 10አቤቱ ጌታዬ፥ ነገሩን አትናቅ፤ ነገር ግን እውነት ስለሆነ በልብህ አኑረው፤ ፈጣሪያቸውን ካልበደሉ ሕዝባችን ሊጠፉ አይችሉም፤ ሰይፍም ሊያጠፋቸው አይችልም። 11አሁንም ጌታዬ የተናቀና የማይረባ እንዳይሆን በፊትህ ሞታቸው ይደርስባቸው ዘንድ በበደላቸው ሥራ አምላካቸውን ያሳዘኑባት ኀጢአታቸው በዚህ ታገኛቸዋለች። 12እህላቸውና ውኃቸው አልቋልና፥ ከብታቸውንም ይበሉ ዘንድ ተመልሰዋልና፥ እንዳይበሉ አምላካቸው በኦሪታቸው የከለከላቸውን ያን ይበሉ ዘንድ ደርሰዋልና። 13የእህላቸውን መጀመሪያና የወይናቸውን ዐሥራት በፈጣሪያችን ፊት በኢየሩሳሌም ለሚቆሙ ለካህናት የለዩትን፥ ከሕዝቡም ላንድ ሰው ስንኳ በእጃቸው መዳሰስ የማይገባቸውን ይህን ዘይቱንም ሊበሉ አስበዋልና፥ 14ከአለቆችም ፈቃድ ያመጡላቸው ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ላኩ፤ በዚያ የሚኖሩ ሰዎች እንዲህ አድርገዋልና። 15ፈቃዱን ከነገሩአቸውና እንዲህ ከአደረጉ በኋላ እንዲህ አድርገዋልና በዚያ ጊዜ እግዚአብሔር በእጅህ ይጥላቸዋል። 16“እኔ ባርያህ ይህን ሁሉ በዐወቅሁ ጊዜ ከእነርሱ ኰበለልሁ፤ የሰማውን ሰውንና ምድርን ሁሉ የሚያስደነግጥ ይህን ሥራ ከአንተ ጋር እሠራ ዘንድ እግዚአብሔር ላከኝ። 17እኔ አገልጋይህ እግዚአብሔርን የምፈራ ነኝና የሰማይ አምላክ እግዚአብሔርንም በመዓልትና በሌሊት አገለግለዋለሁ። አቤቱ፥ አሁንም ከአንተ ጋር እኖራለሁ፤ ነገር ግን እኔ አገልጋይህ ወደ እግዚአብሔር እለምን ዘንድ ሌሊት ወደ ምድረ በዳ እወጣለሁ፤ መቼም የሠሩትን ኀጢአታቸውን ይነግረኛል። 18መጥቼም ይህን እነግርሃለሁ፤ ከሠራዊትህ ሁሉ ጋር ትወጣለህ፤ የሚቃወምህም አይኖርም። 19ወደ ኢየሩሳሌም እስክትደርስም ድረስ በይሁዳ መካከል እወስድሃለሁ፤ በመካከሏም ዙፋንህን ትዘረጋለህ እረኛቸውም እንደ በተናቸው በጎች ፈጽመህ ትከብባቸዋለህ፤ ውሻም በፊትህ አይጮህብህም። ለእኔ እንዲህ ተነግሮኛልና። ይህንም ዐውቄ እነግርህ ዘንድ ተላክሁ።” 20ነገሯም ሆሎፎርኒስንና ሰዎቹን ሁሉ ደስ አሰኛቸው። እነርሱም ጥበቧን አደነቁ። 21እንዲህም አሉ፥ “ከምድር ዳርቻ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ በፊቷ ደም ግባትና በቃልዋ ጥበብ እንደዚች ሴት ያለ የለም።” 22ሆሎፎርኒስም አላት፥ “ኀይል በእጃችን፥ ጥፋትም ጌታዬን በካዱት ላይ ይሆን ዘንድ ከሕዝብሽ አስቀድሞ የላከሽ እግዚአብሔር በጎ ነገርን አደረገ። 23አሁንም አንቺ በመልክሽ ውብ ነሽ፤ በቃልሽም የተባረክሽ ነሽ፤ እንዳልሽውም ከአደረግሽ አምላክሽ አምላኬ ይሆነኛል፤ አንቺም በንጉሡ በናቡከደነፆር ቤተ መንግሥት ትኖሪያለሽ፤ ስምሽም በሀገሩ ሁሉ ከፍ ከፍ ይላል።”