ዮዲት የሆሎፎርኒስን ቸብቸቦ እንደ ቈረጠች
1በመሸም ጊዜ አሽከሮቹ ፈጥነው ሰውን አስወጡ፤ ባግዋም ከወደ ውጭ በላያቸው ድንኳኑን ዘጋ፤ በጌታውም ፊት የቆሙ አሽከሮቹን አስወጥቶ ሰደዳቸው፤ ፈጽመው ስለጠጡ ሁሉም ደክመዋልና ወደ ማደሪያቸው ገቡ። 2ዮዲትም ብቻዋን በድንኳን ውስጥ ከሆሎፎርኒስ ጋር ቀረች፤ እርሱ ግን አብዝቶ ወይን ስለጠጣ ሰክሮ በአልጋው ላይ ተኝቶ ነበር። 3ዮዲትም አገልጋይዋን ወደ ውጭ ወጥታ በማደሪያዋ ትቆም ዘንድ አዘዘቻት፤ “ወደምጸልይበት እወጣለሁ” ብላታለችና እንደ ወትሮው በምትመጣበት ጊዜ ትጠብቃት ዘንድ አዘዘቻት፤ ለባግዋም እንደዚሁ ነገረችው። 4ሁሉም ከእርስዋ ዘንድ ወጡ፤ ታናሽም፥ ታላቅም ቢሆን በእልፍኙ የቀረ አልነበረም። ዮዲትም ተነሥታ በመኝታው አጠገብ ቆመች። በልቧም፥ “የኀይል ሁሉ አምላክ አቤቱ፥ ይህን ነገር እይ፤ ኢየሩሳሌም ከፍ ከፍ ትል ዘንድ በዚች ሰዓት በእኔ እጅ ኀይልህን አድርግ። 5ርስትህን ታነሣ ዘንድ ጊዜው ደርሷልና በእኛ የተነሡ ጠላቶች ይጠፉ ዘንድ አሳቤን ሁሉ ፈጽምልኝ” አለች። 6ወደ ሆሎፎርኒስም መኝታ ወደ ትራሱ ሄደች፤ የራስጌ ሰይፉንም መዘዘች። 7በራስጌውም ቆመች፤ የራሱንም ጠጕር ይዛ “የእስራኤል አምላክ አቤቱ፥ ዛሬ አጽናኝ” አለች። 8በኀይሏ ሁለት ጊዜ አንገቱን መታችው፤ ራሱንም ቈረጠችው። 9ሬሳውንም ከመኝታው ወደ ምድር ጣለችው፤ የራስጌ መጋረጃውንም ከምሰሶው አወረደች፤ ጥቂትም ዐረፈች፤ ወጥታም ለብላቴናዋ የሆሎፎርኒስን ቸብቸቦ ሰጠቻት።
ዮዲት ወደ ቤጤልዋ እንደ ተመለሰች
10እህል በምትይዝበት ከረጢትም ጨመረችው፤ ለጸሎት እንዳስለመዱ ሁለቱ ሁሉ በአንድነት ወጡ፤ ከሰፈሩም አልፈው ወደ ሸለቆው ዞሩ፤ ወደ ቤጤልዋ ዐቀበትም ወጡ፤ ወደ ከተማውም በር ደረሱ። 11ዮዲትም በሩቁ ሆና በር የሚጠብቁ ዘበኞችን፥ “ዛሬ ኀይልን እንዳደረገ ዳግመኛ ለእስራኤል በጠላቶቻቸው ላይ ጽናትና ኀይልን ያደርግ ዘንድ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር አለና ክፈቱ፤ ክፈቱ” አለቻቸው። 12ከዚህም በኋላ የከተማው ሰዎች ቃልዋን በሰሙ ጊዜ ወደ ከተማው በር ፈጥነው ወረዱ፤ የከተማ ሽማግሌዎችን ጠሩ። 13እንደ ተመለሰችም አድንቀዋልና ታናሹም፥ ታላቁም ሁሉ ሮጠው ሄዱ፤ በሩንም ከፍተው ተቀበሏት፤ እሳትም አንድደው፥ ፋና አብርተው ከበቧት። 14“ጠላቶቻችንን በዚች ሌሊት በእጄ አጠፋቸው እንጂ ምሕረቱንና ይቅርታውን ከእስራኤል አላራቀምና በታላቅ ቃል እግዚአብሔርን አመስግኑት፤ አመስግኑት። እግዚአብሔርንም አመስግኑት” አለቻቸው። 15ቸብቸቦውንም ከከረጢቷ አውጥታ አሳየቻቸው፤ “የአሦር ሠራዊት አለቃ የሆሎፎርኒስ ቸብቸቦ እነሆ፥ በሚጠጣ ጊዜ ተንተርሶት የሚተኛበት ሰይፉም እነሆ፥ እግዚአብሔር በእኔ በሴቷ አድሮ ገደለው። 16እንዲሞት በመልኬ አስተው ዘንድ በሄድሁበት ጎዳና የጠበቀኝ፥ በእኔም ኀጢአትንና በደልን፥ መዋረድንም ያላደረገ እግዚአብሔር ሕያው ነው” አለቻቸው። 17ሕዝቡም ሁሉ ፈጽመው አደነቁ፤ ለእግዚአብሔርም ፈጽመው ሰገዱ፤ በአንድነትም እንዲህ አሉ፥ “ዛሬ በዚች ቀን የወገኖችህን ጠላቶች ያጠፋሃቸው አንተ አምላካችን ቡሩክ ነህ።” 18ዖዝያንም እንዲህ አላት፥ “በዚህ ዓለም ከሚኖሩ ሴቶች ይልቅ አንቺ ልጄ፥ ልዑል እግዚአብሔር የባረከሽ ነሽ። ሰማይንና ምድርን የፈጠረ፥ የጠላቶቻችንን አለቃ ቸብቸቦ ትቈርጪ ዘንድ የረዳሽ እግዚአብሔር አምላክም ቡሩክ ነው። 19ለዘለዓለሙ የእግዚአብሔርን ኀይል እያሰቡ ምስጋናሽ ከሰው ልቡና አይጠፋምና። 20እግዚአብሔር ይህን ለዘለዓለም እንድትከብሪ ያድርግልሽ፤ ስለ ወገኖችሽ አንቺ ልሙት ብለሽ ወጣሽ እንጂ፥ በፈጣሪያችን በእግዚአብሔርም ፊት በቀጥታ ሄድሽ እንጂ ለሰውነትሽ አልራራሽምና በቸርነቱ ይመልከትሽ።” ሕዝቡም ሁሉ፥ “አሜን፥ አሜን” አሉ።