ዮዲት በሆሎፎርኒስ እንደ ተጋበዘች
1የብር ዕቃ ወደሚቀመጥበት ድንኳን ያገቧት ዘንድ አዘዘ፤ ለእርሱም ከሚያዘጋጁት ምግብ ይመግቧት ዘንድ፥ እርሱ ከሚጠጣው መጠጥም ያጠጧት ዘንድ አዘዘ። 2ዮዲትም፥ “ካመጣሁት እህል እመገባለሁ እንጂ በደል እንዳይሆንብኝ ከእርሱ አልመገብም” አለች። 3ሆሎፎርኒስም፥ “ያመጣሽውስ ቢያልቅብሽ እንደ እርሱ ያለ ከየት አምጥተን እንሰጥሻለን? ከወገኖችሽ ስንኳ ካንቺ ጋር ያለ ሰው የለም” አላት። 4ዮዲትም፥ “እግዚአብሔር በእኔ ቃል የመከረውን እስኪያደርግ ድረስ እኔ አገልጋይህ የያዝሁትን እንዳልጨርስ ጌታዬ ሕያው ነፍስህን” አለችው። 5የሆሎፎርኒስም አሽከሮች ወደ ድንኳኑ አገቧት፤ እስከ እኩለ ሌሊትም ድረስ ተኛች። ሌሊቱም ከመንጋቱ በፊት በእኩለ ሌሊት ተነሣች፤ 6“እኔ አገልጋይህ ለጸሎት እንድወጣ ይፈቅዱልኝ ዘንድ እዘዝልኝ” ብላ ወደ ሆሎፎርኒስ ላከች። 7ሆሎፎርኒስም እንዳይከለክሏት የሚጠብቁትን ሰዎች አዘዛቸው፤ ከዚህ በኋላም በሰፈር ሦስት ቀን አደረች፤ በየሌሊቱም እየወጣች ወደ ቤጤሌዋ ሸለቆ ትወርድ ነበር፤ ሌሊትም በሰፈሩ ምንጭ ውኃ ትታጠብ ነበር፤ ሌሊትም ወጥታ በምንጩ ውኃ ትጠመቅ ነበር። 8ከውኃውም በወጣች ጊዜ ስለ ወገኖችዋ ልጆች መነሣት መንገድዋን ያቃናላት ዘንድ ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር ትጸልይ ነበር። 9ከዚህም በኋላ ትመለስ ነበር፤ በሰፈርም በንጽሕና ትቀመጥ ነበር፤ ማታ ማታም ትመገብ ነበር። 10ከዚህም በኋላ በአራተኛዪቱ ቀን ሆሎፎርኒስ ለአሽከሮቹ ለብቻቸው ምሳ አደረገ፤ ሌላ ሰው ማንንም ወደ ምሳው አልጠራም። 11የገንዘቡ ሁሉ መጋቢ የሆነውን ጃንደረባ ባግዋን፥ “በአንተ ዘንድ ያለች ያችን ዕብራዊት ሴት ወደ እኛ ትመጣ ዘንድ አባብልልኝ፤ ከእኛ ጋር ትብላ፤ ትጠጣም፤ ሄደህም ንገራት። 12እንዲህ ያለች ሴት አግኝተን ባናነጋግራት ለእኛ ዕፍረታችን ነውና፥ ባንገናኛትም ይስቁብናልና” አለው። 13ባግዋም ከሆሎፎርኒስ ዘንድ ወጥቶ ወደ እርሷ ገባ፥ “መልከ መልካም የሆንሽ አንቺ ልጄ ሆይ! ወደ ጌታዬ መምጣትን እንቢ አትበዪ፤ በእርሱ ዘንድ ትከብሪያለሽ፤ ከእርሱም ጋራ ወይንን ጠጥተሽ ደስ ይልሻል፤ በናቡከደነፆር ቤት ከሚያገለግሉት ከአሦር ልጆችም እንደ አንዲቱ ትሆኛለሽ” አላት። 14ዮዲትም አለችው፥ “ጌታዬን እንቢ እለው ዘንድ እኔ ማን ነኝ? ወገኔስ ማን ነው? የወደድኸውን ሁሉ በፊትህ ፈጥኜ አደርጋለሁ፤ እስክሞትም ድረስ ለእኔ ደስታ ይሆንልኛል፤” 15ተነሥታም ልብሷን ለበሰች፤ የሴቶችንም ጌጥ ሁሉ ፈጽማ አጌጠች፤ ብላቴናዋም ከእርሷ ጋራ ሄደች፤ ከባግዋ የተቀበለችውን፥ በማደሪያዋ ያነጠፈላትን፥ ምሳም ስትበላ የምትቀመጥበትን ምንጣፏን በሆሎፎርኒስ ፊት በምድር ላይ አነጠፈችላት። 16ዮዲትም ወደ እርሱ ገብታ ተቀመጠች፤ የሆሎፎርኒስም ልቡናው በእርሷ ታወከ፤ ከእርሷም ጋር ይተኛ ዘንድ ሰውነቱ ፈጽማ ጐመጀች፤ ከአያትም ጀምሮ እርሷን እስከሚያባብልበት ጊዜ ይጠብቃት ነበር። 17ሆሎፎርኒስም ዮዲትን፥ “ጠጥተሽ ከእኛ ጋር ደስ ይበልሽ” አላት። 18ዮዲትም፥ “ከተወለድሁ ጀምሮ ከዘመኔ ሁሉ ይልቅ ሕይወቴ ዛሬ ከብራለችና ጌታዬ እጠጣለሁ” አለችው። 19አገልጋይዋም ያዘጋጀችላትን ተቀብላ በፊቱ በላች፤ ጠጣችም። 20ሆሎፎርኒስም ስለ እርሷ ደስ አለው፤ ከተወለደም ጀምሮ አንዲት ቀን ስንኳ እንደዚያ ያልጠጣውን ብዙ ወይን አብዝቶ ጠጣ።